መግቢያ:

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት በሁሉም መስክ በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ ማንኛቸውንም አስተያየቶች፣ ወቀሳዎች፣ የመፍትሄ ሀሳቦች፣ የምርምር ውጤቶች፣ የሌሎች አካባቢዎች ውጤታማ ተሞክሮዎች በራሳቸው በየዘርፎቹ ባለሙያዎች በማራኪ አቀራረብ ተሰናድተው በነጻነት የሚስተናገዱበት የሀሳብ መለዋወጫ መድረክ ነው፡፡

በተጨማሪም ልዩ ልዩ ቃለመጠይቆች፣ የምርመራ ጋዜጠኝነት ውጤቶች እና  ትንታኔዎች በጽሁፍ እና በድምጽ የሚቀርቡበትም ልዩ መድረክ ነው፡፡

ስለሆነም፡ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሚወጡት ፅሁፎች ስፖርቱን እና የስፖርቱን ከባቢ  በማገልገል እና በመለወጥ  ዙሪያ የተቃኙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ስፖርት እና የስፖርት ባለሞያዎችን  ስምና ክብርም የሚመጥኑ እና የሚጠብቁ መሆን አለባቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሚዛናዊነት እና ለባለሙያዊነት ተገቢውን ክብር በመስጠት ከግላዊ ጥላቻና አንድን አካል ለይቶ የማጥቃት ስሜት ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

የጽሁፍ አቅራቢዎች፡ የሚደግፉትም ሆነ የሚተቹት እውነት እና ማስረጃን ብቻ መሠረት በማድረግ መሆን አለበት፡፡

ይህንን ለማሳካት ደግሞ ልንከተላቸው የሚገቡ መሰረታዊ  መርሆዎች አሉ፡፡

ከዚህ በታች የተጠቀሱት መርሆዎች ሙሉ በሙሉ በልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ ፀሀፊዎች ሊከበሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡

 1. ስነ ምግባር እና ህግን ማክበር
 • የሙያ ስነ ምግባራትን ማክበር ይኖርብናል፡፡ አለም አቀፍ የጋዜጠኝነት የስነምግባር መርሆዎች በሁሉም የኤዲቶሪያል አባላት የሚሰሩይሆናል፡፡
 • የሐገሪቱን ህጎች ማክበር ይኖርብናል፡፡
 1. አሰራር
 • ሀላፊነትን መውሰድ ፡-በዚህ ድረ-ገጽ ላይ የሚታተሙ ማናቸውም አስተያዬቶች፣ ወቀሳዎች እና የመፍትሄ ሀሳቦች ሙሉ ሀላፊነቱንም ሆነ ክብሩን የሚወስዱት የፅሁፎቹ ባለቤቶችናቸው፡፡ ቅሬታ ያላቸው አካላት ካሉ ድረ-ገጹ ሃሳባቸውን የሚገልጹበትን መድረክ ያመቻቻል፡፡ 
 • ስማቸው የማይጠቀስ ፀሀፊዎች እና ምንጮች ፡- ስማቸው የማይጠቀስ ፀሀፊዎች እና ምንጮች የድረ-ገጹን አመኔታ ይቀንሳሉ፡፡ በመሆኑም የመጨረሻ አማራጭ ካልሆነ በስተቀር ስማቸውን መግለፅ የማይፈልጉ ፀሀፊዎችን እና ምንጮችን አንጠቀምም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ስማቸውን መግለፅ የማይችሉ ፀሀፊዎችን ሀሳቦች የምናስተናግድባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ስማቸውን እንደማንጠቀም ቃል የገባንላቸውን ሰዎች ማንነት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ይፋ አናደርግም፡፡ 
 • የአካዳሚ ስርቆት (plagiarism) ፡- ከሌሎች ህትመቶች፡ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች እና ድረ ገፆች የተገኙ መረጃዎች በሙሉ ምንጫቸው መጠቀስ አለበት፡፡ 
 • ጎሳ/ብሄር እና ሀይማኖት፡- ለዘገባው እጅግ የሚያስፈልግ እንደሆነ ካልታመነበት በስተቀር የአስተያየት ሰጪዎችን ወይም ምንጮችን ጎሳ/ብሔር እና ሐይማኖት አንገልፅም፡፡ 
 • የቃል አጠቃቀም፡- በማናኛውም መንገድ ሀሳቦቻችንን ስንገልጽ፡ የሰዎችን ስብዕና ሊነኩ የሚችሉ ቃላትን መጠቀም የለብንም፡፡ 
 • ራስን ማስተዋወቅ፡- ለልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ ሃሳቦቻችንን በምንፅፍበት ወቅት በቅድሚያ ራሳችንን እና መደበኛ ሙያችንን  ማሰተዋወቅ ይኖርብናል፡፡ 
 • የፎቶግራፍ አጠቃቀም፡- ለግራፊክስ ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር ፎቶግራፎችን ከመጀመሪያ ይዞታቸው መቀየር የለብንም፡፡ ለግራፊክስ እና ለማሳያነት የምንጠቀምባቸው ከሆነ በግርጌ ማስታዎሻ መግለፅ ይኖርብናል፡፡ ከሌሎች ቦታዎች የተገኙ ፎቶግራፎች ከሆኑ ምንጫቸው መጠቀስ አለበት፡፡ ከግለሰቦች የተገኙ ከሆኑ ፎቶዎቹን ለማተም ፍቃድ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ 
 1. የግል ባህሪያት እና የጥቅም ግጭት
 • መልካም ስም፡- በልዩ ስፖርት ድረ-ገፅ የሚወጡ ፅሁፎች እና ሀሳቦች፣ ድረ-ገጹ ይዞት የተነሳውን የኢትዮጵያን ስፖርት በመሰረታዊነት የመለወጥ በጎ አላማ እና ከሁሉም ዘርፍ የሆኑ አንባቢዎቹን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ፀሀፊዎቹ  ይህንን በጎ ስም ሊያጎድፉ ከሚችሉ ተግባራት ራሳቸውን ማቀብ ይኖርባቸዋል፡፡                                     
 1. የፅሁፍ አቀራረብ
 • በሚገባ ዝግጅት የተደረገባቸው፣ ሞጋች፣ ማጣቀሻ የሚቀርብባቸው እና የተሟላ መልእክት የሚያስታልፉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
 • ዘገባዎቹ ህይወት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህም መግቢያ፣ መከራከሪያ፣መፍትሔ እና ስነጽሁፋዊ ውበት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡
 • ፅሁፎቹ ሀተታ /feature/ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

የልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ ኤዲቶሪያል መርሆዎች 

አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ

ታህሳስ 2011 ዓ.ም

www.liyusport.com