አዲስ አበባ ነሀሴ 03/2011ዓ.ም – ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ወጥቶበት በከፍተኛ የጥራት ደረጃ የተሰራውና በወልድያ ከተማ የሚገኘው የሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል በአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ሳይታይ እና ሳይመዘን በደፈናው በሀገሪቱ ውስጥ ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም የለም መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ገለጹ፡፡

ዶ/ር አረጋ ስለሁኔታው ሲያስረዱ ስታዲየሙን ለመገንባት ሼክ ሙሐመድ ወደ 600 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ማድረጋቸውን አስታውሰው ስታዲየሙ በአገር ውስጥ አቅም፣ በአገር ውስጥ መሐንዲሶችና ባለሙያዎች መገንባቱን፣ ሁለገብ ስታዲየም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስታዲየሙ በካፍ በትክክል ተገምግሞ ያላሟላው ነገር ባልተገለጸበት ሁኔታ በደፈናው በሀገሪቱ ዝቅተኛ መሰፈርት የሚያሟላ ስታዲየም የለም መባሉ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሶቹ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪዎች ወልድያ ስታዲየምን ያውቁታል ብለው እንደማይገምቱ የተናገሩት ዶ/ር አረጋ ሄደው አይተውት ቢሆን ኖሮ እዚህ ድምዳሜ ላይ ባልተደረሰ ነበር ብለዋል፡፡

አንዳንድ እግር ኳስ ቡድኖች ለልምምድ ወደዱባይ እንደሚሄዱ መስማታቸውን፣ ነገርግን ወልድያ የሚገኘው ስታዲየም የሜዳው ውሃ በቀላሉ ማስወገድ የሚያስችል የድሬኔጅ ሲስተም የተገጠመለት በመሆኑ በክረምት ወራት ጭምር በቀላሉ ማጫወት የሚችል ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ይህንን ሜዳ ሊጠቀሙበት ይችሉ ነበር ብለዋል፡፡

የሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ያለውን አቅም አውቆ በማስተዋወቅ ረገድ ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞችም ድክመት እንዳለባቸው ዶ/ር አረጋ ጠቅሰዋል፡፡

የነገሩ አመጣጥ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮን ፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ በስድስት በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታዲዮሞች ግምገማ በማድረግ ኢትዮጵያ በካፍ የተመዘገበ ውድድርን ማካሄድ የምትችልባቸው ዝቅተኛውን መስፈርት ሊያሟሉ የሚችሉ ስታዲየሞች እንደሌሏት በደብዳቤ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያን በካፍ ሻምፒየንስ ሊግና በኮንፌዴሬሽን የወከሉት የመቀለ 70 እንደርታና ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድኖች የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች ስታዲየሞች በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ስታዲየሞቹ የካፍን ዝቅተና መስፈርት እስኪያሟሉ ድረስ ብቻ በመቀለ እና በባህርዳር ስታዲየሞች እንዲደርጉ ካፍ ፈቅዷል፡፡

ጥቂት ስለ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል

የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ በመደቡት ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በጀት በወልድያ ከተማ ግንባታው የተጠናቀቀውና «ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል» በመባል የተሰየመው፣ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ የሚገመተው ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም፤ ቅዳሜ ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል ድርጅት በሆነው ሁዳ ሪልስቴትስ አ/ማ አማካይነት ኮንትራክተርነት ሥራው የተከናወነው ይህ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታው የጀመረው በ2003 ዓ.ም ሲሆን ግንባታው ማጠናቀቂ ድረስ ግማሽ ቢሊየን ብር የሚደርስ ወጪ በሼህ ሙሐመድ ተሸፍኗል፡፡ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር በሆኑት ዶ/ር አረጋ ይርዳው የቅርብ አመራርና ሙያዊ ክትትል የተደረገለት ይህ ሁለገብ ስታዲየም «ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል» በሚል ስያሜ ለወልዲያ ከተማ ሕዝብና አስተዳደር በስጦታ መበርከቱም የሚታወስ ነው፡፡

ስለስታዲየሙ አጠቃላይ መረጃ

 • በ19 ሺ ሄክታር መሬት ስፋት ላይ ያረፈ ነው፣
 • የዓለም አቀፉን እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) ደረጃ የሚያሟላ 105 ሜትር ርዝመት፣ 68 ሜትር የእግርኳስ ሜዳ እና ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ደረጃን የጠበቀ የመሮጫ ትራክ አሉት፣
 • ርዝመቱ 47 ሜትር፣ የጎኑ ስፋት 26 ሜትር የሆነ የተሟላ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ፣ የቅጫት ኳስ ሜዳዎችን በአንድ ላይ የያዘ ሁለገብ ሜዳ እና እያንዳንዱ 24 ሜትር በ11 ሜትር የሆኑ ሁለት የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ ሜዳዎችን እንዲሁም የኦሎምፒክ ደረጃን የጠበቀ ስፋቱ 25 ሜትር በ50 ሜትር፣ ጥልቀቱ ከ2 እስከ 5 ሜትር የሚደርስ የመዋኛ ገንዳም አካቷል፣
 • ስታዲየሙ በአንድ ጊዜ 25 ሺ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችሉ የፕላስቲክ ወንበሮች ተገጥመውለታል፡፡ ከእነዚህ መካከል 100 ደረጃቸውን የጠበቁ ወንበሮች ለክብር እንግዶች (ቪአይፒ)፣ 50 ወንበሮች ደግሞ ለአሰልጣኞች፣ ለተቀያሪ ተጫዋቾች እና ለአራተኛው ዳኛ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለወንዶችና ለሴቶች ተለይተው የተዘጋጁ የልብስ መቀየሪያ ክፍሎችን ይዟል፣
 • ስታዲየሙ ለተመልካቾች ምቾት ሲባል ዙሪያውን ጥላ (canopy) ያለው ሲሆን በምሽት ወቅት አገልግሎት ለመስጠት 156 ዘመናዊ መብራቶች ተገጥመውለታል፡፡ የሜዳው ብርሃን በተጨዋቾች ዕይታ ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር ለሜዳው በቂ ብርሃን እንዲሰጥ ተደርጎ ተሰርቷል፣
 • ስታዲየሙ ዙሪያውን 7 በሮች፣ በአደጋ ጊዜ ወደሜዳው ሊያስገባ የሚችል የአምቡላንስ ተሽከርካሪ መተላለፊያ በር አለው፣ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አካቷል፣
 • ስታዲየሙ በሶስት ደረጃዎች የተከፋፈሉ 32 መኝታ ክፍሎች እና ባለአንድ ፎቅ የእንግዳ ማረፊያ ያለው ሲሆን በተጨማሪም የገላ መታጠቢያ ክፍሎች፣ መጸዳጃ ቤቶች (በተለያዩ ቦታዎች ከ238 በላይ)፣ ቢሮዎች፣ የተጎዱ ተጨዋቾች ማረፊያ ክፍሎች፣ የሕክምና መስጫ ክፍሎች፣ የእንግዳ ማረፊያ አሉት፣
 • የክብር ትሪብዩኑ ሕንጻ ባለሶስት ፎቅ ሆኖ በውስጡ በአንድ ጊዜ አራት ቡድኖችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ ክፍሎች አሉት፡፡ የልብስ መቀየሪያ ክፍሎች፣ ሻወር፣ መጸዳጃ፣ የስብሰባ፣ የህክምና ወዘተ ክፍሎችም አሉት፡፡ በተጨማሪም ሕንጻው የክብር እንግዶች ማረፊያና ማስተናገጃ፣ ጨዋታዎችን በራዲዮ ወይንም በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ስምንት ቻናሎች እና የድምጽ መከላከያ (Sound proof) የተገጠሙለት የጋዜጠኞች ክፍል እንዲሁም ለተመልካቾች ምግብ ማዘጋጃ ክፍሎች አሉት፣
 • ለስታዲየሙ በዝናብ ጊዜ መጫወት እንዲያስችል የሰረገን ውሃ ወደውጭ የሚያስተላልፍ ደረጃውን የተበቀ የተፋሰሰ ቦይ (Drange system) አለው፡፡
 • በተመረጡ ሥፍራዎች የድምጽ ማጉያዎች ሲስተም ተገጥመውለታል፣ የውድድር ውጤቶችን ጎላ ባለ ሁኔታ ለማስታወቅ የሚያስችል የነጥብ ማሳያ ሰሌዳ አካቷል፣
 • ስታዲየሙ በአንድ ጊዜ እስከ 270 ሜትር ኪዩብ ወይም 270 ሺ ሊትር ውሃ ለማጠራቀም የሚያስችሉ 36 ታንከሮች ተገጥመውለታል፣ ድንገተኛ የእሳት አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ ሶስት የውሃ የእሳት ማጥፊያዎች እንዲሁም በቁጥር 14 የሆኑ በካርቦንዳይኦክሳይድ እሳት ማጥፊያ ሲሊንደሮች በተመረጡ ቦታዎች እንዲቀመጡ ተደርገዋል፣
 • ስታዲየሙ ከወልዲያ ከተማ በስተምዕራብ ቀደም ሲል መቻሬ እየተባለ በሚጠራና ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በቅርበት የሚገኝ ሲሆን የአካባቢው መልክዐምድር ማራኪ መሆኑ ተጨማሪ ውበትን አላብሶታል፡፡

መረጃው፡ የድሬ ቲዩብ ነው

author image

About Liyusport.com

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *