የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2019ኙ የፊፋ የሴቶች የአለም ዋንጫ እና በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ወቅት ሀላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ፡ ባምላክ ተሰማ፡ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እንዲሁም የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ በአመቱ መገባደጃ በሚከናወን ደማቅ ስነ ስርዓት እውቅና እንደሚሰጣቸው አስታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የዳኞች ብሄራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ‹‹በተለይም ዳኞቻችን ምንም እንኳን በሀገራችን ውድድሮች ላይ ተገቢው ክብር እና የስራ ነጻነት ባይኖራቸውም፡ በአለም አቀፍ ውድድሮች ግን ምን ያክል ብቁ መሆናቸውን አሳይተውናል፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ በተናጥል እና በተጨማሪም ከመንግስት ጋር በመነጋገር ደማቅ የእውቅና ፕሮግራም ያዘጋጅላቸዋል›› ብለዋል፡፡

ዛሬ ከሰአት በኋላ በጁፒትር ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግላጫ ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሞያዎቹም በየውድድሮቹ ስለነበራቸው ስኬታማ የሚባል ቆይታ እና ለሀገራቸው ጠቃሚ የሚባሉ ልምዶችን በመቅሰም ስለመመለሳቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአፍሪካ ዋንጫው ቱኒዚያ እና ሴኔጋል ያደረጉትን የግማሽ ፍጻሜ መርሃግብርን ጨምሮ አራት ጨዋታዎችን የመራው ኢንትርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ‹‹ እዚህ ደረጃ እንድንደርስ ላገዙኝ በሙሉ ምስጋናየን ማቅረብ እወዳለሁ፡ በውድድሩ እጅግ ደስተኛ የሆንኩበትን ቆይታ አሳልፌ መጠቻለሁ ፤ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ደግሞ ከዚህ የበለጠ ርቀት ለመጓዝ ጠንክሬ እንደምሰራ ቃል እገባላችኋለሁ›› ሲል፡ በፈረንሳዩ የሴቶች የአለም ዋንጫ አፍሪካን ከወከሉ ሶስት ዳኞች መካከል አንዷ በመሆን ወደ ውድድሩ ያመራቸው ሊዲያ ታፈሰ በበኩሏ ‹‹ለእኔ ብቻ ሳይሆን ከኔ በኋላ ለሚመጡት ባለሞያዎች ሁሉ የማካፍለው ጥሩ ልምድ ይዤበት የተመለስኩበት ውድድር ነበር›› ስትል አስተያየቷን አካፍላለች፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በረዳት ዳኝነት የተሳተፈው ተመስገን ሳሙኤል በበኩሉ እጅግ ብዙ ጠቃሚ ትምሀርት ያገኘበት ቆይታ እንደነበር ገልጿል፡፡ ተመስገን በአፍሪካ ዋንጫው ቱኒዚያ ከ አንጎላ ባደረጉት ጨዋታ ላይ በረዳት ዳኝነት ተሳትፎ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የካፍ የቴክኒክ የጥናት ቡድን አባል በመሆን ወደስፍራው ያቀኑት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በበኩላቸው ‹‹ የአፍሪካን ብሎም የአለም እግር ኳስ አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃ የት እነደሆነ የተመለከትኩበት፣ ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት ጠቃሚ የሚባሉ ተሞክሮወችን የቀሰምኩበት ቆይታን ያደረግኩ ሲሆን፡ ወደፊት ሊሳኩ የሚችሉ የብሄራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ እድሎችንም አመቻችቼ ተመልሻለሁ›› ብለዋል፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *