2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በውድድር አመቱ ማከናወን ከሚገባው 240 ጨዋታዎች 239ኙን አከናውኖ (ቅ/ጊዮርጊስ ከ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እስካሁን መቼ እንደሚከናወን አልታወቀም) መቀሌ ከነማን አዲሱ የሊጉ ሻምፒዮን አድርጎ፡ ደደቢት፣ መከላከያን እና ደቡብ ፖሊሰን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሸኝቶ በምትካቸው ደግሞ ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከነማ እና ሀዲያ ሆሳእናን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሳይጠናቀቅ ተጠናቋል፡፡

የዘንድሮው የውድድር ዘመን ደጋግመው በተከሰቱ አሳፋሪ የሜዳ ውጭ እና ሜዳ ላይ ሁነቶች፣ በተለይም ደግሞ  ወደ ማጠናቀቂያው ሰሞን አካባቢ በአወዳዳሪው አካል እና ተወዳዳሪ ክለቦች መካከል በተፈጠሩት እግር ኳሳዊ ብቻ  የማይመስሉ አላስፈላጊ ክስተቶች እና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች  በበጎ እንዳናስታውሰው አድርጎን ያለፈ ነበር፡፡

እግር ኳሳችን በቀጥተኛ ባለድርሻ አካላቱ ሁለንተናዊ  የስፖርታዊ ስብእና መጓዳል እና  በግልጽ የሚታይ የአቅም እና ቅንነት ማነስ የተነሳ እንደ ፖለቲካ እና ብሄርተኝነት ባሉ ሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች እጅ ጠምዛዥነት ከመዝናኛነቱ ይልቅ የስጋት ምንጭነቱ የጎላበት እንዲሁም ስፖርቱን ለሚወዱ ሁሉ በአብዛኛው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ያለፈበት አመት ነበር፡፡


ለመሆኑ የውድድር አመቱ ምንምን ነገሮችን አስመለከተን?

ሀ. የእግር ኳሱን አመራር “አልባ” መሆን

የአንድን ዘርፍ/ተቋም ውድቀትም ሆነ ውጤታማነት በዋናነት ከሚወስኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የተቋማዊ አመራር የብቃት ሁኔታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመለከትናቸው ለሚገኙ ችግሮች፡ ሃላፊነቱን  ሙሉበሙሉ ለፌዴሬሽኑ አመራሮች መስጠት ፍትሀዊ አያስብልም፤ ነገር ግን በግልጽ በሚታይ መልኩ ከአንድ ግዙፍ ሀገራዊ ተቋም አመራር የማይጠበቁ ተራ ግን እግር ኳሱን ውድ ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶችን የፌዴሬሽኑ አመራሮች ደጋግመው ሲሰሩ ተመልክተናል፡፡

በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅቶች የእግር ኳስ አመራሩ ህግን እና አሰራራርን በትክክል መተግበር ብቻ ሳይሆን የተፈጠሩ ውዝግቦችን በንግግር እና ውይይት  የመፍታት የዲፕሎማሲ  አቅሙ ምን ያክል ደካማ እና እግር ኳሱን የማይመጥን መሆኑ በአደባባይ የተገለጠበት አመት ነበር፡፡

ለ. የደህንነት ስጋት መሆኑን

እግር ኳሳችንን አሁን ሀገራችን በፖለቲካው መስክ ያጋጠማትን አለመረጋጋት ለማከም እንደመፍትሄነት ከመጠቀም ይልቅ፤ ይልቁንም ለሌሎች ማህበረሰባዊ ችግሮቻችን እንደ አቀጣጣይ ቤንዚንነት ስንጠቀምበት የከረምንበት እና ስፖርቱ ለሀገራችን ተጨማሪ የጸጥታ መደፍረስ ስጋት ምንጪ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው፡፡

ምንም እንኳን የዘንድሮውን ውድድር በአማራ እና ትግራይ ክልል ክለቦች መካከል የነበረውን ቅራኔ በመፍታት የሁለቱም ክልል ቡድኖች በገለልተኛ ሜዳ ከመጫወት ወጥተው በሜዳቸው እንዲጫወቱ በማድረግ ቢጀመርም፣ ከችግሩ ጥልቅነት አንጻር ሙሉ በሙሉ ሊቀረፍ አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ በዘንደሮው ውዝግብ ብቻ ሳይወሰኑ ወደቀጣይ አመትም የተሸጋገሩ፡ በመቀሌ እና ወልዋሎ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር፣ በኢትዮጵያ ቡና እና በመቀሌ ከነማ፣ በፋሲል ከነማ እና በመቀሌ ከነማ እንዲሁም በሲዳማ እና ወላይታ ድቻ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስታወስ ይቻላል፡፡

ሐ. ብሄርተኝነት እና ኳሱ ያለልክ መወዳጀታቸውን

ሁለቱ ነገሮች በወቅታዊው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ፡ ከምንም በላይ ደግሞ በአወዳዳሪው አካል ቸልተኝነት የተነሳ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለመያየት እስኪቸግሩን ድረስ ተዋህደዋል፡፡

አንደኛው እና ምናልባትም ቀላሉ ጊዜያዊ መፍትሄው ደግሞ ፌዴሬሽኑ የክለብ ፈቃድ በሚሰጠበት ወቅት የብሄር ማንነትን ይዘው የሚመጡ ክለቦችን አለመመዝገብ እና ያሉትንም እንዲስተካክሉ ማድረግ ነው፡፡

የሁለቱ አካላት መዋሀድ የሜዳ ላይ እግር ኳስ ፉክክሩን የብሄር ከ ብሄር ፉክክር በማስመሰል በተወዳዳሪዎች መካከል አላስፈላጊ ጡዘት በመፍጠር የሚመዘገቡ ውጤቶችን አሜን ብለው ለመቀበል እንዲቸገሩ እያደረገ ሲሆን በአንዳንድ የአካባቢ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ እግር ኳሳዊ ፉክክሮችን ሙሉ በሙሉ አጥፍቷቸዋል (በአንድ አካባቢ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች ውጤቶች የበለጠ ለሚያስፈልገው እንደሚሰጡ ቀድሞ የሚተነበይ እስከመሆን ደርሷል::)

መ. ፈታኝ የፋይናነስ ቀውስ የስፖርቱ በር ላይ መቆሙን

በዚህ አመት እግር ኳሳችን ያጋጠመው ትልቁ ፈተና ከተጫዋቾች የክፍያ ዋጋ መናር ጋር ተከትሎ እና ስፖርቱ ገንዘብ አውጭ እንጂ አስገቢ ባለመሆኑ ያጋጠመው የፋይናንስ ፈተና ነው፡፡

የደደቢት ክለብ ሁኔታ በይፋ ስለወጣ ነው እንጂ የሌሎች ክለቦች ሁኔታም ከዚህ በብዙ የተለዬ አይደለም፤ ለአብነትም በርካታ ክለቦች ለወራት ለተጫዋቾቻቸው ደሞዝ መክፈል አቅቷቸው ሲቸገሩ ተመልክተናል፡፡

በተለይም ደግሞ የአልኮል መጠጥ አምራቾች ከስፖርቱ አካባቢ ዘወር እንዲሉ የሚያደርገው አዋጅ ስራ ላይ መዋልም ፈተናውን የበለጠ እንደሚያከብደው ይጠበቃል፡

ሠ. የእግር ኳሱ የልማት ስራ ጉዳይ ችላ መባሉን

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ዘንድሮም በከዚህ ቀደሙ አኳኋን መጓዝ መቀጠሉ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አብዝቶ በመጠመዱ ምክንያት ትልቁን ጉዳያችን ዘንግተነዋል፡፡ የታዳጊዎች፣ የዳኞች፣ የአሰልጣኞች እና የልዩልዩ ባለሞያዎች ልማት እና የማብቃት ስራዎች የተዘነጉበት አመት ነበር፡፡

ዘንድሮስ ከሊጋችን ምን ተማርን?

ዘንድሮ ከሊጉ አትርፈናል ብዬ የማስበው አንድ ነገር ቢኖር የችግሮቻችን ጽዋ ሞልቶ በመፍሰሱ ምክንያት በትልልቅ እግር ኳሳዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ በፍጥነት ለመፍትሄ እንድንነጋገር አድርጎናል፡፡

ከዚህ ቀደም ረገጥ አድርገን ያልተወያየንባቸውን እንደ መሰረታዊ የአወቃቀር፣ የስርዓት፣ የሊግ ፎርማት እና የፋይናነስ አወጣጥ አይነት ታላላቅ ጉዳዮቻችን ላይ መነጋገር እና በፍጥነት መፍትሄ ማምጣት  እንዳለብን እንድንነጋገር በር ከፍቶልን ያለፈ ዓመትም ይመስለኛል፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *