አዲስ አበባ – ሰኔ 25/2011 ዓ.ም

ክለቡ ዛሬ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አወዳዳሪው አካል ያለበቂ መረጃ እና አሳማኝ ምክንያት የ28ኛው ሳምንት የሊጉ  መርሀግብር የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦች ጨዋታ ለብቻው ተነጥሎ መቼ እና የት እንደሚካሄድ ሳይገለጽ በደፈናው “በጸጥታ ስጋት ምክንያት” ውድድሩ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል መባሉን፡ የክለቡን የዋንጫ ተፎካካሪነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ነው ሲል ገልጾታል፡፡

የክለቡ የቦርድ ዋና ጸሀፊ አቶ ንዋይ በየነ በጋዜጣዊ መግለጫው  ላይ ” ክለባችን እንደ አንጋፋነቱ በርካታ ችግሮች ባሉበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የችግሩ ሳይሆን የመፍትሔዎቹ አካል ለመሆን ሲል ብቻ፡ ከዚህ ቀደም በርካታ እና ሆነ ብለው የክለባችንን ውጤት የሚጎዱ ውሳኔዎች ሲወሰኑ በትዕግስት ማለፋችን ዛሬ ለተወሰነብን ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ ዳርጎናል ብለን እንድናስብ አሰገድዶናል” ብለዋል፡፡

የክለቡ ሀላፊዎች ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፡ ክለባቸው በሂሳብ ስሌት መሰረት ሻምፒዮን የመሆን እድል እያለው ፌዴሬሽኑ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ላይ መድረሱ ” ስፖርቱን የሚመራው አካል ያለውን እግር ኳሳዊ እውቀት እንድንጠራጠር እና ውሳኔውም ቅንነት የጎደለው መሆኑን እንድናምን አድርጎናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ክለቡ በነገው እለት ጎንደር ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር የ29ኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታ ቢኖርበትም እስካሁን ድረስ ወደ ስፍራው አለማቅናቱ ታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ አጣብቂኝ ውስጥ መግባት

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት እንደነበር እና ፌዴሬሺኑ በወቅቱ ይዞት የነበረው አቋም ብዙ ርቀት ሊያስኬደው ባለመቻሉ ከብዙ አላስፈላጊ ውዝግብ በኀላ እልባት ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

ከስህተቱ የተማረ የማይመስለው ፌዴሬሽኑ ከውሳኔ አስቀድሞ ነገሮችን በሚገባ ባለማጤኑ ምክንያት ዛሬም ከዚህ ቀደም ከነበረበት የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ ራሱን አስገብቷል፡፡

በአንድ በኩል ለቻምፒዮንነት የሚፎካከሩ ቡድኖች ጨዋታዎቹ በተያዘላቸው መርሃግብር መሰረት እንዲካሄዱ አጥብቀው እየጠየቁ ሲሆን በሌላ በኩል ሰኔ 30 የበጀት መዝጊያ ወቅት ስለሆነ ውድድሩ በዚያው ቀን እንዲያልቅ የሚጠይቁም በርካቶች ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በበኩሉ በቀጣይ አመት ኢትዮጵያን በአህጉራዊው የክለቦች ውድድር ላይ የሚወክሉትን ክለቦች ከአምስት ቀናት በሗላ አሳውቁኝ ሲል ለፌዴሬሽኑ ቀጭን መመሪያ አስተላልፏል፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *