አዲስ አበባ –  ሰኔ 07/2011 ዓ.ም

ዛሬ በጎልደን ቱሊፕ አዲስ አበባ በተከናወነው የልዩ ስፖርት ድረ-ገፅ ይፋዊ የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረገው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ የድረ-ገፁ ስራ መጀመር የስፖርት ሚድያው ለአትሌቶች እና ለአትሌቲክሱ ዕድገት እና ተቀባይነት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በይበልጥ ያጠናክረዋል ብሏል፡፡

ሻለቃ ኃይሌ በዕለቱ ፕሮግራም ላይ፡ ወቅታዊው የአትዮጵያ እግርኳስ ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልፆ  የእግር ኳስ ፌዴሬሽን  አመራሮች እግር ኳሱን  በትክክል  መምራት ካልቻሉ  እርሱ በአትሌቲክስ ፌደሬሽን   እንደወሰነው  ሁሉ  ራሳቸውን ከሃላፊነት እንዲያነሱ ሀሳብ አቅርቧል::

ኃይሌ የአትሌቲክስ  ፌዴሬሽን  ፕሬዚደንት  ሆኖ  በተመረጠ በ12 ወራት ውስጥ ”  ከአቅም  በላይ  በሆነ  ምክንያት” በሚል ራሱን ከኃላፊነት ማንሳቱ ይታወሳል::

በድረ-ገፁ ምርቃት ወቅት በነበረው ውይይት ላይ ሀሳባቸውን የሰነዘሩት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ኢንስ. አብርሐም መብራቱ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከውድድር እና ውጤቶች ባለፈ ጥልቅ ሙያዊ ግምገማዎች እየተደረጉ አይደለም ፤ በአሰልጣኞች መካከልም ተቀራርቦ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ቀና መንፈስ አይስተዋልም ብለዋል፡፡

አሰልጣኙ ድረ-ገፁ “በኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች መካከል የዕውቀት ልውውጥ እንዲኖር ፣ ሐሳብን የመግለፅ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንዲሁም የሚሰሩ ጥናቶች እና ምርምሮች ለአንባቢያን እንዲበቁ ያስችላል” ብለዋል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ አየለ በበኩላቸው ድርጅታቸው ያለፈባቸውን ፈተናዎች እና የደረሰበትን ስኬት በማውሳት ሌሎች መሰል ድርጅቶች ከታላቁ ሩጫ ቢወስዷቸው ያሏቸውን የስኬት ምስጢሮችንም አካፍለዋል፡፡

የሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገፅ መስራች እና ኤዲተር ጋዜጠኛ አብርሐም ገ/ማርያም በበኩሉ በኢትዮጵያ የድረ-ገፅ ሚድያ ላይ መስራት ያለውን ፈታኝነት ገልፆ አዲስ ጀማሪው ‹ልዩ ስፖርት›  በአዲስ ይዘት እና አቀራረብ ተጨማሪ አማራጭ ሆኖ መምጣቱ እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በርካታ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፡ ለስፖርቱ እድገት ጠቃሚ የሚሏቸውን ሀሳቦች ለማካፈል ፍላጎታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *