የግል ምልከታ | በኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም


አዲስ አበባ – ሰኔ 04/2011 ዓ.ም – በሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ተከታታዮች ባለቤት የሆነው የእግር ኳስ ስፖርት፡ ከዚህ ቀደም በጉልህ ሲነሳበት ከነበረው የውጤታማነት ችግር ባለፈ፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰባሰቢያችን መሆን ሲገባው መለያያችን፡ የደስታ ምንጫችን እንዲሆን ሲገባው የሀዘናችን ውቅያኖስ እየሆነ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡

ወቅታዊው የእግር ኳሳችን አካሔድም በጊዜ ፈር እንዲይዝ ካልተደረገ በስተቀር ከፊት ለፊታችን ሊያደርስ የሚችለው ከስፖርቱ ያለፈ ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ከበቂ በላይ የሆኑ ጠቋሚ ምልክቶችን ከእለት እለት እያስመለከተን ይገኛል፡፡

ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት የሚቀመጠው ደግሞ ዘመናትን ተሻግረው እየተንከባለሉ የመጡ እና በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች ያሉበት የሀገራችን የእግር ኳስ ስፖርት፡ የነበሩበትን ዘርፈ ብዙ የስርዓት፣ የአቅም ግንባታ እና የውጤታማነት ችግሮች መፍትሔ ሰጥቶ ሳይጨርስ፡ ስፖርቱን ከእግር ኳስ መርህ ጋር ፈጽሞ ከማይገናኙ እንደ ብሄርተኝነት እና ፖሊቲካ ካሉ ጉዳዮች ጋር ያለቅጥ ማወዳጀታችን ነው፡፡

የእግር ኳስ ሜዳወቻችን ሰላም እና አዝናኝነት የራቃቸው መሆን የተለመደ ክስተት እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ወቅት: ከመሰረታዊ የህግ ክፍተት እና የውይይት ማነስ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት የሀገሪቱ ትልቁ ሊግ የሆነው፡ የክለቦች ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጥም የችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስን ይጠቁመናል፡፡

እኔም በተከታይነት እግር ኳሳችን አሁን ካለበት ዘርፈ ብዙ የችግር ትብታብ እንዲላቀቅ በአጭር እና ረጀም ጊዜያት የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መከወን አለባቸው ብዬ የማስባቸውን ጉዳዮች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

በፍጥነት ሊከወኑ የሚገባቸው ጉዳዮች

በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሀ-ግብር በኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ ሰባ እንደርታ እግር ኳስ ክለቦች መካከል በተፈጠረው ችግር እና ይህንን ጉዳይ ለመፍታት የተሄደበት አቅጣጫ የፈጠረው ተጨማሪ አለመግባባት ሌላ መልክ ይዞ ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት እና ህልውና ተጨማሪ እክል እንዳይሆንብን ህግ እና ስርአትን እንዲሁም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተጨማሪ ውይይትን በማድረግ እና የመፍትሄው አካል በማድረግም ጭምር ለጉዳዩ በጊዜ እልባት በመስጠት ውድድሮቹን ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ ቀጥሎ የውድድር አመቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ፡ ልዩ ክትትል በሚስያስፈልጋቸው ለሻምፒዮንነት እና ላለመውረድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እና የካበቢውን ሰላማዊ ሁኔታ ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድረሻ አካላት የሀላፊነት ክፍፍል በማድረግ እንዲሁም ከፌዴራል እና የክልል የጸጥታ እና ደህንነት አካላት ጋር በመተባበር መስራት ያስፈልጋል፡፡

በዘላቂነት ሊከወኑ የሚገባቸው ጉዳዮች

የእግር ኳሳችን ብቸኛው ዘላቂ መዳኛ እውነተኛ ሙያዊ አሰራርን ተግባር ላይ ማዋል ነው፡፡ የእግር ኳስ ስፖርትን፡ በእግር ኳስነቱ ብቻ የሚያውቁ፣ የሚረዱ እና የሚተገብሩ ተጫዋቾችን፣ አሰልጣኞችን፣ አመራሮችን፣ ደጋፊዎችን እና የሚዲያ ባለሞያዎችን ማፍራት ፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አቅዶ እና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡

እግር ኳሳችንን በተለይም ፌዴሬሽኑን ውድድር ተኮር ብቻ አለማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ሁኔታ ነው፡፡ ጠንካራ እና ተዓማኒ ስርዓት መፍጠር ፣ የሰብዓዊ ልማት እና ስራን ለባለሞያዎቹ መስጠት ትልቅ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ፡ ብሎም ለተግባራዊነቱ መረባረብ ከሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በተለይም ከአመራሩ ይጠበቃል፡፡

እግር ኳሳችን በሁሉም መልኩ፡ ማለትም በመዝናኛነት፣ በስራ እና በአዎንታዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ እናንዲሁም በውጤታማነት ረገድ ቀጣይነት ባለው የእድገት ሀዲድ ላይ እንዲጓዝ ከተፈለገ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት እና ሀላፊነትን ተከፋፍሎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም ይህንን እንቅስቃሴ ለማስጀመር ይረዳ ዘንድ ቀጥሎ በምዘረዝራቸው አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጉ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትን መስመር ማስያዝ

እንደ ኢትዮጵያ ባለ፡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ብዙም ባልዳበረበት እና መንግስት የፖሊቲካውንም የኢኮኖሚውንም የበላይነት ይዞ በሚገኝበት ሀገር ውስጥ፡ ብዙ ነገሮች ከመንግስት መጠበቅ የተለመደ ሂደት ነው፡፡ እግር ኳሳችንም ቢሆን ለእድገቱ እና ለደህንነቱ ሲል የመንግሰትን ድጋፍ በእጅጉ መሻቱ የሚያከራክረን ጉዳይ አይደለም፡፡

ነገር ግን የመንግስትን ሚና፡ የሚያወጣውን በጀት ትክክለኛ መዳረሻ እንዲያውቅ፣ ህጋዊ አሰራሮች በትክክል እየተተገበሩ እንደሆነ እንዲከታተል እና በመሳሰሉት የእግር ኳሱን እውነተኛ ትርጉም መስመር በማያስቱ እንቅስቃሴዎች ብቻ እንዲገደብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በጥቅሉ በእግር ኳሱ ላይ የመንግስት ሚና የአጋዥነት ብቻ እንዲሆን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ  ነው፡፡

በዋናዋና ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ

የእግር ኳሳችን ባለድርሻ አካላት በዚህ ክረምት ወቅት ለሚቀጥሉት አመታት ለስፖርቱ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ በሚያሳርፉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ ጊዜ ሊሰጡት የማይገባ ጉደይ እንደሆነም ይሰማኛል፡፡ ስለሆነም፡-

1. አሁን ላይ እየተነሳ በሚገኘው የሊግ ፎርማት ሁኔታ ላይ አዋጭው መንገድ የትኛው ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የብዙሀኑን ሀሳብ አክብሮ ለተፈጻሚነቱ በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡

2. የፕሮፌሽናል ሊግ ምስረታ ላይ መነጋገርም እንዲሁ  ያስፈልጋል፡፡ ፌዴሽኑም ከአመት አመት በብዙ መንገድ እድገት በማያሳየው እግር ኳሳችን እና ውድድሮች ላይ ጊዜውን ከሚያጠፋ ሙሉ በሙሉ ወደ ዘላቂ የልማት ስራዎች ትኩረቱን እንዲያዞር፡ ክለቦችም ሁልጊዜ ውድድርን ከተመለከተ የማያባራ ንትርክ ነጻ እንዲወጡ ለማስቻል ይረዳቸው ዘንድ፣

በመጀመሪያ – በጊዜያዊነት ፌዴሬሽኑን ሙሉ በሙሉ ከውድድር ማስወጣት ወይንም ሀላፊነቱን ከበላይ ጠባቂነት እንዳይዘል በማድረግ ሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል ድምጽ ኖሯቸው እና ብዙሀኑ የደገፈው እየተተገበረ የሚሄድበት አዲስ ምክር ቤት ማቋቋም፤ በመቀጠል ደግሞ ውድድሩን የሚመራ ራሱን የቻለ በባለሞያዎች የተደራጀ አዲስ አካል በመፍጠር፤ ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ውድድሮቹን ራሳቸው ክለቦቹ በባለቤትነት ይዘው እንዲመሩ ማድረግ በዘላቂነት ደግሞ የፕሮፌሽናል ሊግን ስለመመስረት መወያዬት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

3. ለክለቦች እና እግር ኳሱ ቀጣይነት ስጋት እንደሆነ እየተነገረ የሚገኘው እና እምብዛም ቁጥጥር የማይደረግበት የገንዘብ አጠቃቀም ፍትሀዊነትን ( Financial Fair Play) በተመለከተም ሰፊ ውይይት ያስፈልጋል፡፡

ጠንካራ ተቋም መገንባት

እንዳለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገራችን ስፖርት ጠንካራ ተቋማት የሉትም፤ ምናልባትም የብዙዎች የትኩረት ማእከል የሆነው እግር ኳሳችን ይህንን ልማድ ሰብሮ በመውጣት እና ጠንካራ እና ዘመናዊ ተቋም በመገንባት ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችልበት መልካም እድልም አለው፡፡

ፌዴሬሽኑ ተዓማኒ፣ በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት እና በብቁ የሰው ሀይል የተደራጀ ተቋም እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ደግሞ፡- የፌዴሬሽኑ የበላይ አካል የሆነውን የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አይነት፣ ስብጥር እና ብዛት በህግ ወስኖ ማስቀመጥ፤ መተዳደሪያ ደንቡን አሰሪ እና ግልጽ እንዲሆን የማሻሻያ ስራዎችን መስራት እንዲሁም ፌዴሬሽኑን የሚመሩት ስራ አስፈጻሚዎችን የምርጫ አካሄድ በማያሻማ መልኩ ማስቀመጥ በአጽንኦት ሊተገበር የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

የክለብ ፈቃድ አሰጣጥን መፈተሽ

ክለቦች የእግር ኳሱ የጀርባ አጥንት እንደመሆናቸው መጠን እነርሱን ማጠናከር በተዘዋዋሪ እግር ኳሱን ማሳደግ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በመሆኑም እያንዳንዱ ክለብ በፊፋ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የክለብነት መስፈርት እንዲያሟላ፡ ማለትም፡- ህጋዊ ሰውነት፣ ጠንካራ እና የታወቅ የገቢ ምንጭ፣ የስፖርት መሰረተ ልማት፣ የተደራጀ የሰው ኃይል እና በሚገባ የተደራጁ እና ተመጋጋቢ የሆኑ የስፖርት ቡድኖች እንዲኖሩት፤ ፌዴሬሽኑ መከታተል፣ ማገዝ እና መቆጣጠር ያስፈልገዋል፡፡ ለተግባራዊነቱም በጊዜ ሂደት ተከፋፍለው የሚፈጸሙ የቤት ስራዎችን መስጠት ይኖርበታል፡፡

ተዓማኒ የፍትህ ስርዓት ማስፈን

ብዙውን ጊዜ በሀገራችን የእግር ኳስ ስፖርት ላይ የምንመለከተውን አለመግባባት የሚፈጥረው የፍትህ ስርዓቱ ተቀባይነት ማጣት እና የፍትህ ሚዛን መዛነፍ ነው፡፡

ስለሆነም ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና በፌዴሬሽኑ አባላት ዘንድ እምነት ለማግኝት፡ በመጀመሪያ ፌዴሬሽኑ የሚገለገልባቸውን የስነስርአት መመሪያዎች ብቁነት ማረጋገጥ፤ በመቀጠል ደግሞ በፍትህ ሂደቱ ላይ ጣልቃ አለመግባት፣ ብቁ እና ገለልተኛ የህግ አካላትን ማቋቋም፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ህግን ብቻ መሰረት ያደረጉ፣ ተፈጻሚ እና ሁሉንም በእኩልነት የሚያገለግሉ እንዲሆኑ በማድረግ ተዓማኒ የፍትህ ስርዓት መዘርጋት እና በዚህ ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስቀረት ሌላኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በመጨረሻም እነዚህን እና የሌሎች ባለሞያዎችን ተጨማሪ ጠቃሚ የመፍትሔ ሃሳቦች በማድመጥ እና የአስፈላጊነት ቅደም ተከተል በማዘጋጀት ለተፈጻሚነቱ መስራት፡ ተወዳጅ የሆነውን የእግር ኳስ ስፖርታችንን  አሁን ከሚገኝበት ችግር ለማላቀቅ እና ወደሚፈለግበት የእድገት ደረጃ ለማድረስ የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ጉልህ  እንደሚሆን እተማመናለሁ፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *