የግል አስተያየት | በኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም


አዲስ አበባ – ግንቦት 27/2011 ዓ.ም – እጅግ አጨቃጫቂ እና አሰልቺ ከነበረው እና ሰባት ወራትን ከፈጀው ያለፈው አመት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትነት እና ስራ አስፈጻሚ አባልነት የምርጫ ሂደት በኀላ፡ አፋር ሰመራ ላይ ግንቦት 26/2010 ዓ.ም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ኢሳያስ ጂራ በሚፋጀው ወንበር ላይ በሀላፊነት ከተቀመጡ ድፍን አንድ አመት ሞላቸው፡፡

እኔም በዚህ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ፕሬዝዳንቱ ምን ምን ነገሮች ላይ ተሳክቶላቸዋል፡ የትኞቹ ላይስ አልተሳካላቸውም ፡ በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ የግል ምልከታዬን ቀጥሎ ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡

ስኬቶች

ቀጥሎ ለመዘርዘር በምሞክራቸው ጉዳዮች ላይ በእርሳቸው የፕሬዝዳንትነት ዘመን በግላቸውም ሆነ በቡድን ጥረት እንዲሁም በሌሎች መልካም ፈቃድ ባለፈው አንድ አመትጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የተፈጠሩ መልካም ነገሮችን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

ጥናት

የአቶ ኢሳያስ ጅራ የመጀመሪያው የሚደነቅ ተግባር፡ የፌዴረሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙ ማግስት በግብታዊነት እና ያለ በቂ ጥናት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ፡ ሳይንሳዊ የሆነና ምንአልባትም በርሳቸው የሀላፊነት ዘመን ብቻ ሊተገበር የማይችል የሁሉንም የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላት ሀሳብ በግብዓትነት የተጠቀመ፡ አጠቃላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ነባራዊ ሁኔታ የሚዳስስ እና የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦችን ያስቀመጠ፡ አራት ወራትን የፈጀ በስፖርቱ ባለሙያዎች በገለልተኝነት የተዘጋጀ ጥናት ማስጠናታቸው ነው፡፡

የካፍ የልህቀት ማዕከልን መረከባቸው

እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለ በብዙ መንገድ ከብዙዎቹ በብዙ ወደኀላ ለቀረ ኢንደስትሪ ራሱን ለማሻሻል እንደዚህ አይነት የልህቀት ማዕከላት ባለቤት መሆን ጥቅሙ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡

እግር ኳሳችን በመሠረተዊነት ለመቀየር ማዕከሉን የበቁ አሰልጣኞች፡ ዳኞች፡ አስተዳዳሪዎች እና ሌሎችንም ባለሞያዎች ለማፍራት ያስችላል እና ነው፡፡

የፊፋ ቢሮ በአዲስ አበባ መከፈት

ፊፋ የሰሜን፡ መካከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉራዊ የእግር ኳስ ልማት ማስተባበሪያ ቢሮውን በአዲስ አበባ የከፈተው በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ ነበር፡፡

የዚህ ቢሮ በሀገራችን መከፈት፡ እግር ኳሳችን ለማሳደግ በምናደርገው እንቅስቃሴ የፊፋን የቴክኒክ እገዛ በቅርብ እንድናገኝ በማድረግ በኩል የሚኖረው አስተዋጽኦ ጉልህ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ፌዴሬሽኑ የራሱን አዲስ ህንጻ መግዛቱ

ፌዴሬሽኑ ከፊፋ የልማት በጀት በተደረገለት ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ፡ ወሎ ሰፈር አካባቢ ለቢሮ እና ለንግድ ስራ አገለግሎት መስጠት የሚችል አዲስ ህንጻ ገዝቷል፡፡

የህንጻው ደህንነት፡ የአርክቴክቸር ውበት፡ የኢንቨስትመንቱ ተገቢነት/አዋጭነት እና የተገዛበት የ93 ሚሊዮን ብር ዋጋ ተገቢነት ራሳቸውን የቻሉ መልሶች የሚፈልጉ ቢሆንም፡ ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ አንድ ተጨማሪ ንብረት ማፍራቱ ግን እንደ ስኬት ሊታይ ይችላል፡፡

የሔይንከንን የስፖንሰርሺፕ ኮንትራት ማራዘም መቻሉ

በሀገራችን የጸደቀው አዲሱ የምግብ እና መድሀኒት አስተዳደር አዋጅ የአልኮል መጠጦችን በብሮድካስት ሚዲያ፡ በስፖርት ማዘውተሪያ እና ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ማስተዋወቅን በከለከለበት ወቅት ፌዴሬሽኑ በአመት 14 ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ የአራት አመት ኮንትራትን ከሔይንከን ቢራ ጋር መፈራረሙ ተቋሙን ውጤታማ ብቻ ሳይሆን አስገራሚም ያደርገዋል፡፡

በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ከጣሊያኑ ኢሪያ ወደ እንግሊዙ ኧምብሮ የብሔራዊ ቡድን ትጥቅ አቅራቢዎች ያደረገው ሽግግር ዋጋ የተከፈለበት ቢሆንም ስምምነቱ ከሚያስገኘው የረጅም ጊዜ ጥቅም ሲባል መከወን የነበረበት ሌላኛው ውጤታማ ስራ ነበር፡፡

ከእነ ዘርፈ ብዙ ችግሮቹም ቢሆን ሁሉንም ውድድሮች ማካሄድ መቻሉ

ሀገራችን አሁን ካለችበት መንገራገጭ እና የብሔርተኝነት ትኩሳት እንዲሁም ከጸጥታ መድፍረስ አንጻር፡ እግር ኳሱ ከእነ ዐርፈ ብዙ ችግሮቹም ቢሆን በህይወት እንዲኖር፡ ውድድሮቹም እንዲቀጥሉ መደረጋቸው በራሱ ባያኩራራም እንኳን ቀላል ግምት የሚሰጠው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡

ውድቀቶች

ምንም እንኳን አቶ ኢሳያሳ ወደ ሀላፊነት መንበሩ ከመጡ ገና አንድ አመታቸው ቢሆንም እና ይሄንን፡ ይሄንን አልሰሩም ብሎ ብይን ለመስጠት አስቸጋሪ ቢሆንም፡ ባለፉት 12 ወራት እርሳቸው በሚመሩት ፌዴሬሽን ውስጥ የታዘብኳቸውን ውጤታማ ያልሆኑ ሁነቶችን እንደሚከተለው ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

ከቻን 2020 አስናጋጅነት መሰረዝ

እንደኔ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ አቶ ኢሳያስን ጨምሮ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት አካለት በሙሉ ከመመረጣቸው አስቀድሞ ሊሰሯቸው ያሰቧቸውን እቅዶች፡ የቻን 2020ን ጉዳይን ጨምሮ አሰቀድመው አቅርበው ቢሆን ኖሮ በእጅጉ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተጠያቂነትን ለማስፈን ይረዳ ስለነበር ነው፡፡

የቻን 2020 ውድድርን ኢትዮጵያ ማዘጋጀት ባለመቻሏ ባጣቻቸው ጉዳዮች ዙሪያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በጻፍኩት ሌላ ጽሁፍ በዝርዝር አሰቀምጨዋለሁ፡

አቶ ኢሳያስ ከላይ በስኬታማነት ከገልጽኳቸው ክንውኖች መካከል፡ በካፍ ቀጥተኛ ውሳኔ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደተላለፈው የልህቀት ማዕከል ፡ በአቶ ጁኔዲ ባሻ የፕሬዝዳንት ዘመን ሂደታቸው ተጀምሮ በእርሳቸው አመራርነት ተግባራዊ በሆኑት የአዲስ ህንጻ ግዥ እና የፊፋ ቢሮ በአዲስ አበባ መከፈት ፕሮጀክቶች ላይ ሙሉ በሙሉ ሙገሳውን እርሳቸው ብቻ እንደማይወስዱት ሁሉ፡ የዚህ ውድድር መሰረዝ ላይም ምን አልባትም ከመጨረሻ ሰዓት መሯሯጥ ቀደም ብለው ጉዳዩን መስመር ለማስያዝ በሚገባቸው ልክ አለመንቀሳቀሳቸው ቢያስተቻቸውም፡ ይህ ውሳኔ ከእርሳቸው አቅም በላይ በመሆኑ ተጠያቂነቱን ለእርሳቸው ብቻ መስጠት ፍትሐዊ አያስብልም፡፡

ነገር ግን ይህም የተፈጠረው በእርሳቸው ዘመን ነው፡፡

የአፈጻጸም ደካማነት

የፌዴሬሽኑ ልዩ መገለጫ እስኪመስል ድረስ መቀረፍ ያልተቻለ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ የተለያዩ ህጎች፡ ደንቦች እና መመሪያወች አለመከበር፡ የፌዴሬሽኑ ውሳኔዎች ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወቅታዊነት፡ ቀጥተኝነት እና ርትዕ የጎደላቸው መሆን፡ ዛሬም ቢሆን በአቶ ኢሳያስ አመራር ፌዴሬሽኑ የጎደፈውን ስሙን ማደስ ያልቻለ እና በሁሉም ዘንድ ተዓማኒነትን ያጣ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

ለአብነት ያክልም፡ ፌዴሬሽኑ ራሱ ያስጠናውን የተቋማዊ ለውጥ ጥናት ወደ ተግባር የቀየረው በጣም ጥቂቱን ብቻ መሆኑ፣ የካፍ የልህቀት ማዕከልን ወደ ስራ ለማስገባት ያደረገው ጥረት ውስን መሆኑ፣ ከአዲሱ የተቋሙ ህንጻ ግዥ እና ከኢሪያ ወደ ኧምብሮ የብሔራዊ ቡድን ትጥቅ አቅራቢዎች ያደረገው ሽግግር  ግልጽነት የጎደለው መሆኑን እና በወቅቱ ለተነሱት ክሶች የተሰጡት ምላሾች አጥጋቢ አለመሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የእግር ኳስ ልማት

ዘንድሮም የተዘነጋ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ ቁልፍ አጀንዳ መሆን የነበረበት አበይት ጉዳይ ነበር፡፡ ዘንድሮም ልክ እንዳለፋት አመታት ሁሉ ተደጋጋሚ የሚባሉ የአልጣኞች፡ የዳኞች እና የሌሎች ባለሞያዎች ስልጠናወችን ፌዴሬሽኑ ሲከውን አልተመለከትነውም፡፡

በታዳጊዎች ልማት በኩል ቢሆንም፡ መውጫ እና መግቢያው በዉል የማይታወቀው የባየር ሙኒክ ክለብ፡ የእግር ኳስ ትምህርት ቤት እና እስካሁን ድረስ ስለ ተግባራዊነቱ ምንም ያልሰማንበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ልማት ፕሮጀክት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በዚህ አመት የእግር ኳስ ልማቱ ላይ በተለይ ታዳጊዎች ላይ እንደሚሰሩ የሰማናቸው፡ ነገር ግን በእቅድ ላይ ብቻ የሚገኙ ተስፋዎች ናቸው፡፡

አቶ ኢሳያሳ ከፊት ለፊታቸው የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለበጎም ይሁን ለመጥፎ ሊቀይሩ የሚችሉባቸው ሶስት የፕሬዝዳንትነት አመታት ይቀሯቸዋል፡፡

በእነዚህ ጊዜያትም፡ ተዐማኒ እና ብቁ የሆነ ተቋም መፍጠር፣ የብሔርተኛ ክለቦችን ሁኔታ መሰመር ማስያዝ፣ የሊግ ፎርማት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረግ፣ የፕሮፌሽናል ሊግ ምስረታ፣ የታዳጊዎች እና ባለሞያወች የእግር ኳስ ልማት ፣ የፌዴሬሽኑን የመተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ ጉባኤ ስብጥር እንዲሁም የአመራር ምርጫ ሂደቱን ማስተካከል፣ ውጤታማ ብሔራዊ ቡድኖችን መገንባት፣ ጠንካራ የፍትህ ስርአት መዘርጋት፣ ጠንከራ የፋይናንስ አቅም መገንባት ዋና ዋና የቤት ስራዎቻቸው ይመስሉኛል፡፡

 

Why Ethiopia should not have fluffed their chance to host CHAN 2020

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *