በ ግርማቸው ከበደ

ፋሲል ከነማ፡ መረጋጋት 

አፄዎቹ የንግስናቸውን ዘውድ ደፍተዋል:: 19 ጨዋታዎች ሳይሸነፉ መጏዝ ትልቅ ትልቅ ስኬት ነው:: ቡድኑ ሁሉም ነገር አለው::

በዓመት 20 ጎል የሚያስቆጥር አጥቂን በሙጂብ ቃሲም- ታታሪነት ስጋ ለብሶ የምታዩበት የመስመር ተጫዋችን በሽመክት ጉግሳ- በበዛብህ እና ሀብታሙ ጥሩ አማካይ እንዲሁም ጠንካራ የተከላካይ መስመርን ይዟል::

የድላቸው ዋና ምንጭ ግን “መረጋጋት” ይመስለኛል:: ቡድኑ አብሮ ቆይቷል:: አሰልጣኝ ሲቀይር ከአስልጣኙ ጋር በርካታ ተጫዋቾችን አላግበሰበሰም:: ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ቋሚ ቡድን ለውጥ ያደረገው ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው::

አሰልጣኙ ስዩም ከበደ ቡድኑን ብዙ አለመንካቱ ምርጡ ውሳኔው ነው:: ይህ የተጫዋቾች አብሮ መቆየት በ2011 ዓ.ም ዋንጫ ማጣት ከፈጠረው ቁጭት ጋር ተጨምሮ ለድል አብቅቷቸዋል::

ቡድኑ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ በአሰልጣኙ ስዩም ላይ ከደጋፊዎች የተነሳውን ተቃውሞ ቢያንስ በአደባባይ የያዘበት መንገድም የመረጋጋት ምልክት ነው:: ዘንድሮ ብቻ ስምንት ክለቦች አሰልጣኞችን በቀየሩበት ሊግ የፋሲል አስተዳዳሪዎች ውሳኔ ቡድኑን ለዋንጫ አብቅቶታል::

 

ኢትዮዽያ ቡና፡ ለካሳዬ ጊዜ መስጠት

የቡና የውድድር ዘመን በካሳዬ አራጌ እና አቡበከር ናስር የሚገለፅ ይመስለኛል:: የሊጉ ምርጡ የሚያጠቃ ቡድን ነው:: አቡበከር ልዩ የውድድር ዘመን አሳልፏል:: እርሱ ለብቻው ያስቆጠራቸው ጎሎች ብዛት የሊጉ ስምንት ቡድኖች እያንዳንዳቸው ከመረብ ላይ ካሳረፏቸው ኳሶች ይበልጣሉ:: በሊጉ የእርሱ አይነት ተስጥኦ ያለው አጥቂ ያለ አይመስለኝም::

ኢትዮዽያ ቡና ውስጥም ሆነ በሌሎች ክለቦች ያሉ አጥቂዎች አቡበከር ካገኛቸው እድሎች ምን ያህሉን ወደ ጎል ይቀይራሉ የሚለው (መላምታዊ ግምት ቢሆንም) አጠያያቂ ነው:: የውድድር ዘመን ሽልማቶችን ጠቅልሎ የመውሰዱ አንዱ ምክንያትም ይህ ይመስለኛል::

ሆኖም አቡበከር ያስቆጠራቸውን ጎሎች ያህል ቡና ገብቶበታል:: የቡድኑ አጨዋወት ለአቡበከር የጎል እድሎችን የፈጠረውን ያህል ቡድኑን ተጋላጭ አድርጎታል:: አቡበከር በግሉ ድንቅ የሆነውን ያህል ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂዎች (ወይም ሁለቱም በጋራ) በግል በሚሰሩት ስህተት ቡድኑ በቀላሉ ጎል ተቆጥሮበታል::

ይህ ግን መስተካከል የሚችል ይመስላል:: በእግር ኳስ ጥቁር ወይም ነጭ የለም:: ብዙ ነገር ግራጫ ነው:: በግራጫ ቦታዎቹ ውስጥ ስህተትን ማሻሻል ይቻላል:: ለካሳዬ ረጅም ውል የተሰጠውም ለዚህ ይመስለኛል:: ካሳዬ የሚገኘው የውሉ ጠዋት ላይ ነው:: ጠዋት ቡድኑን ለአፍሪካ መድረክ ካበቃው ከሰዓት ምን ሊሰራ እንደሚችል አስቦ መታገስ ወሳኝ ነው::

ቅዱስ ጊዮርጊስ፡ ሊጉ ሲቀየር ባሉበት መቆም

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጨረሻ ጊዜ የሊግ ዋንጫ ከወሰደ በኃላ ሻምፕዮን የሆኑት ቡድኖች ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ናቸው:: ለሊጉ መቀየር ከዚህ በላይ ማስረጃ የለም::

የከተማ አስተዳደር ክለቦች ቁጥር ጨምሯል:: የአዲስ አበባ የሊግ ተወካዮች ደግሞ ቀንሰዋል:: በዚህም የአዲስ አበባ ክለቦች የነበራቸውን መጠነኛ የውድድር ሚዛን ወደ እነርሱ ማጋደል አጥተውታል::

አንዳንዶቹ የከተማ አስተዳደር ክለቦች በፋይናንስም በደጋፊም ይበልጥ ጠንካራ ናቸው:: የፈለጏቸውን ተጫዋቾች ማስፈረም ይችላሉ:: አሰልጣኝ ከፈለጉም ማግኘት አያቅታቸውም::

ለዚህ ደግሞ አንዳንዶቹ ክለቦች ወደ ሊጉ ባደጉበት አመት የሚያስፈርሟቸውን ወይም ሊያስፈርሟቸው የሚፈልጏቸውን ተጫዋቾች ማሰብ በቂ ነው:: ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ሌሎች ክለቦች እየፈለጏቸው በፋሲል ለአራተኛ ዓመት የቆዩትን ተጫዋቾችን ማየትም ይቻላል::

በዚህ በተቀየረ የሊግ መልክ አሁንም አሰልጣኝ ስለተቀየረ ብቻ ለውጥ ይመጣል ማለት ከባድ ነው:: ለውጥ ቢመጣም እንኳን ከጊዜያዊ ውጤት ያለፈ አይሆንም::

ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ የባህል ለውጥ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው::


ስለ ጸሀፊው


ግርማቸው ከበደ መንገሻ

የሚዲያ ባለሞያ እና ፍሪላንስ የስፖርት ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *