በ አወቀ አብርሐም

በ1993 ዮርዳኖስ አባይ የመብራት ሃይልን ማልያ ለብሶ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያስቆጠራቸው 24 ጎሎች ለ16 ዓመታት የድሬዳዋውን ልጅ የሊጉ ባለሪከርድ አድርገው ቆዩ!

ከታፈሰ ተስፋዬ አዳነ ግርማና ሳሙኤል ሳኑሚ ለሪከርዱ የቀረቡ ነገር ግን ያልተሳኩ ሙከራዎች በሗላ የደደቢቱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካ ቆይታ መልስ በ2009 ዓ.ም በ25 ጎሎች ሪከርዱን ተረከበ!

ጌታነህ ይህን ሪከርድ በሰበረበት ዓመት አቡበከር በኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን በጥቂት ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ  3 ጎሎች አስቆጥሮ ነበር የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው::

ይህ በሆነ በ4 ዓመት ጊዜ ትንሹ አጥቂ አድጎ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ደምቆ የጌታነህን ሪከርድ የግሉ አድርጏል::በቀሪ 2 ጨዋታዎች ሪከርዱን ለመስበር አዳጋች አድርጎ ሊሰቅለው የሚችልበት እድል በእጁ ነው::

አቡበከር ናስር ጌታነህ ባለ ክብር ከሆነበት ዓመት በ6 ያነሰ ጨዋታ በሚደረግበት ሊግ ላይ 2 ቀሪ ጨዋታዎች እያሉ የሪከርዱ ባለቤት መሆኑ የተጫዋቹን ብቃት በትልቁ ያሳያል::

ከዮርዳኖስና ጌታነህ የሚለየው አቡበከር ተለምዶአዊ 9 ቁጥር አጥቂ አይደለም:: ወደ ሗላ አፈግፍጎ የሚጫወት ሃሰተኛ 9 ቁጥር እንጂ::

በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ቡና ካስቆጠራቸው 41 ጎሎች 27ቱን ከመረብ አሳርፏል:: በመቶኛ ሲሰላ 66 በመቶ የቡድኑ ጎሎች ከእሱ እግር የተገኙ ናቸው!

ከተቀሩት 14 ጎሎች አብዛኞቹ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አለው::

 

ፈጣን ነው ፈጣን እግር ኳሳዊ አዕምሮ አለው አንድ ለአንድ ሲገናኝ ተጫዋች ቀንሶ የማለፍ ክህሎቱ ድንቅ ነው ጎሎች ከማስቆጠር ባለፈም ለጎል እድሎች መፍጠር ላይ ያለው ሚና በአስደናቂ ጎል አስቆጣሪነቱ ቢሸፈንበትም በዚህም ዘርፍ የተካነ ነው!

አቡበከር የእግር ኳስ ተጫዋችነት ህይወቱ ገና እየጀመረ ነው::ካሳለፈው በላይ የሚቀረው ጊዜ በእጅጉ ይበልጣል:: ከጉዳት ርቆ ከቆየና እስካሁን እንዳደረገው በጭብጨባና አድናቆት ጎርፍ መሃል አንገቱን ደፍቶ እግር ኳሱ ላይ ብቻ ካተኮረ ነገ ከዚህም የላቀ ታላቅ ተጫዋች መሆኑ አይቀሬ ነው::

አቡበከር የኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እግር ኳስ ተስፋ ወደ መሆን ተሸጋግሯል!

እንኳን ደስ አለህ አቡበከር!

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *