አዲስ አበባ – መጋቢት 09/2013 ዓ.ም – የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ ከሰዓት በኋላ በኔክሰስ ሆቴል በሶስት አበይት ጉዳዮች ማለትም፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የእስካሁን ዝግጅት፣ በ50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በፌዴሬሽኑ እና በብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማባሪያ ያጣ አለመግባባት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማደር ደራርቱ ቱሉ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ ሌሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የህክምና ቡድን አባላት፣ አሰልጣኞች አትሌቶች እና ሌሎች የቴክኒን ሰዎችም በተገኙበት እና ሶስት ሰዓታን በፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሚከተሉት ዋናዋና ጉዳዮች ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ዙሪያ፡

 • ከህዳር 02/2013 ዓ.ም ጀምሮ 85 አትሌቶች እና 17 አሰልጣኞች በሶስት የተለያዩ ሆቴሎች በመግባት ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ እና ነገር ግን ከነገ ጀምሮ ለቡድን አንድነት ስሜት ሲባል ሁሉም አትሌተች በአንድ ሆቴል ገብተው ዝግጂት እንዲያደርጉ መወሰኑም ተገልጧል፡፡
 • ለኦሊምፒክ ዝግጂት እንዲረዳ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያዎች በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በዙሪክ፣ ሰዊትዘርላንድ የ35ኪሜ የማራቶን ማጣሪያ ውድድር እንዲሁም ከ800ሜ – 10000ሜ ያሉትን ውድድሮች ደግሞ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በሄንግሎ ሆላንድ ለማድረግ መወሰኑ ገልጸዋል፡፡

በ50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዙሪያ፡

ዘንድሮ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን የሚያከበረው አመታዊው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በልዩ ሁኔታ ለማክበር ዝግጂቶች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ መሆኑ ተነግሯል፡፡

 • በስድስቱም ቀናት የሚካሄዱት ሁሉም ውድድሮች የቀጥታ የቴሊቪዥን ስርጪት ሽፋን እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡
 • በውድድሩ ላይ ሁሉም የሀገሪቱ ታዋቂ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡

በፌዴሬሽኑ እና ኦሊምፒክ ኮሚቴው አለመግባባት ዙሪያ፡

የኢትጵያን ስፖርት በቅርበት ለሚከታተል ማንኛውም ግለሰብ በቀላሉ የሚረዳወ ነገር ቢኖር፡ በሁለቱ ተቋማት እና መሪዎቻቸው መካከል ያለው አለመግባባት ዛሬ ያልተፈጠረና በቶሎ የሚፈታ አለመሆኑን ነው፡፡ ዛሬ በነበረው ጋዜጣዊ መግላጫ ላይም አብዛኛውን ሰዓት የያዘው ይኼው ጉዳይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትም ሆኑ ሌሎቹ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አሁን ላይ በግልጽ ወደ ግጪት ያስገቧቸውን እና ከህግ እና አሰራር ውጭ ተፈጸሙ ያሏቸውን ህጸጾች አንድ በአንድ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት፡

 • የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንን መምረጥ ማሰልጠን እና ለውድድር የማዘጀት ሀላፊነት በግልጽ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ሆኖ ሳለ፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከተሰጠው ስልጣን እና ሀላፊነት ውጭ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ጣልቃ በመግባት የቡድኑን ዝግጅት እና የአንድነት መንፈስ እንዲረበሽ አድርጓል
 • ከአምአቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያልተላለፉ መመሪያዎችን እንደተላለፉ በማስመሰል ፌዴሬሽኑ ተረጋግቶ በእቅዱ መሰረት ዝግጅቱን እንዳይሰራ እና አትሌቶቹም እንዲረበሹ አድርጓል፡፡ ለአብነትም ከመሬት ተነስቶ የማራቶን ተሳታፊዎች የመጨረሻ ዝርዝርን በቶሎ አስገቡ ተብላችኋል በማለት፣ አትሌቶቻችን ሳይዘጋጁ ወደ ውድድር ልንገባ ነው በሚል ስሜት አላስፈላጊ መረበሽ እንዲፈተርባቸው ማድረጉ
 • ኮሚቴው ላለፉት አራት ወራት አትሌቶቻችን ላረፉባቸው ሆቴሎች ምንም አይነት ክፍያ ባለፈጸሙ እና ለአትሌቶቻችንም በቂ የልምምድ መስሪያ አቅርቦቶችን ባለማሟላቱ ፌዴሬሽኑ ለሆቴሎቹ የመተማማኛ ቃል በመግባት፡ ከነገ ጀምሮ የተሻለ ዝግጅት ወደሚያደርጉበት ሆቴል በራሱ ውሳኔ እንዲዛወሩ ለማድረግ መገደዱ
 • ላለፉት አራት ወራት ለአትሌቶች እና አሰልጣኞች መከፈል የነበረበት የውሎ አበል ክፍያን ኦሊምፒክ ኮሚቴው መክፈል ባለመቻሉ ፌዴሬሽኑ 3.5ሚ (ሶስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ብር ለመክፈል ተገዷል፡፡ እነዚህ እና ሌሎች በኦሊምፒክ ኮሚቴው በዝግጂቱ ወቅት መሟላት የሚገባቸው ነገሮች መጓደል በአትሌቶቹ እና አሰልጣኞቹ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ሄዶ ሄዶ ሀገርን ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት ፌዴሬሽኑ ሀላፊነት ስለሚሰማው በጊዜ ለማስተካካል ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ሀላፊዎች ከዝግጅቱ ጋር በተያያዘ ከተፈጠሩት እክሎች ባለፈ ከኦሊምፒክ ኮሚቴው እና በተለይም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ያላግባቧቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡

 • ኦሊምፒክ ኮሚቴው በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ሰባት ጠቅላላ ጉባኤዎችን ያካሄደ ሲሆን ከመጀመሪያው ጉባኤ ውጭ አብዛኞቹ ወጪ ከማባከን ያለፈ ትረጉም የሌላቸው እና መደበኛ የጠቅላላ ጉባኤ አጠራር እና አካሄድን ያልተከተሉ በጥቅሉ ህጋዊ ያልሆኑ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም፡ የጉባኤው አጀንዳዎች በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያልተመከረባቸው ነበሩ፣ አጀንዳዎቹ ህጉ እንደሚያዘው ቀደም ብለው ለጉባኤው አባላት ተልከው አያውቁም ወዘተ…
 • የብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሀፊ በጠቅላላ ጉባኤው ወይንም በግልፅ የስራ ቅጥር ማስታወቂያ ተወዳድሮ መሾም/መቀጠር ሲገባው፡ ከሁለቱም ውጭ በፕሬዝዳንቱ የግል ውሳኔ ብቻ በሀላፊነት መቀመጣቸው
 • የብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዓቃቤ ነዋይም እንዲሁ በፕሬዝዳንቱ የግል ምርጫ ሀላፊነት ላይ መቀመጣቸው እና ከላይ የተጠቀሱት ሀላፊነቶች ደግሞ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በመሆን በተቋሙ ሂሳብ ላይ ቼክ ፈራሚዎች መሆናቸው፣ በተቋሙ ውስጥ ላለው አላስፈላጊ የገንዘብ ብክነት አስተዋጽኦ ስለሚኖረው…
 • በዚህ አመት ታህሳስ ወር ላይ በሀዋሳ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የአስፈጻሚ አካላት ምርጫን በሚቀጥለው አመት ከኦሊምፒክ ውድድሩ በኋላ ለማድረግ እና አሁን ሙሉ ትኩረታችን ለውድድሩ ዝግጂት እናድርግ ተብሎ ከተስማማን በኋላ ምርጫው በአስቸኳይ እንዲደረግ የተወሰነበት ምክንያት አሳማኝ ባለመሆኑ
 • በቅርቡ ሊካሄድ ለተሳበው ምርጫ እጩ ለማቅረብ ተብለው የቀረቡት መስፈርቶች ከኦሊምፒክ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ ጋር የሚጋጩ በመሆናቸው
 • በአጠቃላይ በኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዝዳነት እየተተገበረ ባለው የምን ታመጣላችሁ እና አምባገነናዊ አካሄድ መማረራቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የፌዴሬሽኑ መሪዎች እነዚህን እና ሌሎቹንም ቅሬታዎቻቸውን በመዘርዘር ለአለምአቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለአለም አትሌቲክስ እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *