በ ሳሙኤል ስለሺ – የስፖርት ባለሞያ – ለልዩ ስፖርት

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአኖካ ሽልማት

የፅሁፉ መነሻ

ከሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር /አኖካ/ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት /ኦርደር ኦፍ ሜሪት/ ለሐገሪቷ እና ለአህጉሪቷ ስፖርት እድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ በሚል አበርክቶላቸዋል፡፡ ክቡርነታቸው የተበረከተላቸውን ሽልማት በቦታው ተገኝተው አለመቀበላቸውን ተከትሎ በሌላ የተለየ ፕሮግራም አልያም በስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ይወስዳሉ የሚል ግምት ቢኖርም ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎች እርስ በእርስ የሚሸላለሙበት ሌላ ፕሮግራም አዘጋጅተው ተለያይተዋል፡፡

በእለተ እሁድ በተዘጋጀው በዚህ የአኖካ ሽልማት ፕሮግራም ላይ ሱፍ ለብሰው በኢ.ሲ.ኤ አዳራሽ ይገኛሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት መሪያችን በተቃራኒው በቱታ ሽክ ብለው በጦርነቱ የተጎዱ የመከላከያ ሰራዊት አባሎቻችንን ሊጠይቁ  ወደ ሆስፒታል አምርተዋል፡፡ ይባስ ብሎ በአህጉር ደረጃ ትልቅ የተባለውን ሽልማት ያገኙት ጠቅላያችን በየትኛውም አጋጣሚ ስለ ተሰጣቸው ክብር ሲያመሰግኑ አልያም የተሰማቸውን ስሜት ሲገልፁ አልተስተዋለም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስቴር  ፅ/ቤት በኩል የ‹‹ደርሶኛል-አመሰግናለሁ›› የሚል ይፋዊ ደብዳቤ ካሁን ካሁን ይልካሉ የሚል ግምት የብዙዎቻችን ቢሆንም ይኸው ሽልማቱ ከተበረከተላቸው ወር አለፈው፡፡ መደበኛ ደብዳቤው ቀርቶ ዘወትር ስሜታቸውን በሚገልፁበት እና ለህዝባቸው ውስጣቸውን በሚያጋሩበት የማህራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ እንኳን እስካሁን ያሉት አንዳችም ነገር የለም፤ “ተከድኖ ይብሰል” ያሉ ይመስላል፡፡

‘’ለምን ይሄን ያህል የተባለለትን እና ከ6ወራት በላይ ዝግጅት የተደረገበትን ሽልማት እንዲህ ጀርባቸውን ሰጥተው ሊያልፉት ወደዱ?’’ የሚለው ብዙ መከራከሪያዎችን የሚያስነሳ ቢሆንም በእኔ እምነት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በስፖርቱ መስክ የሰሩትን ስራ በራሳቸው ገምግመው ብዙም ሚዛን ስላልደፋላቸው የሽልማቱን ውስጣዊ ዋጋ (Intrinsic Value) ሊቀበሉት እንዳልቻሉ እና በመሰል መድረኮች ላይ ተሰይመው ቢገኙ ፖለቲካዊ ቅቡልነታቸውን እንደሚሸረሽርባቸው ስለተረዱት ነው በማለት እንደሚከተለው ሀሳቤን በሁለት ክፍሎች አቅርቢያለሁ፡፡

ትላንት

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡ ሰሞን አንድ የኢትዮጵያን ስፖርት በአፅንኦት እንደምከታተል የሚያውቅ እና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር  ወዳጄ ደውሎ  ‹‹እንኳን ደስ አለህ! ሙያህ ቀን ሊወጣለት ነው›› አለኝ፡፡ እንደ እርሱ ከሆነ ዶ/ር ዐብይ የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ፕሬዝደንት በነበሩበት ጊዜ  የዩኒቨርሲቲውን ሰራተኞችን እና መምህራንን የመሰብሰብ ልማድ ነበራቸው፡፡ በነዚህም ጊዜያት የስፖርት ጠቀሜታን፣ ለሙያው ያላቸውን ዝንባሌ እና የህይወት ዘይቤያቸውን በማንሳት ምክሮችን ያስተላልፉ ነበር፡፡ ሌላ አንድ ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰራ ወዳጄም ሰውየው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በሚመሩት ስብሰባ መሀል ኮታቸውን አውልቀው ፑሽ አፕ እንደሰሩና በስፖርቱ ዘርፍ ለሌሎች አርአያ ለመሆን እንደሞከሩ አጫውቶኛል፡፡

የእነዚህን ወዳጆቼን ‹‹የእንኳን ደስ አለህ›› መልዕክት ተከትሎ ጠቅላያችንን እና ስፖርታችንን በአንክሮ መከታተል ጀመርኩ፡፡ እንደተባለውም ብዙም ሳይቆይ ለስፖርቱ ምቹ መሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክቶችን አስተውልባቸው ጀመርኩ፡፡ በአንድ ክልል ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ‹‹የወጣቶች ማዕከል ማለት ድንጋይ ጠፍጥፎ አዳራሽ መገንባት አይደለም፤ ወጣት የሚያስፈልገው ከታላላቆቹ ጋር ዱብ ዱብ የሚልበት ሰፋፊ የስፖርት ሜዳ ነው›› ሲሉ ብሰማ ንግግራቸውን ከአሜሪካዊው የቀድሞ ፕሬዝደንት ጆን. ኤፍ ኬኔዲ ንግግር ጋር አመሳስየው አረፍኩት፡፡ ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተባባሪ አዘጋጅነት በማቀርበው “የስፖርት ካፌ” ፕሮግራም ላይ ሁለቱን መሪዎች በማነፃፀር ስፖርቱ ነፃ ሊወጣ እንደሆነ ተረኩኝ፤ ንግግራቸውንም የምር ወስደነው አጀንዳው ዜና ለመሆን በቃ፡፡ በዚህ አላበቁም ብሄራዊ ቴያትር ሳይታሰቡ ተገኝተው እግረ መንገዳቸውን አትሌቶችን አመስግነው ስፖርትን እና ስፖርተኝነትን ሰብከው ወረዱ፡፡ ሌላ ቀን የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ሰብስበው ፈቃደኞችን ፑሽ አፕ አሰርተው ሲጨርሱ ለጉብኝት ወደ ውጭ እንደሚልኳቸው ቃል ገቡ (ምንም እንኳን በአንዳንድ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ነገሩ የተገቢነት ጥያቄ ቢያስነሳም)፡፡ በዚህ አላበቁም መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ቤተመንግስታቸው ቢመጡ አብረዋቸው ፑሽ አፕ ሰርተው በስፖርት ስሜትን እንዴት ማረጋጋት እንደሚቻል አስተምረው ገሚሱን ወደ እስርቤት ሌላውን ወደ ቤቱ ሸኙት፡፡

‹‹እስካልተያዙ ድረስ ሌብነት ስራ ነው›› የሚለውን እና ስር እየሰደደ የመጣ የሐገራችንን ችግር ለመስበር እንደመጡ እና ‹‹ሙስናን›› በስሙ ‹‹ሌብነት›› እያሉ ሲጠሩት ባይ በስፖርታችን ውስጥ ሌብነትን ስራ ያደረጉ ሰዎች መፈናፈኛ ሊያሳጧቸው ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ካልተሳሳትኩ በእኔ እድሜ እግር ኳስን ከስቱዲዮ እና ከስቴዲየም አውጥተው በፓርላማ ደረጃ ያወሩ መሪ እርሳቸው ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ‹‹ወጣትም ገንዘብም አንጨርስም›› በማለት በአሉታዊ ጎኑም ቢሆን በእግር ኳሱ ውስጥ እየታየ ያለው ረብሻ እና ብጥብጥ እንደሚያሳስባቸው ፓርላማ ውስጥ ተናገሩ፡፡

እርሳቸውን ተከትሎ ከወራት በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን የስራ አመት ሲጀምር ባልተለመደ ሁኔታ ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ መንግስታቸው በሶስት ጉዳዮች ላይ ስፖርቱን ትኩረት እንደሚሰጠው አብራሩ፡፡ ‹‹መንገድ ለሰው›› በሚል መሪ ቃል ሰፋፊ ጎዳናዎች እየተዘጉ ሰው ኳስ ይጫወት፣ ስፖርት ይሰራ ጀመር፡፡ ሰውየው የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ ሽርክ መሆናቸውን ተከትሎ ሩዋንዳዊ ስፖርታዊ ባህሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊስፋፉ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡

ዶ/ር ዐቢይ በጦርነቱ የተጎዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በሆስፒታል ተገኝተው ሲጎበኙ

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ፈተናዎች እና ስፖርት

ከጊዜያት በኋላ በጠቅላያችን ፊት አውራሪነት አማካኝነት ይመጣል ብዬ ስጠብቀው የነበረው የስፖርት ዘርፍ ለውጥ እንደጉም እየተነነ፣ ሲደርሱበት እንደሚርቅ የአስፋልት ላይ ውሐ እየሆነ መጣ፡፡ ለዚህ ዋንኛው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ሐገሪቷ ለመሪም ሆነ ለተመሪ ምቹ ወደአለመሆን መምጣቷን ተከትሎ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ እጅግ ፈታኝ፣ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ስራ ላይ ከተጠመዱ የአለማችን ሰዎች መሀከል አንዱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እንደሆኑ ለመመስከር የፖለቲካ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡ እርሳቸው ስልጣን ላይ ከወጡበት ወርሀ መጋቢት 2010ዓ.ም ጀምሮ አንዱን ሲጨብጡት ሌላው እያፈተለከ፣ በዚህ ያለውን ሲይዙት በዛ ያለው እየተበተነ ያሰቡትን እና ያለሙትን በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው እንዳይፈፅሙ አድርጓቸዋል፡፡

የሰላም፣ የፀጥታ፣ የደህንነት አንዳንዴም የሉአላዊነት አጀንዳዎች እዚህና እዚያ መታየታቸውን ተከትሎ የጠቅላያችን ስራ ፈታኝ እንዲሆን  አድርጎታል፡፡ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ሰው መግደል፣ ዜጎችን ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም በስፋት የታዩ እና የመሪያችንን ስራ ያበዙ ነበር፡፡ ከሰው ሰራሽ ችግሮች አለፍ ሲሉ ደግሞ ኮሮና፣ ጎርፍ፣ አንበጣ፣ እምቦጭ የመሳሰሉ የተፈጥሮ ችግሮች ሀገሪቷ በተጠናወታት እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነው ታይተዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ ሆነው እንኳን በተለያዩ መስኮች ማለትም የሰላም ማስከበር ስራዎች፣ የዲፕሎማሲ ግኑኝነቶች እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች ላይ ስኬታማ ሆኖ መንግስታቸው እንዲታይ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ዶ/ር ዐብይ ለስፖርቱ ጠለቅ ያለ ፍቅር፣ ፍላጎት እና ዘመናዊ አረዳድ አላቸው ብዬ ባምንም ኢትዮጵያ ካለችበት እና ከላይ ከተጠቀሱት ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር የልባቸውን መሻት ያህል በስፖርቱ ላይ እንዳልሰሩ ይሰማኛል፤ እርሳቸውም ይሄንን በደንብ ያውቁታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከእኔ እና እርሳቸው በተቃራኒ ግን የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በስፖርቱ ዘርፍ አጥጋቢ ስራ ሰርተዋል በማለት በአህጉሪቱ አለ የሚባለውን ትልቁን ሽልማት ሸልሟቸዋል፡፡

ወጥነት የጎደሉት የአኖካ ሽልማት ምክንያቶች

ዶክተር ዐቢይ መሪያችን ናቸው እና መሸለማቸው በየትኛውም መልኩ ቅር የሚያሰኘኝ አይደለም፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ ባይሸለሙ እንኳን ያለባቸውን ፈተና ብዛት እንደሚረዳ እና እንደሚመለከት ዜጋ ‹‹ነገ ይሰራሉ- ከነገ ወዲያ ይሸለማሉ›› ብዬ የማልፍ ሰው ነኝ፡፡ የሚገርመው ‹‹ተሸለሙባቸው›› ተብለው የተቀመጡት የተለያዩ ነጥቦች እና ምክንያቶች አልፎ አልፎ ለመሪዬ ክብር የማይመጥኑ፣ አንዳንዴ ወጥነት የሚጎድላቸው፣ አለፍ ሲልም ሆነ ተብለው የተጋነኑ መሆናቸውን ተከትሎ የሽልማቱ አላማ ምን እንደሆነ ግራ አጋብቶኛል፡፡

ለምሳሌ በአንድ ወቅት ከተሰጠ መግለጫ በኋላ በአንድ ከፍተኛ ኦፊሴላዊ ማህበራዊ ገፅ ላይ እንደተቀመጠው ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትራችን የኦሎምፒክ ችቦ እንዲዞር አቅጣጫ በመስጠታቸው›› ይላል፡፡ ችቦ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ድሬዳዋ ወይም ሐረር ይሂድ ለማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ሚና ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይሄ በአንድ የሽብርቅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አልያም በአንድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሊሰራ የሚችልን ስራ የጠቅላይ ሚኒስትር ገድል አድርጎ ማቅረብ ለክብራቸው የማይመጥን በሌላ መስክ እያስመዘገቡ ካለው ከፍተኛ ስኬት ጋርም ትከሻ ለትከሻ የማይለካካ ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ‹‹የኦሊምፒክ አካዳሚ እንዲሰራ አቅጣጫ ስለሰጡ›› በሚል እንደተሸለሙ መስማትም ለደረጃቸው የሚመጥን አይደለም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ነገር ሰርቶ በመስጠት የሚያምኑን ሰው ‹‹አስበዋል፣ አቅጣጫ ሰጥተዋል፣ አቅደዋል፣ ወስነዋል፣ ፈልገዋል…›› ተብለው መሸለማቸው ለራሳቸው ሳይገርማቸው አይቀርም፡፡ ሰዎች በተለይም በትላልቅ ደረጃ የሚገኙ መሪዎች የሚሸለሙት በእቅዳቸው ሳይሆን በአፈፃፀማቸው ነው፡፡ በእቅድማ ቢሆን ስንት አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተካፍለን ስንት የአለም ዋንጫ በወሰድን ነበር፡፡

‹‹ላልተገባ አላማ ወደ ፅ/ቤታቸው የመጡ የሰራዊት አባላትን ፑሽ አፕ በማሰራት ስላረጋጉ›› የሚለው እና የኋላ ኋላ መሰማት የጀመረው ነጥብ ደግሞ ሌላው ገራሚ ምክንያት ነው፡፡ እውነት ነው ለዚህ ከፍተኛ ጥበብ ለተሞላበት ተግባራቸው በብልህ መሪነት ዘርፍ አልያም በሰላም ዘርፍ ቢሸለሙ እንደ ኖቤል ሽልማቱ “እልልል….” ብዬ ልቀበል እችላለሁ፡ ነገር ግን ይሄንን የመሪነት ብልሀት እና ጥበብ ለስፖርቱ እድገት እና ልማት በእቅድ፣ በባጀት እና በአመራር ተመርቶ በተደራጀ መልኩ እንደተሰራ ስፖርታዊ ስኬት አድርጎ ለአህጉሪቷ ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት አብቅቷል መባሉ ‹‹እንዴት አሳንሰው ቢያስቡን ነው›› አስብሎኛል፡፡

ከሁሉ ከሁሉ የሚያሳዝነው እና አንዳንዴ ነገሮችን እንድንጠራጠር በመንግስትም ሆነ በመሪዎቻችን እንዳናምን የሚያደርገንን ነገር በትልቅ ደረጃ ሲፈጠር እናያለን፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን ሽልማት የተሸለሙት 3ቢሊየን ብር ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት እና ለአካዳሚ ግንባታ ስለሰጡ ነው›› መባሉ ነው፡፡ በተለይም የአኖካ ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ተገኝተው ይሄንን ደጋግመው መናገራቸውን ስሰማ አንዳንዴ የመሪዎቻችንን ቅቡልነት የሚሸረሽሩት አላስፈላጊ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚሰጡ ሰዎች እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ያልሰማነውን እና እንደዜጋ ያልተነገረንን መረጃ ነጮቹ መጥተው ‹‹እንዲህ ተደርጎላችኋል›› መባላችን አስገርሞኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በአንድ ወቅት ብሄራዊ የኦሊምፒክ ዝግጅት ኮሚቴውን በፅ/ቤታቸው ጠርተው ባነጋገሩበት ወቅት ቃል ገብተዋል የተባለው ‹‹እራት ጋብዘንም ቢሆን በአጠቃለይ በእኔ እና በእናንተ በኩል 3ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ እንሞክራለን›› ነው እንጂ ‹‹3 ቢሊየን ብር እንካችሁ›› አላሉም፡፡

በክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ጥብቅ ክትትል የተገነባው የወዳጅነት ፓርክ

ጠቅላያችን በልዩነት ከሚታወቁባቸው ነገሮች አንዱ ወጣ ያሉ እና ከመንግስት ዕቅድ ውጭ የሆኑ ልማቶችን በራሳቸው ተነሳሽነት ገንዘብ በማሰባሰብ መስራት መቻላቸው ሲሆን ለዚህም የእንጦጦ ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክ እና አሁን በተለያዩ ክልሎች በመገንባት ላይ የሚገኙት ፓርኮች ይጠቀሳሉ፡፡ አንዴ ባለሀብቶችን እራት እየጋበዙ አልፎ አልፎም ከውጭ ሀገር እየለመኑ በሚያመጡት ገንዘብ የሚሰሯቸውን ስራዎች ከመንግስት ካዝና እንደ ልብ እየዘገኑ እንደሚያመጡ አድርጎ የሚያሳይ አጉል ፕሮፖጋንዳ እና የሐሰት መረጃ መንዛት መሪዎችን ከተመሪዎቻቸው ምን ያህል ሊነጥላቸው እንደሚችል የታሰበበት አልመሰለኝም፡፡ ይህ የትላንቱ መንግስት ተዘፍቆበት ኪሳራ በኪሳራ የሆነበትን ባህል የዛሬው መንግስትም ይሁንታ ሰጥቶ ከደገመው ከአመታት በኋላ ከመወቃቀስ እና ከመፋጀት የሚያድነን አይኖርም፡፡

ከፊት ለፊት ያለውን ነገር ብቻ ከተመለከትን (Face Value) ሰበብ አስባብ እየፈለጉ እና ወጥነት የጎደላቸው የማይጨበጡ ምክንያቶችን እያቀረቡ መሪዎችን መሸለም የሚያስከፋ ነገር የለውም፡፡ ከዚህ ቀደምም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የስፖርት ቤተሰቡ ባላመነው መልኩ ‹‹ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ›› በሚል ሽፋን ፊፋ ሽልማት እንዲያበረክትላቸው ተደርጎ የስፖርት ቤተሰቡን ግራ እንዳጋባ ይታወቃል፡፡ የኋላ ኋላ በነገሩ እምነት ባጡ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስቴዲየም ተሰቅሎ የነበረው ባነር ተገንጥሎ መሬት ላይ በመጎተቱ እና በመረገጡ የተነሳ በክለቦች አልፎም በህዝቦች መሀከል ቂም ተቋጥሮ በሀገሪቷ ስፖርት ላይ “ለሽብርተኝነት የቀረበ” ከፍተኛ ረብሻ ማስነሳቱ የትላንት ትዝታችን ነው፡፡

አንዳንድ ሽልማቶች በማን፣ እንዴት፣ ለምን ይዘጋጃሉ እና ይሰጣሉ የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በስፖርቱም ሆነ በሌላው ዘርፍ የሚሰናዱ መሰል የሽልማት ዝግጅቶች ግለሰቦች ከመሪዎች ጋር ያላቸውን ኢ-መደበኛ ቅርበት የሚጨምሩበት፣ ከመሪዎች ጋር ስማቸውን እና ምስላቸውን በማስተሳሰር በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚቀርቡበት፣ የራሳቸውን ምስል ከፍ የሚያደርጉበት፣ በዚህም በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተፈሪነት እንዲሁም ተከባሪነት የሚጨምሩበት መንገድ ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የሎሌ እና የጌታ ክፍፍል ባለበት (Hierarchy)  እና ስልጣን የክብር፣ የዝና እንዲሁም የጉልበት ምንጭ በሆነበት ሀገር  ውስጥ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መታየት፣ እራት መብላት፣ አብሮ መድረክ መምራት እንዲሁም ወዳጅ ተደርጎ መሳል የትርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ይረዳል፡፡ ‹‹እርሳቸው እኮ ለእከሌ ቅርብ ናቸው›› የሚል የስነ ልቦና ታፔላ በፎቶ፣ በሚዲያ እና በንግግር አማካኝነት ዜጎች ላይ በመጫን ግላዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ፣ በተቋማት የግል ጉዳዮቻቸውን ለመፈፀም፣ አሉን ብለው የሳሏቸውን ተቀናቃኞቻቸውን ለማሸማቀቅ እና ትናንሽ ጥቅመኞችን ደግሞ በቀላሉ ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል፡፡

አሁን አሁን በአንዳንድ የኢትዮጵያ ስፖርት ቤት ውስጥ አጓጉል የሆኑ ልማዶች እና ባህሪያት እያቆጠቆጡ መጥተዋል፡፡ የስፖርትን ቁመና በግድ እያጠፉ እና ቅርፅ እያሳጡ ፖለቲካ ዘመም እንዲሆን ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ የሰውነት ማጎልመሻ መምህር የነበረው ፒየር ዲ ኩበርቲን ከዛሬ 130 አመት በፊት የፈጠራቸውን እና በመፅሀፍ ቅዱስም ሆነ በቁራን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸውን የመልካምነት ፍልስፍናን በስፖርት፣ በኦሊምፒክ ጨዋታ፣ በባነር፣ በሎጎ፣ በቀለማት፣ በሞቶ እና በመሳሰሉት አስተሳስሮ ቢያቀርብልንም የእኛ ‹‹ዘመነኞቹ›› ሲረብሹት እያየን ነው፡፡

ኢንተርናሽናል የኦሊምፒክ ቀንን ለማክበር ሁላችንንም ከሚያስማሙን አበበ ቢቂላ እና ደራርቱ ቱሉ ይልቅ የፖለቲካ ምልክት በመሆናቸው ከፊል ደጋፊ/ከፊል ተቃዋሚ ያላቸውን መሪዎችን በታፔላ እና ባነር ላይ እየሰቀሉ በስፖርቱ ላይ ዜጎች የተከፈለ አመለካከት እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው (ምስል-5)፡፡ ከኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲ እና ፍልስፍና ውጭ የኦሊምፒክ ቀለበቶችን እንደ ምርጫ ምልክት ከፖለቲከኞች ፎቶ ስር ማየት ፍልስፍናው ለገባው ህመም አለው፡፡

‹‹ቀለበቱን እንዴት ከፖለቲከኞች ጋር አብራችሁ ትጠቀማላችሁ›› የሚል ትችት ሲደርሳቸው ደግሞ ከቀለበቱ ይልቅ ፖለቲከኞቹን መርጠው ያለ ኦሊምፒክ አርማ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ በአለም የመጀመሪያዎቹ ለመሆን ችለናል፤ እዚህ ጋር የፒየር ዲ ኩበርቲን አጥንት ሳይወጋን ላለመቅረቱ ዋስትና የለንም፡፡ ህዝባዊ ስፖርታዊ ጉባኤዎች እና እንቅስቃሴዎች በጠቅላይ ሚኒስትር፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም በፕሬዝዳንት ፎቶዎች እንዲታጀቡ እና ለስፖርት እንቅስቃሴ የወጡ ዜጎች ደጋፊ ሆኑም አልሆኑ በእነርሱ ጥላ ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡

 

ተያይዞም የማስ ስፖርት ፕሮግራሞች፣ ስቴዲየሞች እና የተለያዩ መሰል ቦታዎች ካድሬዎች ከህዝብ ጋር የሚተዋወቁበት ‹‹የድጋፍ ሰልፍ›› ቅርፅ እየያዙ መተዋል፡፡ ከዚህም አልፎ በእግር ኳስ ክለቦች ውስጥ ስር ለስር በመግባት የደጋፊ ማህበራትን በመቅረብ፣ ማልያዎቻቸውን በመልበስ ወጣቶችን ለማባበል እና ለወደፊቱ የምርጫ ዘመቻ ቀብድ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከጉምቱ ፖለቲከኞች ጋር በህዝባዊ ስፖርት ኮሚቴ ውስጥ እየተደራጁ፣ የፓርቲ አመራሮችን ለረባ ላረባው እየተጠቀሙ እንዲሁም ከፌዴራልም ሆነ ከክልል መንግስታት ጋር ዘወትር መግለጫ እየሰጡ ‹‹ገለልተኛ›› (Neutral) የሆነውን ስፖርት ‹‹ፓርቲያዊ›› ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡

ስፖርት እና ሐይማኖት ከሞላ ጎደል አንድ አይነት ፍልስፍና አላቸው፡፡ ሁለቱንም በመደገፍ ረገድ መንግስት ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም (ይህንንም የሚያደርገው ለራሱ ጥቅም ሲል ነው) እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ የህዝብ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቤተክርስቲያን ላይ የጠቅላይ ሚኒስቴር ፎቶ ተሰቅሎ አይተን እንደማናውቀው ሁሉ መስኪድ ላይ የፖለቲካ አመራር ፎቶዎችን ለጥፈን እንደማናውቀው ሁሉ የስፖርት መልዕክቶችም ሆኑ ቦታዎች ከመሰል ባህሪያት የፀዱ ሆነው ሊታዩ ይገባል፡፡ ይህ አለም አቀፍ የስፖርት ፍልስፍና እና የኦሊምፒክ መሰረት ሲሆን በአንድ ሐገር ውስጥ ይህንን ሳያከብሩ እና ሳያስከብሩ ህዝባዊ የስፖርት ተቋማትን እየመራሁ ነው ማለት በዘርፉ ትንሽ ፊደል ለቆጠርን ሰዎች የሚዋጥ አይደለም፡፡

በክፍል ሁለት፡- የኢትዮጵያ ስፖርት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ይበልጥ እየተጎዳ እንደሄደ የሚያሳዩ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ላይ ጥያቄ የሚያጭሩ አምስት በከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ሊሰሩ የሚገቡ ተጨባጭ ማሳያዎችን አቀርባለሁ፡፡ 


ስለ ጸሀፊው


ሳሙኤል ስለሺ

ፀሀፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የስፖርት ስነልቦና እና የእግር ኳስ መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ሲሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡  

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

2 Comments

  1. It is time and correct to forward educative comments to undress wolf with sheep’s hide our dirty hands can pollute clean sport. Sport should not serve as a landing mattress for drop out politician

  2. Hiya, I am really glad I have found this information. Nowadays bloggers publish just about gossip and web stuff and this is actually annoying. A good website with interesting content, that is what I need. Thank you for making this website, and I will be visiting again. Do you do newsletters by email? Ileane Arie Denie

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *