ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ20 አመት ቆይታው ከ500,000 በላይ ሯጮችን አሳትፏል!

የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዘንድሮው ውድድር የፊታችን እሁድ (ጥር 2/ 2013 ዓ.ም) የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የመከላከል ስራን ታሳቢ ባደረገ እና በሶስት የተለያዩ የመነሻ ማዕበላት በመስቀል አደባባይ ተጀምሮ መጨረሻውን አትላስ አካባቢ በማድረግ ይከናወናል።

20ኛውን የታላቁ ሩጫ ውድድር እስከ 50,000 ተሳታፊዎች እንዲካፈሉበት ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፡ በወረርሽኙ ምክንያት ቁጥሩ ወደ 12,500 ዝቅ ተደርጎ እና በልዩ ጥንቃቄ እንዲከናወን ተወስኗል። የዘንድሮው ውድድር ተሳታፊዎች ቁጥር ቢቀንስም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በእስካሁኑ ቆይታው ከ500,000 በላይ ተሳታፊዎችን ማሳተፉ ተገልጿል።

ውድድሩ ከጤና ሯጮች በተጨማሪም የ5000ሜ የአለም ሻምፒዮኑ ሙክታር እድሪስ፣ ከአራት አመታት በፊት ውድድሩን ያሸነፈው አቤ ጋሻሁን፣ የአምናው ቅድሚያ ለሴቶች ውድድር አሸናፊዋ ጽጌ ገብረ ሰላማን ጨምሮ ከኬንያ እና ኤርትራ ከመጡ ሌሎች አትሌቶች ጋር ወደ 300 የሚሆኑ ወንድና ሴት አዋቂ አትሌቶችም የሚፎካከሩበት ይሆናል።

በኮቪድ 19 ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ የውጪ ሃገር ተሳታፊዎች በአካል መጥተው የውድድሩ አካል መሆን ባይችሉም፤ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የውጪ ሀገራት አምባሳደሮች የሚሳተፉበት የዲፕሎማቶች ውድድር ግን እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ20 አመታት ቆይታው፡ የሩጫ ስፖርት በህዝቡ ዘንድ እንደ መዝናኛ አማራጪነት እንዲታይና እንዲዘወተር በማድረግ ጤናማ ማህበረሰብን በመፍጠር፣ ለታዳጊ አትሌቶች ደረጃውን የጠበቀ ውድድር በማዘጋጀት አለምአቀፍ የውድድር ልምድ እንዲያገኙ በማመቻቸት እና ተተኪወችን በማፍራት፣ በስፖርት ቱሪዝም መልክ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት እና የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ በጥቅሉ ስኬታማ አመታትን ማሳለፉን፤ ዛሬ ረፋዱን በኸያት ሪጀንሲ ሆቴል ከውድድሩ አስቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲ ኤታ የተከበሩ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ፣ ኬንያዊው ጋዜጠኛ ኤልያስ ማኮሪ፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም እና የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ገልጸዋል።

በዚህ ውድድር ተሳታፊ ለሚሆኑት ሁሉም አዋቂ አትሌቶች የኮቪድ 19 ምርመራ በታላቁ ሩጫ አስተባባሪነት በዛሬው እለት የተደረገላቸው ሲሆን ውድድሩም በጥብቅ የኮቪድ መከላከል ጥንቃቄ ታጅቦ እንደሚካሄድ ታውቋል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *