በ ዐቢይ ሐብታሙ – ለልዩ ስፖርት

ጤና ይስጥልን ክቡራን የልዩ ስፖርት ገፅ አንባቢያን በዚህኛው የጤና አምዳችን እምብዛም ስለማይታወቀው አሎፔሺያ(Alopecia) ስለሚባል የጤና እክል፣ በበሽታው ስለተጠቁ የተለያዩ ስፖርተኞች፣ ስላሳለፏቸው ከባድ የህይወት ውጣ ውረዶች እንዲሁም ስለስኬቶቻቸው አስቃኛችኋለው።

አሉፔሺያ ፀጉርን ከራስ ቅልና ከሰውነት ላይ በከፊል ኾነ በሙሉ የሚያረግፍ የበሽታ ዓይነት ነው። ሰበቦቹ በርካታ ቢኾኑም በዘር በሚተላለፍ ተፅዕኖ፣ የሆርሞን መምከን እንዲሁም አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ዋነኞች ናቸው።

እንደ የአሜሪካ ብሔራዊ አሎፔሽያ ፋውንዴሽን(National Alopecia foundation of the United states) መረጃ በመላው ዓለም ከመቶ ዓርባ ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች በአሎፔሺያ ተጠቅተዋል።

በበሽታው የተጠቃ አንድ ግለሰብ ፀጉሩ በፍጥነት ስለሚረግፍበት ባዶ ራስ ቅል የመቅረት ዕድሉ ሰፊ ይኾናል። በሽታው የሚያስከትላቸው ችግሮች ከስነ ልቦና ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።
በዕርግጥ ተጠቂዎቹ ህመማቸውን እንደ እርግማን ባይቆጥሩትም በአንፃሩ ጥቂት የማይባሉት የመከራ ያህል ያዩታል።

ስለስፖርታዊ ጉዳቶች ጹሐፎችን ለማዘጋጀት ጥናት ሳደርግ በአሎፔሺያ ህመም የተጠቁ በርካታ እውቅ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ከየስፖርት ዘርፉ እንደሚገኙ ለመረዳት ችያለሁ።

በዚህ ረገድ የበርካቶችን ስም ማንሳት ቢቻልም ከቆፍጣናው የእግር ኳስ አልቢትር እስከ ኤን ቢኤ ቅርጫት ኳስ ተጨዋቹ ቪላንዌቫ፣ ከእንግሊዛዊው እግር ኳስ ተጫዋች ጆንጆ ሼልቪ እስከ ሌላኛዋ ኤንግሊዛዊት የብስክሌት ተወዳዳሪ ጆሃና ሮሴል ድረስ ያሉ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ድንቅ ታሪኮችን ብቻ መራርጬላኋለሁ።

ፔርልዊጂ ኮሊና

ይህ ስም ከበርካታ ስሞች በላይ ገናና ነው። እርሱ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ በአልቢትርነት የነገሰ የዳኝነት ጄነራል ነበር ። እንደተወረወረ የእሳት አሎሎ በአይኖቹ የሚወረወረውን ቁጣ ፊት ለፊት ደፍሮ የሚጋፈጥ አንድስ እንኳ አልነበረም። ፈገግታም በእርሱ ያምራል። ለሙያው የተሰጠ፣ ከብሮ ሙያውን ያስከበረ ታላቅ አልቢትር ነበር። ስለዚህ ሰው ብዙ ማለት ቢቻልም ነገረ ጉዳያችን ከአሎፔሺያ ጋር በተገናኘ ያለውን ህይወቱን ማስቃኘት ነውና ሰለአልቢትርነት ህይወቱ በሌላ አምድ ላይ በሰፊው አጫውታችኋለሁ።

ፔርልዊጂ ኮሊና የራስ ቅልና ሰውነቱን ፀጉር ያጣው የሃያ ዓራት ዓመት ወጣት ሳለ ነበር። በበሽታው በተጠቃ ሁለት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜያት ውስጥ ነበር ፀጉሩ የረገፈው። ኮሊና እንግዳ የኾነውን ነገር ለመቀበል አልተቸገረም። ምናልባት ነገሮችን ማመዛዘን የሚችልበት ዕድሜ መኾኑ እንደጠቀመው ይናገራል።

ጣልያናዊው የዳኝነት ስልጠና ለመውሰድ በአስራ ሰባት ዓመቱ ተመዘገበ። በሃያ ዓራት ዓመቱ ደግሞ የፕሮፌሽናል ቡድኖች ጨዋታዎችን በብቃት መዳኘት የሚችልበትን ደረጃን ተቆናጠጠ። በአገረ ጣልያን በ1980 ዎቹ አጋማሽ የራስ ፀጉርን ኾነ ፂምን ሙልጭ አድርጎ የሚላጭ (በዜሮ የሚቆረጥ) መመልከት እምብዛም ያልተለመደ ነበር። ይኹንና አንድ ፔርሉዊጂ ኮሊና የሚባል የመጪ ዘመናት ብርቱ አልቢትር በጣልያን እግር ኳስ በኩል ከዓለም ጋር ተዋወቀ። የመጀመሪያ የዳኝነት ሥራው ሶሻል ኤክስፐርመንት የሚሉት ዓይነት ነበር። በወቅቱ የነበረው የጣልያን አልቢትሮች ኮሚቴ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች ለወጣቱ ዳኛ ምን ዓይነት አቀባበል እንደሚያደርጉለት ለማየት እስካየው ጓጓሁ ሆነበት። ለክፉ የሚሰጡ ነገሮች ግን ቢያንስ አልተከሰቱም።

ኮሊና የዳኝነት ሥራን ሀ ብሎ ስለጀመረባት የመጀመሪያ ጨዋታ በአውቶባዮግራፊው ላይ እንዲህ ይገልፃታል። ” ከበርካታ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ይልቅ ያቺን ጨዋታ በሚገባ አስታውሳታለሁ። የወደፊት ዕጣ ፈንታዬን ከሚወስነው የሥራ ጥራት ይልቅ ስለገፅታዬ ማሰብ ከባድ ነበር። እንደ ዕድል ኾኖ ግን ተጨዋቾቹ ከሌላው ነገር ይልቅ በውሳኔዎቼ ደስተኞች ነበሩ። ለዚህም ሁልጊዜ ስለእነርሱ ክብር አለኝ።”

የጣልያናዊው እውቅና እድገት የጀመረው አሉፔሺያ ፀጉሩን አሳጥቶት ከተፈጠረበት እንግዳ የኾነ ገፅታና የሥራ መስጠትና በራስ መተማመኑ መዳበር በኋላ ነበር።

ኮሊና አሎፔሺያ በደለኝ አሊያም ይህን አሳጣኝ አይልም ይልቁንም እውቅና እንዲያገኝና ከሌሎች ለየት ብሎ ዓይን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። የሲዊዝ ሎሬንዝ ሰዓትንና ኤርያል የተባለውን የቱርክ ሞባይል ኦፕሬተርን ማስታወቂያ ሰርቷል። የካርቱን ምስሉ በዝነኛው ሙዚቀኛ ጆርጅ ማይክል ክሊፕ ላይ መታየት ችሏል ደግሞም እውነተኛ ስታርም ሆኗል።

በ2015 አገረ ጣልያን በአሎፔሺያ የራስ ፀጉሩ የረገፈበት የብሬሺያ ተወላጁ የአስራ አንድ ዓመት ልጅ መከራ ይሉት ነገር አጋጥሞት ነበር። የታዳጊ ህፃናት ቡድኖች ጨዋታ ላይ ከተቀናቃኞች ዘንድ የስላቅና ፌዝ ቃላትን አስተናገደ። የኾነው ሁሉ ከታዳጊው አዕምሮ በላይ ስለነበር እንባውን እያዘራ በሩጫ ሜዳውን ለቆ ወጣ። ከጨዋታው በኃላ ግን አሰልጣኙ ከታዳጊው ህፃን ጎን ለመቆም ፀጉሩን ተላጭቶ አይዞህ ከጎንህ ነኝ ብሎታል። የታዳጊውን አሰልጣኝ በመከተል ሌሎችም ከየአቅጣጫው የድጋፍ ድምፃቸውን ማሰማት ጀመሩ። እውቁ ፔርልዊጂ ኮሊናም አንዱ ነበር። እንደውም ደብዳቤም ፅፎለታል።

የኮሊና ደብዳቤ

“እኔ ማን እንደኾንኩ ለማወቅ በጣም ታዳጊ ነህ” ይላል የደብዳቤው መግቢያ። ኮሊና ይቀጥላል “አንድ ጊዜ የ pro evolution PlayStation ተጫውተህ ቢኾን ልታየኝ ትችል ነበር። በአሎፔሺያ ሳቢያ እንዲህ ዓይነት ገፅታ አለኝ። ሙሉ ፀጉሬን አጥቻለሁ። በጊዜው የሃያ ዓራት ዓመት ወጣት ብኾንም በጣም ዕድለኛ ነበርኩ። ፀጉሬን ማጣቴ ህልሞቼን ከማሳካት አግዶኝ አያውቅም ይልቁን ይበልጥ በቀላሉ ታዋቂና ዝነኛ አድርጎኛል። ይህንንም ቢሆን በርካታ ጊዜያት ተነግሮኛል። ስለዚህ ላንተ ያለኝ ምክር ‘በመላጣህ ምክንያት በየጊዜው ሰዎች ቢጮሁብህ ቸል በላቸው፣ ንቀህ እለፍ። በውስጣቸው ጥላቻ አለባቸው። ባያውቁትም ቅናት አለባቸው። ቢቀኑብህም ከምንም ነገር አያግዱህም። ያለፀጉርህም ቢኾን መጓዝ አለብህ። አሰልጣኝህ በጣም ጥሩ ገፅታን ፈጥሯል። ስለዚህ ልትኮራ ይገባል። አሁን አትፍራ ወይም አይናፍር አትሁን።”

ጆንጆ ሼልቪ

አንድ ወቅት የዌስትሃም ዩናይትድ ደጋፊዎች በሀሪ ፖተር አስፈራርተውታል። ከኮሊና በተቃራኒ እንግሊዛዊው የኒው ካስትል ዩናይትዱ አማካይ የራስ ፀጉሩን ያጣው ገና በለጋ ዕድሜው ነበር።ገና የዕድሜ ማለዳው ሼልቪ ከደረጃ ላይ ወድቆ የራስ ቅሉ ተጎዳ። ከዚያም በአሎፔሺያ በሽታ ተጠቃ። የበሽታውን ዕድገት ለማዝገም ዶክተሮች ለሦስት ወራት ያህል የራስ ቅሉን የተለየ ቅባት( special ointment) እና ሻሽ መሰል ነገር ጠቅልሎ እንዲተኛ ታዘዘ። ነገር ግን ታዳጊው ጆንጆ ዶክተሮች ያዘዙትን መፈፀም የቻለው ለተከታታይ ዓራት ቀን ብቻ ነበር። ሁሉንም ነገር አቁሞ በዕምቢተኝነቱ ፀና።

“ራሰ በራነትን በጣም ስለማፍር እስከ አስር ዓመቴ ድረስ ከስንት አንዴ ነበር ያለ ቤዝ ቦል ኮፍያ ከቤት የምወጣው።” ይላል ዝነኛው እግር ኳስ ተጨዋች ነው።

በጊዜው ታናሽ እህቱ ሊሊ ትልቅ እገዛ ታደርግለት ነበር። እግራቸውን ለማፍታታት በጎዳናው ጥግ ከታች ላይ ሲሉ ወንድሟን አተኩረው የሚያዩ ሰዎችን ዓይናቸውን ከእርሱ ላይ እንዲነቅሉ ትናገራቸው ነበር። ቤተሰቦቹ የሚኖሩት በምስራቃዊ ለንደን ሀሮልድ ሂል አካባቢ ነበር።
የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ይጮሁበትና ብስጭት ውስጥ የሚከቱ ቅፅል ስሞቾ ያወጡለት ነበር። የሼልሺ የልጅነት አስተዳደግ ከማህበራዊ ህይወት በራቀ ነበር።

በፈረንጆቹ ምዕተ ዓመት(Millennium) አባቱ የታዳጊዎች እግር ኳስ ቡድን ሲከፍቱ ሁሉንም ልጆቻቸውን ወደ አካዳሚው አካታቷቸው። ከልጆቻቸው መካከል ጆርጅ የተባለው ትልቁ ልጃቸው ጥሩ የእግር ኳስ ተሰጥኦ ስለነበረው በጊዜው እንደ ቶተንሃምና ዌስትሃም ባሉ ታላላቅ ክለቦች መልማዮች የመታየት ዕድል ነበረው።

ሼልሺ ስለ ታላቅ ወንድሙ ጆርጅ አንድ ወቅት ይህን ተናግሮ ነበር። “ወንድሜ ከኔ በተሻለ ባለተሰጥኦ ነበር ይኹንና እግረ መንገዱ ሁሉ ወደ ምሽት ክበቦችና ሴቶች ዘንድ ስለነበር ተሰጥኦዎን በሚገባ አልተጠቀመበትም።” በአንፃሩ ስለራሱ ሲናገር ምንም ጓደኞች ስላልነበሩት እግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረት ያደርግ እንደነበር ይገልፃል።

አምኗት የወደፊት ተስፍዬ ናት ብሎ የሙጢኝ ያላት እግርኳስ አላሳፈረቺውም። ሊቨርፑልን ጨምሮ ለተለያዩ ክለቦች የመጫወት እድልን አግኝቷል ምንም እንኳ በገፅታው ሳቢያ የሚደርስበት የቃላት ጥቃት ተጠናክሮ ቢቀጥልም።
2013 የውድድር ዘመን የሊቨርፑል ተጨዋች ኾኖ ከዌስትሃም ጋር ሲጫወቱ ከተቃራኒ ክለብ ደጋፊዎች የደረሰበትን የሽሙጥ ወርጅብኝ ዝንት ዓለም እንደማይረሳው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይናገራል። ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከመግባቱ በፊት በሜዳው ጠርዝ ሰውነቱን ለማፍታታት ብቅ ሲል ‘ሀሪ ፖተር ይገባላችኋል'” እያሉ መጮህ ጀመሩ። ጆንጆ ግን ከመበሳጨት ይልቅ በፈገግታ አፀፋዊ ምላሽ ቸራቸው። ከጨዋታው በኃላ ደግሞ የዌስትሃም ደጋፊዎች ለሚወዱት ክለባቸው ባለመጫወቱ እንደሚቀኑበት ተናገረ።

ከዓመት በኋላ ለሲዋንሲ ክለብ እየተጫወተ አስቶንቪላ ላይ እጅግ አስደናቂ ጎል አሰቆጠረ። በቀጣዩ ቀን ግን አንድ ልብ የሚነካ ደብዳቤ ከአንድ ብላቴና ደረሰው።

“ሰላም! ሀሪ ጃኮብስ እባላለሁ። ሰባት ዓመቴ ነው። ትላንት ከዓርባ ሁለት ሜትር ላይ ያስቆጠርከውን ጎል ተመልክቼዋለው። እጅግ ድንቅ ነበር። እኔም እንዳንተው የአሎፔሺያ ተጠቂ ነኝ። ያን ያህል መጥፎ አይደለም ምክንያቱም ወደ ፀጉር ቤት መሄድ አያስፈልገንም። ይሁን’ጂ አሁንም ድረስ ‘መላጣነቴን’ አልወደውም። አንተ የትምህርት ቤቴ እውነተኛ ጀግና ነህ። ከትምህርት ቀናቶች በአንዱ ትምህርት ቤታችን መምጣት ትችላለህ? ሁላችንም ደስተኞች እንሆን ነበር።”

ከዛስ ምን ተፈጠረ?

ሼልቪን ሰው አክባሪ ነው በተለይ ደግሞ ልጆችን በተለየ ሁኔታ ይመለከታቸዋል። ግብዣውን ተቀብሎ የታዳጊው ትምህርት ቤት ተገኘ። በዚህ ብቻ አላቆመም ስዋንሲ ከሳውዛምተን ባደረገው ቀጣይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ላይ ታዳጊውን ከነቤተሰቡ ጋበዛቸው። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በጆንጆ ጥያቄ መሰረት ታዳጊው ሀሪ ወደ ሊበርቲ ስታዲየም መጫወቻ ሜዳ መጥቶ መልዕክት አዘል ፍፁም ቅጣት ምት እንዲመታ ተደረገ።

ቻርሊ ቪላኑዌቫ

ቻርሊ ቪሊኑዌቫ ኤን ቢ ኤ (NBA) ወስጥ በአጥቂነት ለአስራ አንድ ዓመታት የተጫወተ ድንቅ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ነው። ቶሮንቶ፣ ሚልዋኬ፣ ዲትሮይትና ዳላስ ውስጥ ነበር። 2006 ላይ አዲስ አዳጊ ሻምፒዮን ቡድን ውስጥ መካተት ችሏል። በዚህም ለአሜሪካ አዳጊ ሻምፒዮና ቡድን ጥሪ ተደርጎለታል። 2009 ላይ ቻርሊ የስፖርቶች ዜግነቱን ለወጠ። እስከ ሙያ ዘመኑ ማብቂያ ድረስ ለዶሚኒካ ሪፐብሊክ ተጫውቷል።

ቪላኑዌቫ የራስ ፁጉሩን ያጣው በአስር ዓመት ዕድሜው ነበር። አዲስ ገፅታው ያመጣበት ፈተና ከባድ የሚባሉ ጊዜያትን እንዲያሳልፍ አድርጎታል “የራሴ ቆዳ ምቾት አይሰጠኝም። ሁልጊዜ ኮፍያና አሊያም ኮፍያ ያላቸውን ሹራቦች አዘወትር ነበር። ሰዎችን በሙሉ አይኔ ተመልክቼ አላውቅም ምክንያቱም የቅንድብ ፀጉሮች እንደሌሉኝ ልብ እንዲሉ ስለማልፈልግ”

በትምህርት ቤት ቆይታው ምንም እንኳ ዘለግ ባለው ቁመቱና ፈርጣማ ጡንቻዎቹ ከእኩዮቹ ለየት ብሎ ቢታይም በበሽታው ምክንያት ውስጡ ይረበሽ ነበር።
ቻርሊ በህይወቴ አተረፍኩባቸው ከሚላቸው ነገሮች ውስጥ ቅርጫት ኳስ ዋነኛው ነው።

“ጨዋታ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ቅርጫት ኳስ ቴራፒዬ ሆኗል። በጨዋታ ሰዓት የጭንቅላት መሸፈኛ ስለማደርግ በሂደት ተመልክቾች ከገፅታዬ ይልቅ በጨዋታው ውበት እንደሚገመግሙኝ መረዳት ጀመርኩ። አስታውሳለሁ የደብታ ስሜት ስለታከተኝ አንድ ቀን መስታወት ፊት ቆሜ ‘እውነታውን መቀበል አለብህ’ ስል ለራሴ ነገርኩት።”

ቪላኑዌቫ ቅርጫት ኳስ ጨዋታ ሲያቆም የፎካል አሎፔሺያ ብሔራዊ ፋውንዴሽን ተጠሪ ኾነ። አሁን ላይ በርካታ በጎ አድራጎት ሥራዎችንና ትምህርት ሰጪ ቪዲዮዎችን ይሰራል። ለታመሙ ህፃናትም ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ያደርርጋል።

“ለወጣቶች ተምሳሌት መኾን ያስፈልገኝ ነበር ምክንያቱም እንደ አርአያ የምመለከተው ሰው ስላልነበረኝ ። እናም ያንን እንዳጣሁት ይሰማኛል። በዕርግጥ እጦት ሊረዳኝ እንደሚችል አውቄያለሁ። ሌሎችን ለመረዳት በአሎፔሺያ ተጠቃሁ። ይህ በረከቴ ነው።”

2016 ላይ በግራ ክንዱ ላይ ‘አሎፔሺያ በመልዓክ ክንፎች ላይ አርፏል’ የሚሉ ቃላትን ተነቅሷል። በየዓመቱ ሁለት መቶ ሺህ ኬዞች በሚመዘገቡባት አሜሪካ፣ ቻርሊ አሎፔሺያ ያስከተለበትን የጤና መጓደል ታግሎ የረታ እውነተኛ ጀግና ነው።

ጆሃና ሮሴል

ጆሃና ሮሴል እንግሊዛዊት የብስክሌት ግልቢያ ተወዳዳሪ ናት። የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮናም ናት። ጆሃና በአሎፔሺያ የተጠቃችው ገና የአስር አመት ወጣት ሳለች ነበር። በወቅቱ የህክምና ባለሙያዎች ወላጆቿን ስለመከሯቸው ቀን ከሌት ክብካቤ አልነፈጓትም።
ዕድሜዋ እየጨመረ ሲመጣ አዳዲስ ለውጦችን ቆዳዋ ላይ መመልከት ጀመረች። አስራ ስድስት ዓመት ሲሞላት የቅንድቧ፣ አስራ ዘጠኝ ዓመቷ ላይ ደግሞ የራስ ፀጉሮቿ በሙሉ ረገፉባት። በመጨረሻም አይቀሬ ነውና ከአዲሱ ገፅታዋ ጋር ለመላመድ ተገደደች።

ስለሁኔታው እንዲህ ትገልፃለች “ፀጉሮቼ መርገፍ ሲጀመሩ ክፉኛ ድንጋጤ ውስጥ ገባሁ። ረጅም ፀጉር እወድ ነበር። ማስዋብም እንደዛው። አስታውሳለሁ አንድ ምሽት በምሬት እያባሁ ወላጆቼን ‘ይህ ስለምን ይኾናል?’ ስል ጠየኳቸው። ስለገፅታዬ ማሰብ ስለማልፈልግ ለሜክ አፕና አልባሳት ግድ የለኝም ነበር።”

ጆሃና የብስክሌት ግልቢያ ውድድርን መምረጧ ብቻ ልዩ ሴት አድርጓታል። በልምምድና ውድድሮች ወቅት የአደጋ መከላከያ ቆብ(Helmet) ታደርጋለች።

ሮሴል እጅግ ስኬታማ የብስክሌት ግልቢያ ተወዳዳሪና ባለድል ናት። የሁለት ጊዜ የኦሎሞፒክ ወርቅ ሜዳሊያና የአምስት ጊዜ የአለም ሻምፒዮና አሸናፊነቷ በስፖርቱ ማህደር በደማቅ የተመዘገቡላት አንፀባራቂ ድሎቿ ናቸው።

በለንደን ኦሎምፒክ በቡድን አጋሮቿ እገዛ የአለምን ሪከርድ በማሻሻል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ኾነች። ሄልሜቷን በማውለቅ ከቡድን አጋሮቿ ጋር የክብር ትርዒት አሳየች።

አሁን አዕምሮዋ ስለጎለበተ አሉታዊ ስሜቶቿ በሙሉ ተወግደውላታል። ስለበሽታውም ያላት አመለካከት በእጅጉን ተለውጧል። ወደ ክብር ሽልማት ኾነ ንግግር ታደርግ ዘንድ የምትጋበዝባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ያለ ሰው ሰራሽ ፀጉር ትገኛለች።
አሸናፊነቷ በዓለም አቀፍ የአሎፔሺያ ቀናት ላይ ተደጋግሞ ተዘክሮላታል።

ጆሃና ለበርካታ የህትምት ውጤቶች በሰጠቻቸው የግል ኾነ አካታች ቃለ መጠይቆች አሎፔሺያ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ከመሸሸግ ይልቅ ወደፊት ብቅ ማለት እንዳለባቸው ወትውታለች። ጭንቀት ምንም እንደማይፈይድ ታስረዳለች።

“ጠንክሮ መሥራት ስለወደፊቱ ከመጨነቅ አድኖኛል። ቤተሰብ ይኑረኝ አይኑረኝ፣ ሰዎችን እንዴት ላገኝ እችላለሁ በሚሉ ሃሳቦች እንዳልሰንፍ ረድቶኛል።”
አሎፔሺያን በተመለከተ የብስክሌት ግለቢያ ወደህይወቴ ሲመጣ ተመሳሳይ ፍልስፍናን ተከተልኩ። አሎፔሺያ ስፖርቶች ላይ ብቻ እንዳተኩር ረድቶኛል። የአሁኑ ማንነቴን የፈጠረው አሎፔሺያ ነው።”
ስለበሽታው ኾነ ስለህይወት ያላት ዕይታ እጅግ ድንቅ ነው።

ባለፈችባቸው የህይወት ውጣውረዶች ራሷን ያበረታችበት የአዕምሮ ጥንካሬ እጅግ ይደንቃል። እውነታን መጋፈጥና ነባራዊውን ሁኔታ መቀበል ግድ መኾኑን ለማስረዳት ከሷ በላይ ምስክር አይገኝም።

“አሁን፣ህይወትን ያለ አሎፔሺያ ማሰብ ያስቸግረኛል” እነዚህ ራሷን አበርትታ ሌሎች መሰል ቢጤዎቿን የምታበረታባቸው ቃላት ናቸው።

ወዳጆቼ! እኛም መከራን መሻገር የምንችልበትን ብርታትና ፅናት፣ ይስጠን። ቸር ያሰንብታችሁ።


ስለ ጸሀፊው


ዐቢይ ሐብታሙ

መምሕር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *