አዲስ አበባ  – መስከረም 27/2013 –  የማልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ እናት ኩባንያ የሆነው መልቲቾይስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ፕሪምየር  ሊግ ጨዋታዎችን በእህት ኩባንያው ሱፐር ስፖርት ላይ የማስተላለፍ ህጋዊ መብት አሸናፊ መሆኑን ገለጸ።  ይህ የኢትዮጵያን እግር ኳስ እና ወዳጆቹን ለመደገፍ ትልቅ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚታመን ሲሆን መልቲ ቾይስ ግሩፕም በኢትዮጵያና በመላው አፍሪካ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰሱንና ሰፊ የኢንቨስትመንት ስራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት የሚያረጋግጥ ነው።

ሱፐር ስፖርት በአሁኑ ወቅት የዛምቢያን ፕሪሚየር ሊግ እና ፕሪሚየር ሶከር ሊግ የተሰኘውን ተወዳጅ የደቡብ አፍሪካ ሊግ የሚያስተላልፍ ሲሆን መልቲ ቾይስ ግሩፕ የአፍሪካን ስፖርት ለመደገፍ ያለውን ፍላጎት ባረጋገጠ ሁኔታ የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግንም በባለቤትነት ከሚያተላልፋቸው ታላላቅ  የአፍሪካ እግር ኳስ ሊጎች ውስጥ አካቷታል።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሃገሪቱ ትልቁ እግር ኳስ ዲቪዚዮን ሲሆን በውስጡም 16 ክለቦችን ያካትታል። እነዚህ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችም ከፍተኛ የእግር ኳስ ተመልካች ባለባቸው መላው ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራትና በዙሪያው ባሉ ደሴቶች የሚታዩ ይሆናል።የመልቲቾይስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ካልቮ ማዌላ ስፖርት ለመልቲቾይስ ግሩፕ ያለውን ትርጉምና ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለውን አንደምታ አስመልክተው የሚከተለውን ብለዋል ፡

“በሱፐር ስፖርት በኩል በምናስተላልፋቸው በመላው አፍሪካ በሚሊዮኖች የሚታዩ የስፖርት ውድድሮች በአፍሪካ ተወዳዳሪ የለንም። ስፖርት ለምናቀርባቸው ፕሮግራሞች ወሳኝ አካል ሲሆን የስፖርትን እድገት መደገፍ ደግሞ ለኛ ስራ ትልቅ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው። ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ከፍተኛ ታዋቂነትና በርካታ ደጋፊዎችን ከመላው አፍሪካ የሚያስገኝ ነው።”

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቦርድ ሊቀመንበር መቶ አለቃ ፈቀደ ማሞ በበኩላቸው ፡

“የሀገራችንን የእግር ኳስ ሊግና የተጫዋቾችን ችሎታ በማሳደግ ረገድ ትክክለኛውን አጋር የማግኘትን ጥቅም በሚገባ እንረዳለን። ይህ ስምምነት የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ሲሆን፡ ለተጫዋቾች ፡ ለኢንደስትሪውና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በአጠቃላይ ብሩሁ ጊዜን የሚያመጣና የኢትዮጵያንም እግር ኳስ ለአለም የሚያስተዋውቅ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

“ይህ ስምምነት ለመልቲቾይስና ለዲኤስቲቪ ኢትዮጵያ በጣም አስደሳች ነው” በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ኦማር ባገርሽ ናቸው፡ አክለውም:

“ይህ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የተፈጠረ ትልቅ እድል እንደሆነና በአፍሪካ አህጉር ላይ ግዙፍ ከሆኑ አገሮች አንዷ ለሆነችው ኢትዮጵያ እግር ኳስ መሻሻልና ከስፖርቱ ጋር የተያያዙ በርካታ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃቶችንም እንደሚፈጠር እናምናለን” በማለት ተናግረዋል፡፡

የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ገሊላ ገብረሚካኤል እንዲሁ የተሰማቸውን ሲገልጹ የሚከተለውን ብለዋል፡

“ይህ በተለይ ለኢትዮጵያ የዲኤስቲቪ ደንበኞች በጣም አስደሳች ተጨማሪ አማራጭ ነው። ይህንን አስደሳች ስራ ለመስራትና የሀገራችንን ጨዋታዎች ለሀገራችን ስፖርት አፍቃሪዎች ፍጽም ቀላልና አርኪ በሆነ አገልግሎት ለማቅረብ ከወዲሁ እየተረባረብን እንገኛለን።”

በዚህ ስምምነት መሰረት ሱፐር ስፖርት ስርጭቶቹን ራሱ እያዘጋጀ ጎንለጎን የሀገር ውስጥ የፕሮዳክሽን ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ የሚሰራ ይሆናል።

ሱፐር ስፖርት ሃገር በቀል ሊጎች እንዲያድጉ የሚያደርገው ሁሉን አቀፍ አስተዋጽኦ በየሀገሩ ያሉ ሊጎች በጥንካሬ ላይ ጥንካሬን እየጨመሩ እንዲሄዱ አድርገል፡፡ ከዚህ ስምምነት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያም ፕሪሚየር ሊግ ያለጥርጥር በሱፐር ስፖርት አቅምና ሰፊ ልምድ ውስጥ ተጠቃሚ እንደሚሆንና ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚደርስ ይታመናል።

ይህ ከሰሞኑ መልቲቾይዝ ግሩፕ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያደርጋቸው ቀጣይ ኢንቨስትመንቶች ዙሪያ በተከታታይ ካወጣቸው አስደሳች ዜናዎች ትኩሱ ሲሆን መልቲቾይስ ግሩፕ በመልቲቾይስ ኢትዮጵያ እንደ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፡ በአማርኛ የሚተላለፉትን ዚ አለምና ኒክ ጁኒየርን እንዲሁም ከ13 በላይ የሚሆኑትን የሀገር ውስጥ ቻናሎች ሲያቀርብ ቆይተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ፕሮግራሞች ላይ በሚያደርገው ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ደንበኞቹ አለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና በርካታ አገራዊ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞችን ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል። በመጨረሻም የመልቲቾይስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ማዌላ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት ይህን ብለዋል:

“ይህ ለመልቲቾይስ ግሩፕ ወሳኝ ስምምነት ሲሆን በኢትዮጵያ ብሎም በመላው አፍሪካ ያለንን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነው። የኢትዮጵያዊያንን እውቀትና የሀገር ውስጥ የዘርፉ ኢንደስትሪዎችን በኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ የሚዘጋጁ አስደሳች ኢትዮጵያዊ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለንን ቁርጠኝነት አጠንክረን እንቀጥላለን።

በመላው አፍሪካ የሀገር ውስጥ ገበያ ላይ ያለማቋረጥ ኢንቨስት በማድረግ ለሀገር በቀል ኢንደስትሪዎች ዘላቂነት ፡ ለሀገር ውስጥ ጸሃፊዎችና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጆች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ፕሮግራሞች ስርጭትና ለሀገር ውስጥ የስራ እድል ፈጣሪዎች ማደግ ሰፊ እድል እንፈጥራለን።”

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *