በ ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል – ለልዩ ስፖርት

Haile and Tergat

ዕለቱ አርብ ነው፡፡ አዲስ አበባ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ አላማዎች አሸብርቃለች፡፡ ሚሊዮኖች ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ መንግስት ይህንን ቀን ሰራተኞች ወደ ስራ እንዳይሄዱ ፈቅዷል፡፡ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆችም ተዘግተዋል፡፡ ሁሉም ላይ የአሸናፊነት፣ የትኛውንም ነገር መከወን ይቻላል የሚል ስሜት ይነበባል፡፡

በአውስትራሊያ ሲድኒ ኢትዮጵያን ወክለው የሄዱት 28 ሯጮች፣ ሶስት ቦክሰኞች እና ሌሎች ልዑካንን የያዘው አውሮፕላን በልዩ ጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

አራት ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሶስት ነሀስ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ትልቁ የኦሊምፒክ ድል ነው፡፡ በአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች፤ በአትሌቲክስ አሜሪካንን ተከትላ ከዓለም ሁለተኛ ነች፡፡ ብዙ ዋጋ ከፍለው፣ አንብተው፣ ቆስለው፣ ወድቀው እና ተነስተው  … ሰንደቅዓላማዋን በስስት ለብሰው … የአሸናፊነትን እና የይቻላል መልዕክትን ለኢትዮጵያውያን ጽፈው አትሌቶቻችን ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡

ይሔንን ውለታ መመለስ የፈለጉ ኢትዮጵያውንም አዲስ አበባን ትንፋሽ አሳጥተዋታል፡፡

ባለድል አትሌቶችን የያዘው አውሮፕላን ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እየተቃረበ ነው፡፡ ተዋጊ ጀቶች ለክብራቸው ከፍ ብለው በመብረር አውሮፕላኑን ያጅቡ ጀመር፡፡ ሁለት ሔልኮፕተሮችም የአየሩን ሰልፍ በክብር ከፊት እየመሩት ነው፡፡

አትሌቶቹ በሚወዷት ሀገራቸው ይሔ እንደሚጠበቅባቸው ማወቃቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ከአውሮፕላን ከወረዱባት ደቂቃ ጀምሮ የማይደገም የሚመስል አቀባበል ነበር የጠበቃቸው፡፡ ከከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሚዲያ ባለሞያዎች ጋር በአውሮፕላን ማረፊያ ከተገናኙ በኋላ፤ በፕሬዝዳንታዊ ሊሞዚኖች እና በክፍት ባስ ታጅበው ስሜቱን መግለጽ ወዳቃተው ህዝብ ጉዞ ጀመሩ፡፡

ከዚያ በኋላ ያለውን እያንዳንዱን ትዕይንት መግለጽ እጂግ ከባድ ነው፡፡ “ይቻላል!” የሚለውን የማሸነፍ ስሜት የፈጠረውን፣ ሀገር መውደድን፣ ኢትዮጵያዊነት ያለውን ውድ ዋጋ ያንጸባረቀውን ያንን ድል እና የተመልካቹን ስሜት በምንም መንገድ መግለጽ አይቻልም፡፡

ባለድል ኮከቦችም የሚያዩትን ማመን አልተቻላቸውም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠረው ህዝብም አትሌቶችን የሚገልጽበት ድምጽም ትንፋሽም አጥሮታል፡፡ “ይሔንን ማመን ያቅታል፡፡ አቀባበል ጠብቄያለሁ፣ እንዲህ ይሆናል ብዬ ግን በፍጹም አልገመትኩም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ኢትዮጵያ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ማለት ነው፡፡ እኛ ዕደለኞች ነን!” ኃይሌ ገብረስላሴ፡፡

አሐዱ

ሁሉም የሆነው ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፡፡ በኦሊምፒክ የቅብብሎሽ ታሪክ ሁሉ የማይቻለው የተቻለው፣ የማይፈጸመው የተፈጸመው… ሀገርን ለማንገስ በተደረገ ፍልሚያ ነው፡፡

ከህመም ጋር ታግለው ያሸነፉት፤ ሆዳቸውን ይዘው የሮጡት፤ ለመሮጥ ብቻ አይደለም፣ ለመቆም የሚከብድ የዕግር ህመም ችለው አንገት ለአንገት ተናንቀው የድል ክር የበጠሱት፡ ለኢትዮጵያዊነት ከፍ ማለት ነው፡፡ የአትሌቲክስን ረጅሙንም ፈታኙንም ውድድር በባዶ እግር ሮጠው ያሸነፉት፡ ሀገራቸውን የአሸናፊነት ምልክት ለማድረግ ነው፡፡

ከአበበ ቢቂላ የአሸናፊነት ታሪክ የተነሳ፣ የአትሌቲክስ የማሸነፍ መንፈስ፡ ሲድኒ ላይ እስካሁንም አቻ ወዳላገኘ ከፍታ ተንደረደረ፡፡ ሚሊዮኖች በሲድኒ ገድል ከጫፍ ጫፍ ከማንባታቸው ቀድሞ… ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር ካደረገችው ደም አፋሳሽ ጦርነት እና ባጋጠማት ረሀብ  ከተፈጠረባት ድብታ በሲድኒ ኦሊምፒክ ድል ፈገግ ከማለቷ አስቀድሞ… የአሊምፒክ ልዑክ ቡድኑም ወደ አውስትራሊያ ከማቅናቱም አስቀድሞ… ብዙ ነገሮች ሆነዋል፡፡

ጂም ዴኒሰን “The Greatest” ብሎ ባሳተመው የኃይሌ ገብረስላሴ ታሪክ ላይ ይህ ተጽፏል፡፡ ‹‹ከሲድኒ ኦሊምፒክ በፊት የነበረው ጊዜ ለእኔ እጂግ ከባዱ ጊዜ ነው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ ያጋጠመኝን ከፍተኛ ጉዳት ይዤ ወደ ሲድኒ መጓዝ አለብኝ? ወይንስ ራሴን ማግለል አለብኝ? ባህሪዬ ሁሉ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ማንንም ማግኘት ማየት አልፈልግም፡፡ ቁጡ ሆኛለሁ፣ እነጫነጫለሁ፣ ያለምንም ምክንያት ከባለቤቴ አለም ጋርም እጣላለሁ፡፡

ለምንም ነገር ትእግስት የሌለው ሰው ሆኛለሁ፡፡  በመጨረሻ በቃ! ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ ራሴን በደንብ ማየት እና ወደ ሲድኒ መሄድ አለመሄዴን ማሳወቅ አለብኝ፡፡ ያንን ጠዋት እና የትራክ ልምምዴን በደንብ አስታውሰዋለሁ፡፡ ሞቅ ያለ ጠዋት ነበር ሁሉም የሲድኒ ተጓዥ አትሌቶች ተገኝተዋል፡፡ ለሌላ ፈታኝ ልምምድ እየተዘጋጁ ነበር፤ ወደ መጨረሻ ከሚደረጉ ልምምዶች አንዱ ነው፡፡  ዶክተር ሜዳው ላይ ሆኖ እኔ ሳሟሙቅ እየተመለከተኝ ነው…  ህመሜን አሸንፌ ከቡድኑ ጋር እንድጓዝ በተስፋ እየጠበቀኝ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ትንሽ ካሟሟቅኩ በኋላ የዝላይ ውድድር የሚከናወንበት ቦታ ላይ ቁጭ ብዬ የመሮጫ ስፓይኬን አጠለቅኩ፡፡ ጉዳቴ ምን ያህል እንደሆነ ስፓይኬን አድርጌ ማወቅ አለብኝ፤ እግሮቼ ለመሮጥ ተዘጋጁ …ስቆም ጥሩ ስሜት ተሰማኝ፣ ለመሮጥ እና ህልሜን ለመኖር ተዘጋጀሁ፡፡

50 ሜትሮችን እንደሮጥኩ ግን ሁሉም ነገር እንዳበቃ አረጋገጥኩ፡፡ ህመሙ በጣም ከፍተኛ ነበር፤ ሲዲኒ ሄጄ ማጣሪያ እና ፍጻሜ ሁለት 10000 ሜትሮች እንዴት መሮጥ እችላለሁ? ለዚያውም በአራት ቀናት ልዩነት፡፡ ወሰንኩ! ወደ ሲድኒ እንደማልሄድ ወሰንኩ፡፡ ዶክተር ወልደመስቀልን ነገርኳቸው፤ የቡድን አጋሮቼን፣ የእኔ ነገር አብቅቷል መልካም እድል ለእናንተ አልኳቸው፡፡

ጆስ ሔርመንስን እና አንቶንን ወደ ሆላንድ ደውዬ ነገርኳቸው፣ ቤት ስገባ ለዓለም ነገርኳት፤ ከወቅቱ የስፖርት ኮሚሽነር ጋር ቀጠሮ አስይዤ ቢሯቸው ድረስ በመሄድ ወደ ሲድኒ እንደማልሄድ ነገርኳቸው፡፡››

ይህ አስጨናቂ ህመም እና ጊዜ ታልፎ ነው እንግዲህ የኃይሌ እና የፖል ቴርጋት ትንቅንቅ፣ ከምንጊዜም የአልሸነፍ ባይነት  የስፖርት ታሪኮች አንዱ የተወለደው፡፡

ቀጥለን የሲድኒ ሜዳሊያዎች የተገኙባቸውን ውድድሮች ተራ በተራ እናስታውሳቸው፡፡ ኃይሌ እግሩን አስሮ፣ ጥርሱን ነክሶ፣ ህመሙን ችሎ፣ የምንጊዜም ድንቁ አትሌት ከተባለበት እና ኢትዮጵያ ሀገሩን ካኮራበት የ10 ሺህ ሜትር ትንቅንቅ እንጀምራለን፡፡

(L-R) Girma Tolla, Haile Gebrselassie and Assefa Mezgebu

ኃይሌ ገብረስላሴ ከ ፖል ቴርጋት 10000 ሜትር

ኃይሌ ከኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጥያቄ ቀረበለት፡፡ በሯጭነትም ባይሆን ቡድኑን ለማበረታታት አብሮ እንዲጓዝ፡፡ “ኃይሌ ጫና ላሳድርብህ አልፈልግም፣ በሲድኒ መሮጥ አለመሮጥ ያንተ ውሳኔ ነው፤ ነገር ግን አንድ ነገር ከልቤ የምነግርህ ሲድኒ ከመጣህ እና ለመሮጥ ከወሰንክ አንትን የወርቅ ሜዳሊያ ከማምጣት የሚያግድህ ነገር አለ ብዩ አላስብም” የኮሚሽነሩ የመጨረሻ መልእክት ነበር፡፡

ኃይሌ ሶስት ነገሮችን አሰበ፡  ጉዳቱን፣ ከጉዳቱ ጋር ቢሮጥ እስከወዲያኛው የሚያመጣውን ተጽዕኖ፣ በመሮጡ የሚደርስበት ጉዳት በቀጣይ ህክምና የሚፈውሰው መሆን እና አለመሆኑን፡፡ …. አርብ መስከረም 12 ቀን 1993 ዓ.ም የ10ሺህ ሜትር የሲድኒ ኦሊምፒክ ማጣሪያ ሊከናወን ሯቾች መሙ ላይ ተደርድረዋል፡፡ ንጉሱም ከህመሙ ጋር በውስጡ እየታገለ በቦታው ነበር፡፡

አዲዳስ ለኃይሌ ለየት ያለ ጫማ ሰራለት፣ ልምምዱንም በጣም በቀላሉ ሰራ፡፡ ከፍተኛ ህመም እየተሰማውም ቢሆን ማጣሪውን 27፡50.01 በሆነ ጊዜ አሸንፎ ለፍጻሜው አለፈ፡፡ ነገር ግን ለሁለት ቀናት ከአልጋው መነሳት አቃተው፡ ምግቡም ክፍሉ ድረስ ይሄድለት ነበር፡፡

ፍጻሜው በኃሌ አንደበት እንዲህ ይታወሳል “የመጀመሪያዎቹ ዙሮች ትንሽ አደናጋሪዎች ነበሩ፡፡ ከመሪዎቹ ጋር ተጓዝኩ ብዙም አልተቸገርኩም፡ 13፡05 ላይ የርቀቱን ግማሽ ሮጥን፡፡ ዘጠኝ ነን 6000ሜትር ላይ እንዲያውም ለጊዜውም ቢሆን መራሁ ጉዳቴም አልተሰማኝም፡፡ ረሳሁት፡፡ ስድስት ዙር ሲቀር ግን እጂግ መጥፎ ስሜት ተሰማኝ፡ ጉዳቴ ያለበት ቦታ ሳይሆን፣ ትንፋሼ ሲዛባ ታወቀኝ፣ ጉልበቴ ዛለ እና ሰውነቴ ከበደው፡፡   ሃሳብ ገባኝ … ማሸነፍ አልችልም፣ ልምምድ አቋርጫለሁ፣ ለማሸነፍ ጥንካሬ የለኝም ማለት ጀመርኩ በውስጤ፡፡ በሩጫ የውድድር ታሪኬ ለመጀመሪያ ጊዜ አቋርጦ ስለመውጣት አሰብኩ፡፡”

ደወሉ ተደወለ፤  ቴርጋት ከፊት አለ፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ጆን ኮሪር፣ አሰፋ መዝገቡ ፓትሪክ ኦቩቲ ሁሉም አሉ፡፡ ኃይሌ ሀሳቡን ቀይሯል ‹‹ይቻላል!›› የሚለው መርሁ የህመም እና የማቋረጥ ስሜቱን አጥፍቶታል፡፡ የመጨረሻው ትንቅንቅ፣ ቴርጋት አምጧል፡፡ ኃይሌ ከጀርባው አለ፡፡ አንድም የተቀመጠ ተመልካች የለም፤ ኢትዮጵያውን በጭንቀት እያማጡ ነው፡፡ ኬንያውን በቴርጋት መቅደም መደሰት ጀምረዋል፡፡

እግር ለእግር፣ ትክሻ ለትክሻ ተያይዘው ወደ መጨረሻው መም እየተጠጉ ነው፡፡ ሁኔታውን በግሩም ሁኔታ እያስተላለፈ የሚገኘው ኮሜንታተር በድንቅ ሁኔታ ፍልሚያውን እያጀበው ነው፡፡ አለመሸነፍ እና ወርቅ ወይንም ደግሞ በሽርፍራፊ ሰዓት እጅ ሰጥቶ ሌላ የኦሊምፒክ ብር ማግኘት የኃይሌ እና ቴርጋት እጣ ፈንታዎች ናቸው፡፡

ኃይሌ የህይዎት ዘመኑን ትግል፣ ዕልህ እና ቆራጥነት አሳዬ፤ ኃይሌ ለምን የርቀቱ ድንቅ አትሌት እንደሆነ አስመሰከረ፡፡

ከ20 በላይ ሬከርዶችን የሰበረበትን ምክንያት አሳዬ፡፡ ሰዓቱ የኃያልነት፣ የይቻላል፣ የተግባሪነት እነ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነት ማሳያ ሆነ፡፡ “Gebrselassie Beaten Tergat Again!” (ገብረስላሴ ቴርጋትን እንደገና አሸነፈው) አለ ኮሜንታተሩ፡፡

ኢትዮጵያውያን በሀሴት የሚጨብጡት ጠፋቸው፡፡ ያንን ውድድር አንድ ውድድር ብቻ ማለት አሁንም ድረስ ይከብዳቸዋል፡፡ አሰፋ መዝገቡ የነሀስ ሜዳሊያ ጨምሮ የሲድኒን ደስታ ወደ ሌላ ምዕራፍ መራው፡፡

ደራርቱ ቱሉ – 10000ሜ ሴቶች

10ሺህ ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያ ውድ እና ድንቅ ልጆቿን ያሰለፈችበት ልላኛው ውድድር ነበር፡፡ አመታትን አመታት ቢተኩ በማንኛውም መልኩ የማይደበዝዘውን የታሪክ ምእራፍ ከሀገሯ አልፎ ለመላ ጥቁር አፍሪካውያን የከፈተችው ደራርቱ ቱሉ በዚህ ቡድን አለች፡፡

የባርሴሎናዋ ፋና ወጊ በአትላንታ አልተሳካላትም ነበር፡፡ በሲድኒ ደግሞ ወልዳ ተነስታ ወደ ኦሊምፒክ ስላቀናች ጥርጣሬዎች አሉ፡፡ በአልም ሻምፒዮና እና በሀገር አቋራጭ ውድድሮች ኢትዮጵያን እያኮሩ  የመጡት ብርሐኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚም አሉ፡፡ ነገር ግን የያኔው 10ሺህ ሜትር የእጅግ ድንቅ ሯጮች ፉክክር ነበር፡፡

ፓውላ ራደክሊፍ፣ ቴግላ ላሩፔ፣ ኤሊና ማየር፣ ሶኒያ ኦ ሱሊቫን እና ሌሎች ድንቀ ሯጮች የሞሉበት እና አሸናፊው ማንም ሊሆንበት የሚችል ውድድር ነበር፡፡

ውድድሩ ተጀመረ፡፡ ከፊቷ ፈገግታ፣ ከስብዕናዋ አሸናፊት  የማይጠፋባት ኮከብ ደራርቱ ቱሉ፣ በተለይ ከጌጤ ዋሚ ጋር በመሆን ለውድድሩ ዝግጁ መሆኗን የሚያስመሰክር ሩጫ ማድረግ ጀመረች፡፡ እዚህ ከባርሴሎና በኋላ በእያንዳንዱ ልብ የገባቸውን የደራርቱን አጨራረስ ለማየት ህዝቡ እየተቁነጠነጠ ነው፡፡ ደወሉ ተደወለ፡፡ የሲድኒ የሴቶች 10ሺህ ሜትር የመጨረሻ ደቂቃዎች፣ ፈታኙም ሰዐት ደረሰ፡፡

የኢትዮጵያ የሴቶች የ10ሺህ ሜትር ድል በኦሊምፒክ የደራረቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ወርቅም የእሷው ነው፡፡ ግን ይህንን ትግል የበዛበት ውድድር ማሸነፍ አለባት፡፡ የደራርቱ እግሮች ወደ ፊት ተስፈነጠሩ፡፡ ጌጤ እየተከተለቻት ነው፡፡ የሲድኒ ኦሊምፒክ የመሮጫ ትራክን በእርግጠኛነት የድል ስሜት እየረገጠች ደራርቱ ቱሉ ወደ ፊት ገሰገሰች፡፡ የብር ሜዳሊያውም በእርግጠኝነት የኢትዮጵያ ነው፡፡ ጌጤ ዋሚ በልበ ሙሉነት ደራርቱን ትከተላታለች፡፡

30 ደቂቃ 17.49 አትላንታ ላይ በሚያስቆጭ ሁኔታ ያለፋትን የ10ሺህ ሜትር ድል ሲድኒ ላይ ወልዳ ተነስታ፣ የኦሊምፒክ ክብረወሰንን ጭምር በማሻሻል ደራርቱ ቱሉ አሸነፈች፡፡ ጌጤ ዋሚ 30፡22.48 በመግባት የብር ሜዳሊያውን አገኘች፡፡

ፋና ወጊዋ ኮከብ ደራርቱ ቱሉ ለኢትዮጵያውያን ተተኪ አትሌቶች የድል መስመር መጥረጓን አረጋገጠች፡፡  በሲድኒም ፈታኙን የ10ሺህ ሜትር ውድድር አሸነፈች፡፡

ስለ ደራርቱ የሲድኒ ድል ስናወራ፡ በሜዳሊያው መረከቢያ መድረክ ላይ የሀገሯ የኢትዮጵያ ስም ተጠርቶ፣  መዝሙሯ በስቴዲየሙ ተከፍቶ፣ ሰንደቋ ከሀገራት ሁሉ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በፊቷ ይወርድ የነበረውን የደስታ እንባ ማንም አይዘነጋውም፡፡ ከልብ የመነጨ፣ መላው ኢትዮጵያውንን በየቤታቸው በእንባ ያራሰ የሀገር አክብሮት ድንቅ ስጦታ ነበር፡፡

ደራርቱ፡ ራሷን ኢትዮጵያን ትመስላለች፡ ብሎ ትውልድ እንዲገልጻት ያደረገ ታላቅ አክብሮት!

ገዛኸኝ አበራ – ማራቶን

ማራቶኑም አስገራሚ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር በ1968 ሜክሲኮ ላይ በማሞ ወልዴ ማራቶንን አሸንፋለች፡፡ ከዚያ በኋላ ያንን ጥያቄ የሚመልስ ጀግና እየፈለገች 32 ዓመታት፣ ስምንት ኦሊምፒኮችን አሳልፋለች፡፡ ወደ ሲዲኒ የተላከው የማራቶን ቡድን ገዛኸኝ አበራን፣ ተስፋዬ ቶላ እና ስምረቱ አለማየሁን ይዟል፡፡

ገዛኸኝ አበራ ገና የ12 ዓመት ታዳጊ እያለ፡ የክፍል መምህሩ አበበ ቢቂላ ስለሚባል … በባዶ እግሩ 42 ኪሎ ሜትር ሮጦ ስላሸነፈ የሀገሩ ጀግና ሯጭ ይነግሩታል፡፡ ‹‹አንድ ሰው በባዶ እግር 42 ኪሎ ሜትር ሮጦ ያሸንፋል?››   ለገዛኸኝ ጥያቄ ነበር፡፡ ያንን ገድል የፈጸመው ጀግና ደግሞ በልቡ ታትሟል፡፡

ከአስር አመታት በኋላ ገዛኸኝ በሲድኒ ኢትዮጵያን የሚወክለው የማራቶን ቡድን አባል ሆኗል፡፡ ከልምዱ አንጸር ግን ማንም አሸናፊ ይሆናል ብሎ አልጠበቀውም፡፡ ኬንያዊው ኤሪክ ዋርድ፣ እንግሊዛዊው ጆን ብራውን፣ ደቡብ አፍሪካዊወ ሔንሪክ ራማላ፣ ጣሊያናዊው ስቲፋኖ ባልዲኒ አለዚያም ሞሮኳዊው አብድልቃድር ባሉበት ኢትዮጵያዊው ብዙ አልተገመተም፡፡

በነፋሻማው የሲድኒ ጠዋት ማራቶኑ ተጀመረ፡፡ ከ19 ማይል በኋላ ገዛኸኝ በውድድሩ ከፍተኛ ፈተና አጋጠመው፡፡ ከአንድ ሌላ ሯጭ ጋር ተጋጭቶ ወደቀ፡፡ ጉልበቱንም ጉዳት አጋጠመው፡፡ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኦሊምፒክ ማራቶን ድል ጥያቄ በሲድኒ የሚመለስ አይመስልም ነበር፡፡

ወድቀው ለመነሳት፣ ፈተናን ለማሸነፍ፣ ለሀገራቸው ዋጋ ለመክፈል ኢትዮጵያውያን ጥርሳቸውን ነክሰው ይሞክራሉ፡፡ ገዛኸኝ ከወደቀበት ተነሳ፡ ትንሽ ህክምና ብቻ አድርጎ ወደ ፊት ገሰገሰ፣ ቀስ በቀስ የወድድሩ መሪወችን ደረሰባቸው፡፡ ጥቂት ማይል እንደቀረም ከኬንያዊው ኤሪክ ዋርድ እና ከሀገሩ ልጅ ተስፋዬ ቶላ ጋር የመጨረሻውን ምዕራፍ ይጠባበቅ ጀመር፡፡

የመጨረሻው ሰዐት ደረሰ፡፡ አስቀድሞ ኤሪክ ሮጦ ለማሸነፍ ሞከረ አልቻለም፤ ገዛኸኝ አብሮት ሮጠ፡፡ ገዛኸኝ አበራ… ብዙ ያልተገመተው አትሌት ወደ ትራኩ በአሸናፊነት ተንደረደረ ኤሪክን በ20 ሰከንድ ቀደመው፡፡ 2፡10፡11 ኢትዮጵያ የማራቶን ሯጮች ምድር፡፡ ኢትዮጵያ ለ3 ጊዜ ማራቶንን በተከታታይ በሶስት ኦሊምፒኮች በአበበ ቢቂላ አና ማሞ ወልዴ አሸንፋ ብቸኛ የሆነችው ምድር፡ ሌላ የማራቶን ጀግና ፈጠረች፡፡

ኤሪከን ተከትሎ በሶስተኝነት ውድድሩን ያጠናቀቀው ተስፋዬ ቶላም የኢትዮጵያን የሲድኒ ኦሊምፒክ ድል ወደ ሌላ የደስታ ጫፍ የመራ ድል አስመዘገበ፡፡ በመጨረሻም ማራቶንን አሸነፍን፡፡

ገዛኸኝ ውድድሩ ካለፈ በኋላ አንድ አስገራሚ ነገር ተናገረ ያንን ድል ለመግለጽ ቃላት አይኖረኝም ልዩ ነበር፡፡ ግን አንድ ትንሽ ቅር ያለኝ ነገር ነበር፡፡ ውድድሩን ካሸነፍኩ በኋላ ድል የማከብርብትን የደስታ ዙር ስሮጥ፡ ራሴን በትልቅ የሀገሬ ሰንደቅ ዓላማ ጠቅልዬ መሮጥ ነበር የፈለግኩት፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ግን ትንሽ ሰንደቅ ዓላማ ነበር ያገኘሁት፡፡”

እግሩ ተጎድቶም ያሸነፈው ገዛኸኝ፣ በትንሽ እድሜው ማራቶንን በማሸነፍ ከ1932 በኋላ ቀዳሚ ሆነ፡፡ በታዳጊነቱ ሰምቶ የተደመመበትን የአበበ ቢቂላን ተግባር ራሱ ፈጸመ፡፡ ኢትዮጵያ በሲድኒ ሰማይ አንጻባረቀች!

ሚሊዮን ወልዴ – 5000ሜ

ከሞስኮው የምሩጽ ይፍጠር ድል በኋላ 5000ሜ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ርቋል፡፡ ወደ ሲድኒ ከተላከው የ5000ሜ ሯጮች ቡድን ወርቅ ይገኛል ብለው በልበ ሙሉነት የሚናገሩት የቡድኑ ዋና አሰልጣኙ ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) ብቻ ይመስላሉ፡፡

በሲድኒ ኦሊምፒክ ወቅት ዝግጅቱን በቅርበት የመሩት የወቅቱ የስፖርት ኮሚሽነር አቶ መላኩ ጴጥሮስ ስለ ወልደ መስቀል ኮስትሬ በሰጡት ምስክርነት ላይ አንድ ነገር ያስታውሳሉ፡፡ “ወደ ሲድኒ ከመጓዛችን በፊት ዶ/ር ወልደመሰቀልን አንድ ጥያቄ ጠየቅነው፡፡ በሲድኒ  ኢትዮጵያ ወርቅ ልታገኝባቸው የምትችላቸውን ውጤቶች በወረቀት በቅድመ ግምት ሰርቶ እንዲያመጣ፡፡

በወንዶች እና በሴቶች 10ሺህ እንዲሁም በወንዶች 5ሺህ እናሸንፋለን አለን፡፡ ያኔ ምንም ያልጠበቅነውን የወንዶች 5ሺህ ሜትር ድል በሚሊዮን ወልዴ ወርቅ እንደምናገኝበት ገምቶ በኋላም ውጤቱ ተሳክቶ አስደምሞናል፡፡›› የሲድኒ ኦሊምፒክ ያልተጠበቀ ግሩም ድል 5000 ሜትር ወንዶች፡፡

አልጄሪያዊው ሳይፊ፣ ሞሮኳዊው ብራሂም ላህላፊ፡ አለዚያም የብዙ ልምድ ባለቤቱ ፊጣ ባይሳ ወይንም ኬንያውያኑ ሪቻርድ ሊሙ እና ጁሊየስ ጊታሂ ለአሸናፊነት የታሰቡበት ውድድር ነበር፡፡ ሚሊዮን ወልዴ በፍጹም ያልተጠበቀው ወጣቱ አትሌት ነው፡፡

ሚሊዮን 200 ሜትር ሲቀር በልበ ሙነት ወደ ፊት ተንደረደረ፡ ለ20 ዓመታት ርቆን የነበረውን 5000ሜ ወርቅ 13፡35.48 በመግባት፡ የተጠበቁትን ሳኢድ ሳይፊ እና ብራሂም ላህላፊን አስከትሎ አሸነፈ፡፡ የሀገሩን ሰንደቅ አላማ ይዞ በእጆቹ የማይዘነጋ ምልክት አሳይቶ፡ ለኢትዮጵያውን ይሔ ድል የእናንተ ነው የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡፡

ኢትዮጵያውያን መቼም ከማይዘነጓቸው፣ የሲድኒ ተሳትፎን ካገነኑ ውጤቶች አንዱ ሆኖም ተመዘገበ፡፡

እንደ መውጫ

ኢትዮጵያ የመጀመሪ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ባደረገችበት ምድር አውስትራሊያ፡ በጀግኖች አትሌቶቿ ትጋት እና ሀገር መውደድ፡ የማይቻል የሚመስለው ተቻለ፡፡ ህመማቸውን እና ስቃያቸውን ተቋቁመው የምንጊዜውንም ድንቅ ታሪክ አስመዘገቡ፡፡

ወድቀው ተነስተው፡ የአሸናፊነትን የታሪክ አደራ አስቀጠሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ዳግም የጥቁር ህዝብ አብነት መሆኑን አሳዩ፡፡

ሲድኒ …  የኢትዮጵያውን ትልቁ የኦሊምፒክ ውጤት!


ስለ ጸሀፊው


ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ አመታት በስፖርት ጋዜጠኛነት እና ልዩ ልዩ ሀላፊነቶች፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በፋና ቴሊቪዥን በአቅራቢነት እንዲሁም በብስራት ኤፍኤም 101.1 በሳምንት ለሶስት ቀናት የሚተላለፈው “ትሪቡን ስፖርት” ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *