በ ሳሙኤል ስለሺ – የስፖርት ባለሞያ – ለልዩ ስፖርት

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ፅሁፎች በእግር ኳስ ቡድን ግንባታ ላይ ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳቦችን በማስቀመጥ በኢትዮጵያ እግር ኳስ (በተለይም) በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሚታዩ ነባራዊ ትንተናዎችን እና የዝውውር ግድፈቶችን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በጥቅሉ እግር ኳስ ተደጋጋፊያዊ የቡድን ስፖርት በመሆኑ የተጨዋቾች ውህደት አስፈላጊ እንደሆነ እና ይህም ከሚሳካባቸው መሰረታዊ ነጥቦች መሀከል የተጨዋቾች እርጋታ እንዲሁም የቡድን ወጥነት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛ የሆነ የተጨዋቾች ሽክርክሮሽ በሐገራችን እግር ኳሱ ውስጥ መኖሩን ተከትሎ የተጨዋቾች እድገት ሲገታ፣ የቡድኖች ጥንካሬ ሲሸረሸር፣ የሊጎች ድምቀት ሲከስም፣ የብሄራዊ ቡድን ጥንካሬ ሲጎዳ በጥቅሉ የሐገር እግር ኳስ ሲወድቅ እየተመለከትን እንደሆነ ያለፉት ሁለት ፅሁፎች ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

የዛሬው ሶስተኛ ክፍል ከእግር ኳስ ቴክኒካል ጉዳዮች አንድ ደረጃ ከፍ በማለት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን በአሁን ጊዜ እየታየ ያለው የተጫዋቾች ዝውውር ከሐገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር፣ ከስፖርት ፖሊሲው አኳያ፣ ከእግር ኳስ ስትራቴጂክ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ረገድ ትንታኔ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡

የኢ-ፖሊሲያዊ ልማዶች ማቆጥቆጥ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ግራ አጋቢ፣ የተሸፋፈነ፣ ‹‹ለምን?›› እና ‹‹እንዴት?›› ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሚያዳግቱ አሰራሮች ያሉበት መሆኑን ተከትሎ ስህተቶቹ አይን ያወጡ እና ፊት ለፊት ያገጠጡ ናቸው፡፡

መንግስት እግር ኳስ አንዱ እና አስፈላጊው የልማት መስመር ነው በማለት ወደ ኢንዱስትሪው መምጣቱ፣ ዘርፉን በፋይናንስ መደገፉ፣ ሴክተሩን ማገዙ፣ ገንዘብ እና ሐብትን ኢንቨስት ማድረጉ የሚበረታታ እና ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የበጀት አመዳደቡ ከስፖርት ልማት ፍልስፍና እና ከስፖርት ፖሊሲያችን ጋር ሲጋጭ ይስተዋላል፡፡ አሁን አሁን በእጅጉ ስር እየሰደደ የመጣው የክለብ አደረጃጀት እና የፋይናንስ አጠቃቀም እግር ኳሳችንን የማያሳድግ፣ ከፖሊሲያችን ጋር የሚጋጭ ይበልጡንም ከሐገሪቱ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ጋር የሚቃረን ነው፡፡

የፈረደበት እና ዘወትር ስሙን የምናነሳው፣ ብዙ ጭብጦችን የያዘው፣ ነገር ግን እኛ ባለሙያዎች አይደለንም የፃፈው መንግስት እንኳን ከቁብ በማይቆጥረው የ1990ው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ፖሊሲ፤ በፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫ 2.1 ላይ ‹‹የስፖርት አጠቃላይ እንቅስቃሴ አደረጃጀት እና አመራር ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ይደረጋል›› በማለት አስቀምጦ በተጨማሪነት በተራ ቁጥር 4.1 ላይ ‹‹የሐገሪቷን ስፖርት በበላይነት የመምራት ስልጣን የሕዝባዊ አካሉ ይሆናል›› ይላል፡፡ ‹‹ህዝባዊ…ህዝባዊ….›› የሚለው ጭብጥ ተደጋግሞ ስለተወራ መሰላቸትን ፈጠረ እንጂ ትልቅ መልእክት ያለው ፍልስፍና ነው፡፡ ጭብጡ በአንድ አገር ስፖርት ልማት ላይ የመንግስት ሚና የማገዝ እና የመደገፍ እንጂ መሪ ተዋናይ የመሆን አይደለም እንደማለት ነው፡፡

ይህንን ፍልስፍና ወደ እግር ኳስ እናምጣውና ‹‹ማገዝ እና መደገፍ ከመሪ ተዋናይነት በምን ይለያል?›› የሚለውን እንመልከት፡፡ የክልል መንግስታት፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ ክፍለ ከተሞች እና የመንግስት ተቋማት ሚና ክለቦች ሕዝባዊ እንዲሆኑ እና እራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ በጊዜ ሂደት ‹‹ራስ መር›› አደረጃጀት ያላቸውን ክለቦችን መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ከማድረግ አንፃር የመንግስት ቀዳሚ ሚና ክለቦች ቋሚ ሐብቶችን እንዲያፈሩ ማስቻል፣ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ሕዝቦች ተደራጅተው ክለቡን እንዲመሩት ማድረግ ነው፡፡

ለምሳሌ የአንድ ክለብ ባለቤት እና አስተዳዳሪ የሆነ አንድ የከተማ መስተዳድር የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደ አቅሙ የውድድር ስቴዲየሞችን ለክለቡ (ለከተማው አላልኩም) መገንባት፣ የልምምድ ስፍራዎችን አዘጋጅቶ መስጠት፣ የማሰልጠኛ ማዕከላትን አቅም በፈቀደ ሰርቶ ማስረከብ፣ ክፍት የግንባታ መሬቶችን መስጠት፣ ክለቡ የባንክ ብድሮችን  የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸትና እንደ መንግስት ዋስ ሆኖ የመቅረብ፣ አማራጮችን በማየት የንግድ ሕንፃዎችን /ሆቴሎችን/ ጂምናዚየሞችን መገንባት፣ ከዚህ በፊት ብዙ ክለቦች እንዳደረጉት አውቶቡሶችን ገዝቶ መስጠት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ቋሚ ሐብቶችን የሚያስተዳደሩ አመራሮችን ክለቡ ከራሱ ደጋፊዎች የሚያገኝበትን ስልት በመቀየስ አመራርነቱንም ሆነ የፋይናንስ ምንጭነቱን ሕዝባዊ ማድረግ ነው፡፡

በአሁን ሰአት ያለው የክለብ አደረጃጀትም ሆነ የዕለት ተዕለት አሰራር ግን ከዚህ የፖሊሲ ፍልስፍና አንፃር ጋር የሚጣረዝ ሆኖ መንግስት ተጨዋች እያስፈረመ፣ ማልያ እየገዛ፣ ሾርባ እየቀቀለ፣ አልቤርጎ እየተከራየ፣ አበል እየከፈለ እና እጅግ ጥቃቅን የሚባሉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ እየገባ ክለቦች እራሳቸውን የሚችሉበትን አማራጭ ከመፍጠር ይልቅ እራሳቸውን እንዳይችሉ፣ ከመንግስት አመራሮች መዳፍ እንዳይወጡ፣ አንዳንዴም የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆኑ ባስ ሲልም የመንግስት ገንዘብ የማሸሺያ ቁልፍ ስትራቴጂ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡

ይባስ ብሎ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ መንግስት ‹‹ከአልሚነት›› ወደ ‹‹ሸማችነት›› የተቀየረ ከመሆኑ የተነሳ ሌሎች ህዝባዊ ክለቦችን በአቅም እየተፈታተነ፣ የገበያ ዋጋን እያናረ፣ በህዝባዊ ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ እየተሳተፈ እርስ በራሱ የሚጣረዝ፣ ከፖሊሲው ጋር የሚጋጩ አሰራሮች እና ባህሎች እንዲያቆጠቁጡ በር ከፍቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ሕዝባዊነት›› በእግር ኳሳችን ውስጥ ያቆጠቁጣል ማለት እጅግ ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡

ይህ የመንግስት ሚና መደበላለቅ በሌሎች የሐገሪቱ ዘርፎች ላይም የሚስተዋል እንደሆነ እና ሊገታ የሚገባው ቁልፍ የሐገሪቱ ችግር መሆኑን ‹‹መደመር›› በሚለው መፀሀፋቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹የኢኮኖሚ ሥርአቱ ስብራት መንስኤዎች›› በሚለው ምዕራፍ 12 ገፅ 174 ላይ እንደሚከተለው ገልፀውታል፡፡

‹‹የመንግስት ጉድለት በዋናነት መንግስት በገበያው ውስጥ ጣልቃ ሲገባ የሚያበላሻቸው ነገሮችን ይመለከታል፡፡ ሆኖም የመንግስት ጉድለትን ለጥጠን ስንመለከተው ሁለት ዐበይት መገለጫዎች ይኖሩታል፡፡ አንደኛው መንግስት በገበያው ውስጥ ከሚገባው በላይ ጣልቃ ሲገባ የሚከሠት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከመንግስት ዳተኝነት የሚመነጭ ሲሆን መንግስት ገበያው ጤናማ በሆነ ሁኔታ እንዲሄድ የሚጠበቅበትን ሐላፊነት መወጣት ሲሳነው የሚከሰት ነው፡፡ በድምሩ መንግስት በገበያ ውስጥ ገንቢ ባልሆነ መልኩ ጣልቃ ሲገባና በአንፃሩ ደግሞ የገበያ ጉድለትን ለማረም በመደበኛ ሁኔታ ሚናውን በአግባቡ መወጣት ሲያቅተው የሚከሠት የምርት እና የሀብት ድልድል መዛነፍ ችግር ነው፡፡››

ምንም እንኳን የኢኮኖሚ ተንታኝ ባልሆንም ከላይ ከመፅሀፉ የተወሰደው አንቀፅ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ኢኮኖሚያዊ መፋለስ ያሳያል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ስትራቴጂክ የእግር ኳስ ልማት

መንግስት ክለቦችን ሊያግዝበት የሚገባውን የልማት አቅጣጫ ትቶ በአንድ የውድድር አመት ግማሽ የቡድኑን ተጨዋቾች እያባረረ ሌሎች ተጨዋቾችን ደግሞ እየሸመተ መቀጠሉ በክለቦች የረዥም ጊዜ እድገት ብሎም ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ መጣሉ አይቀሬ ነው፡፡ አንድ አመት ሙሉ አሰልጥኖ፣ አጎልብቶ፣ አብልቶ፣ አጠጥቶ፣ ባለሙያ ቀጥሮ የተንከባከበውን ተጨዋች ሐምሌ ግም ሲል ‹‹ጨዋታ ፈረሰ፤ ዳቦ ተቆረሰ!›› በማለት በትኖ ለሌላ ግዢ እና ተመሳሳይ ስህተት ገበያ መውጣቱ የማታ ማታ ክለቡን አደጋ ላይ የሚጥለው እንደሆነ እሙን ነው፡፡

በመንግስት ስር የሚገኝ ክለብ ‹‹የመንግስት›› እንደመሆኑ ህልውናው በአንድ የመንግስት ባለስልጣን ይሁንታ ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን ይገደዳል፡፡ የዛሬ አመት ገደማ የመንግስት ለውጥ በተደረገ በማግስቱ የአዲስ አበባ መስተዳድር ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ቡድን ይፍረስ አይፍረስ›› የሚል ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ለዚህ እንደ ቅርብ ማስረጃ ልንወስደው እንችላለን፡፡ ከዚህ በዘለለ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የድርጅት ክለቦች ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ የተደረገው ጥረት አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ በወረዱበት ሳይመለሱ ቀርተው በዛው ሲፈርሱ ተመልክተናል፡፡ ለዚህም ከሚሊኒየም ወዲህ የፈረሱት ንግድ ባንክ (የወንዶች ቡድኑ)፣ አየር መንገድ፣ አየር ሀይል፣ ኪራይ ቤቶች፣ ሐረር ቢራ፣ ዳሽን ቢራ፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ አየር መንገድ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ጉና ንግድ፣ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ክለቦች እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ምንም እንኳን አሁን ያሉት የከተማ /የአካባቢ/ ክለብ በመሆናቸው ከድርጅት ይለያሉ የሚል መከራከሪያ ቢቀርብ እንኳን አሁን ያለው የፖለቲካ አሰላለፍ እና ፋሽን ጊዜው ሲያልፍበት አደጋ ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም፡፡

ይህ በተጨዋቾች ዝውውር፣ በደሞዝ እና በስራ ማስኬጃ የሚያልቀውን የህዝብ ገንዘብ በአግባቡ አለመጠቀማችንን ለማሳየት ፊታችንን 10 አመታት ወደ ኋላ አዙረን ሒሳብ እናወራርድ፡፡ በ2011 ዓ.ም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስጠናሁት ባለው ጥናት ላይ በተጠቀሰው አመት ብቻ 2.5 ቢሊየን ብር በእግር ኳስ ክለቦች በኩል እንደወጣ ይጠቁማል፡፡ ምን አልባት የዚህን አሀዝ ግማሽ በየአመቱ ለእግር ኳሱ ወጪ ተደርጓል ብለን ብናስብ በአጠቃላይ ባለፉት አስር አመታት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ውድድር የወጣው ገንዘብ 12.5 ቢሊየን ብር ይደርሳል፡፡ ይህም ባለፉት ዘጠኝ አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢ፣ በቃል ኪዳን እና በስጦታ ያሰባሰበውን ሐብት ያህል እግር ኳሱ ተጠቅሟል ማለት ነው፡፡

እግር ኳስን በወጉ ከያዝነው እና እንዳለው ሐገራዊ ፋይዳ ከዚህ በላይ ገንዘብ ቢወጣበት አይከፋም፡፡ ሆኖም ግን ከግጥሚያ፣ ከመሸናነፍ እና ከውድድር (እኔ ድግስ ነው የምለው) በዘለለ ባለፉት 10 አመታት በቋሚነት ክለቦቻችን ያቆሙልን ምን ልማት አለ? የተገነባ ማሰልጠኛ ማዕከል ስንት ነው? ደረጃውን የጠበቀ መለማመጃ ሜዳ ያለው ክለብ ምን ያህል ነው? ቋሚ የገቢ ምንጭ የፈጠሩ እነማን ናቸው? እግር ኳስን ተጫውቶ ሻዎር ወስዶ ከመለያየት በዘለለ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሐገራችን እግር ኳስ ጠብ የሚል ነገር የተደረገው ምንድን ነው? ችግሩ የመነጨው ከእውቀት፣ ከፋይናንስ ችግር፣ ከሰው ሀይል ድክመት ሳይሆን በቁልፍነት መንግስት ከተከተለው ኢ-ፖሊሲያዊ የልማት አሰላለፍ እና ከላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መፅሀፍ ላይ እንደተጠቀሰው ‹‹[መንግስት] በመደበኛ ሁኔታ ሚናውን በአግባቡ መወጣት [ስላቃተው] ነው››፡፡

ሰሞኑን የተለቀቀ እና በቶትንሐም ሆትስፐር የአምና ውድድር ላይ ተመስርቶ የተሰራ All or Nothing የተሰኘ ተከታታይ ፊልም የክለቡ ስራ አስኪያጅ ዳንኤል ሌቪ አዲሱን አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆን ከሰራተኞች ጋር ሊያስተዋውቋቸው ወደ ክለቡ የሰራተኞች ህንፃ ሊሊ ዋይት ሀውስ ይዘዋቸው ገቡ፡፡ በዚህ ህንፃ ውስጥም 600 የሚጠጉ የቢሮ ሰራተኞች ክለቡን እያንቀሳቀሱ እንደሆነ ስመለከት በእጅጉ ገረመኝ፡፡ እኔ ሐገር ግን የተለየ ነው፤ አራት እና አምስት የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ለራሳቸው ‹‹ኮሚቴ››፣ ሲያሻቸው ደግሞ ‹‹ቦርድ›› የሚል ስያሜ በመስጠት ሻል ሲልም አንድ ስራ አስኪያጅ እና ገንዘብ ያዥ መድበው ‹‹ክለብ›› ያንቀሳቅሳሉ፡፡ እኔ እንኳን በእድሜዬ ከማውቃቸው ውስጥ ወደፊት ለመራመድ የማይተጉት ብዙ ናቸው፡፡ ከክለቦቹ ይልቅ ግለሰቦቹ የሚያድጉበት እግር ኳስ ሩቅ እንደማይጓዝ የፈረሱት ክለቦች ምስክር ናቸው፡፡

ይህንን ፅሁፍ አንድ አይኑን ጨፍኖ ለሚያነብ ሰው ‹‹ቅናት የተጠናወተው››፣ ‹‹ምቀኝነትን ያዘለ›› በማለት ሊፈርጀው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የፅሁፉ እንድምታ ተጨዋቾች ከክለብ ክለብ እየዞሩ ለምን ጥሩ ብር ተከፈላቸው፣ ክለቦች ለምን ብዙ ብር ተበጀተላቸው የሚል ሳይሆን እድገቱ ሁለንተናዊ ሊሆን እንደሚገባ እና እንደተጨዋቾች ሁሉ ክለቦችም ሊያድጉ እንደሚገባ የሚያትት ነው፡፡ በአመት 2 ሚሊየን ብር የሚከፈላቸውን ተጨዋቾች ደረጃውን ባልጠበቀ የትምህርት ቤት ወይም የወረዳ እግር ኳስ ሜዳ ላይ የሚያሰለጥን ክለብ ልጆቻችንን፣ ገንዘባችንንም ይባስ ብሎም እግር ኳሳችንን እንደነጠቀን ነው የሚቆጠረው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ክፍያ ቀጣይነት እንዲኖረው እና ከታች የሚመጡትም ታዳጊዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የክለቦች ህልውና የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ክለቦች እስካላደጉ ድረስ እግር ኳሳችን ሊያድግ ስለማይችል ጥያቄው ከክለብ አስተዳደር አንፃር እንጂ ከተጨዋቾች ደሞዝ አኳያ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ለተጨዋቾች የተከፈለ ገንዘብ እዛው እግር ኳስ ውስጥ እንደገባ የሚቆጠር ሲሆን ተጨዋቹ ጥሩ ኑሮ መኖር ከጀመረ፣ ጥሩ መመገብ ከቻለ፣ በእግር ኳስ ህይወቱ ደስተኛ ከሆነ እራሱን እየጠበቀ እግር ኳስ ውስጥ ለመቆየት ስለሚተጋ መልሶ እግር ኳሱን ማሳደግ ይችላል፡፡ ይህንን የሚመለከቱ ሌሎች ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ኳስ ሜዳ መላክ፣ ልጆቻቸው ኳስ ተጨዋች እንዲሆኑ መፈለግ እና ማገዝ ስለሚጀምሩ እግር ኳሱ በማህበረሰቡ ውስጥ የበለጠ ተቀባይነትን እያገኘ ይሄዳል፣ ኢንዱስትሪው ይሰፋል፣ የአካባቢ አሰልጣኞች የስራ እድል ያገኛሉ፡፡

ችግሩ ያለው በተጨዋቾች ስም ገንዘብ ወጥቶ እግር ኳሱ ውስጥ ምንም ሚና ለሌላቸው ሰዎች ሲሰጥ እና ለእግር ኳስ የተበጀተ በጀት እግር ኳሳዊ እሴት በማይጨምሩ ሰዎች እጅ ውስጥ ሲወድቅ ነው፡፡

ሙስና እና የተጨዋቾች ዝውውር

‹‹ክለባችን በዝውውር መስኮቱ ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው፡፡›› የሚል ዜና በክለቦቹ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ማንበብ እና የመገናኛ ብዙሀን ላይ መስማት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹መጀመሪያ ዝውውሩ የተጨዋች ነው? ወይስ አለፍ ብሎ ሌሎች ነገሮችም አብረው ይዘዋወራሉ?›› የሚለው ነጥብ የጥያቄያችን ሁሉ ማጠንጠኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አንዳንዴ ደጋፊን፣ አንባቢን እና የስፖርት ቤተሰቡን በመናቅ እና ምንም እንደማናውቅ በመቁጠር በስመ ‹‹ዝውውር›› ሊያታልሉን ሲሞክሩ ማየት በእጅጉ ያበሳጫል፡፡ ከወራት በፊት የ6 ወር የተጨዋቾች ደሞዝ በዕግዚኦታ የከፈለ ክለብ ዛሬ ላይ ‹‹በዝውውሩ መስኮት በንቃት እየተሳተፍኩ ነው›› ማለቱ እጅግ ፌዝ ነው፡፡

ክለቦች እየተከተሉ ያሉት ቅጥ ያጣ የተጨዋቾች ዝውውር እግር ኳሳችንንም ሆነ ሐብታችን እንዲባክን እንዳደረገ እየታወቀ ለምን በዚህን ያህል ፍጥነት ሊስፋፋ ቻለ? ለምን ለመግታት አልተሞከረም? ሀላፊነት የሚወስድስ ለምን ጠፋ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልሱ ‹‹ዝውውሩ›› የተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን የገንዘብም ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ ስሌቱ ‹‹ወጪ ከሌለ፤ ገቢ የለም!›› የሚባለው የሙስና ስልት ነው፡፡

እግር ኳሳዊ ሙስና አለም አቀፍ ችግር ሲሆን አንዱ መገለጫው ደግሞ የተጨዋቾች ዝውውርን ማወክ /Bungs/ የሚባለው ነው፡፡ ይህ የሙስና አይነት በተጨዋቾች ዝውውር ወቅት የማይገባቸውን ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች መኖርን የሚያሳይ፣ እግር ኳሳዊ ባልሆነ ምክንያት ተጨዋቾችን ማዘዋወር፣ ክለቦችን ላልተገባ ወጪ መዳረግ እና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡

ኢትዮጵያ በ2019ኙ Global Corruption Index  መሰረት ከ199 ሐገራት 162ኛ ላይ እንደመገኘቷ መሰል ሙስናዎች ቢኖሩ ከሐገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሚጠበቅ ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ አጠቃላይ ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋ በመሆኑ እግር ኳሱ ውስጥ ቢታይ አይገርምም የሚል አስተሳሰብ ቢኖርም አሁን ያለውን የእግር ኳስ ሙስና ደረጃ መገምገም እና መሞገት አያስፈልግም ማለት ግን አይደለም፡፡ ስለዚህ ያለውን ነባራዊ የሙስና አቅም ለማየት እንሞክር፡፡

ባለፈው ሳምንት ከቀረበው አጭር የሁለት አመት የወፍ በረር ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ያለው የአንድ ክለብ የተጨዋቾች ዝውውር መጠን በአመት በአማካኝ 52.8 በመቶ ነው፡፡ ይህም አንድ ክለብ ካሉት 25 ተጨዋቾች መሀከል 13.2 ተጨዋቾቹን በአዲስ እንደሚተካ ያሳያል፡፡ እያንዳንዱ ክለብ በአንድ የውድድር መስኮት 13.2 ተጨዋቾችን ካስፈረመ 16 ክለቦች በጥቅሉ 211.2 የተጨዋቾች ዝውውር፣ የአዲስ ተጨዋቾች ውል እና የደሞዝ ስምምነት ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ በየአንዳንዱ ተጨዋች ዝውውር ጀርባ በአማካኝ አመታዊ የአንድ ሚሊየን ብር የደሞዝ ስምምነት አለ ተብሎ ቢታሰብ አጠቃላይ የሚኖረው አመታዊ የገንዘብ ዝውውር ከ211* ሚሊየን ብር ይበልጣል ማለት ነው፡፡

ከዚህ 211 ሚሊየን ብር ውስጥ ‹‹ተጨዋቾች ምን ያህል የፈረሙበትን እና የሚገባቸውን ገንዘብ ያገኛሉ?››፣ ‹‹ምን ያህሉ ጉዳይ መግደያ ሆኖ በማይገባቸው ሰዎች ኪስ ውስጥ ይገባል?››፣ ‹‹እነዚህ ከተጨዋቾች ውጭ የሚገኙ እና ያልፈረሙበትን የሚያገኙ ሰዎች እነማን ናቸው?›› የሚለውን እና ተያያዥ ጥያቄዎችን መመለስ ስንችል ብቻ የሙስናው፣ ሌብነቱ እና ስርቆቱ ደርዝ የት ድረስ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን በመፍታት አዳዲስ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የተቀየረ ገንዘብ ባልተቀየረ አሰራር ብዙም ፋይዳ አይኖረውም፡፡

እዚህ ላይ ክለቦቹ የመንግስት እንደመሆናቸው የሚባክነው ሐብት የህዝብ አባካኙም በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ሹመኞች (ኮድ-4)፣ በክለብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች (ኮድ-3) እንዲሁም በግል የሚንቀሳቀሱ አካላት (ኮድ-2) እንደሆኑ እግር ኳሱን በቅርበት ለሚከታተል ሰው አይጠፋውም፡፡ እነዚህን ‹‹የእግር ኳሱ ስር ቁማርተኞችን›› ነጥለን ማውጣ ካልቻልን የምንወደውን ስፖርት በቁማር ተበልተን ‹‹ከእለታት አንድ ቀን እግር ኳስ የሚባል ስፖርት በኢትዮጵያ ነበር›› እያልን ለልጆቻችን ተረት ማውራታችን የማይቀር ነው፡፡

  • የተጠቀሰው የገንዘብ አሀዝ ፀሀፊው በራሱ አረዳድ በምክንያታዊነት በመውሰድ ለማሳያ አቀረበው እንጂ ኦፊሴላዊ ቁጥር አድርጎ አልተጠቀመበትም፡፡

የተጨዋቾች ዝውውር እና ያልተረጋጋው የኢትዮጵያ እግር ኳስ – ክፍል ሁለት


ስለ ጸሀፊው


ሳሙኤል ስለሺ

ፀሀፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የስፖርት ስነልቦና እና የእግር ኳስ መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ሲሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡    

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *