በ ሳሙኤል ስለሺ – የስፖርት ባለሞያ – ለልዩ ስፖርት

ማስታወሻ: ቀጥሎ የተቀመጠውን  የዚህን ጽሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ሳያነቡ ይኄኛውን ክፍል ባያነቡት ይመከራል፡፡

የተጨዋቾች ዝውውር እና ያለ ባህሪው የተያዘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ – ክፍል አንድ

በክፍል አንድ ዘገባችን የእግር ኳስን ባህሪያትን በመለየት የቡድን ግንባታ ሳይንሳዊ ሒደቶችን ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ በፅሁፋችን ከቀረበው ንድፈ ሐሳባዊ ትንተና በመነሳት የቡድን እርጋታ (Team Stability) ለቡድን ግንባታ (Team Cohesion) ወሳኝነት እንዳለው በቀላሉ ለመረዳት ችለናል፡፡ ያልተረጋጋ እና የሚቀያየር ቡድን ሶስተኛው እና አራተኛው የቡድን ግንባታ ደረጃ ላይ የመድረሱ እድል እጅግ ጠባብ ሲሆን በአንደኛው እና በሁለተኛው ደረጃ ላይ ብቻ ሲዳክር እንዲቆይ ያስገድደዋል፡፡  በዚህ በክፍል ሁለት ጥንቅራችን በሐገራችን በተለይም በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሚታዩ የተጨዋቾች ዝውውርን ከአለም አቀፍ ዝውውሮች እና ሳይንሳዊ መርሆዎች አንፃር በመቃኘት እያስከተለ ያለውን ቴክኒካዊ ፈተናዎች እና እግር ኳሳዊ ኪሳራዎች ለመቃኘት እንሞክራለሁ፡፡

የቡድን እርጋታ በክለቦቻችን

በጥቅሉ የቡድን እርጋታ ሁለት አይነት መልኮች ሲኖሩት አንዱ ‹‹መጠነ አሁናዊ እርጋታ›› (Current Stability Index) ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ‹‹መጠነ ፊታዊ እርጋታ›› (Future Stability Index) በመባል ይታወቃሉ፡፡

አሁናዊ እርጋታ የሚባለው የአንድ ቡድን ተጨዋቾች እስከዚኛው የውድድር አመት ድረስ ምን ያህል አብረው ቆይተዋል የሚለውን የሚያሳይ ሲሆን ፊታዊ እርጋታ ደግሞ የአንድ ቡድን ተጨዋቾች ወደፊት ምን ያህል አብረው ለመቆየት ስምምነት ወይም ውል ፈፅመዋል የሚለውን የሚያመላክት ነው፡፡

በሁለቱ መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ያለ ሲሆን አሁናዊ እርጋታ የተጨዋቾችን መጠናናት፣ መናበብ፣ መላመድ፣ መመቻቸት አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን ፊታዊ እርጋታ ደግሞ ተጨዋቾች በቡድኑ ያላቸውን ተስፋ፣ ደስተኛነት፣ የረዥም ጊዜ እቅድ እና ሌሎችንም የሚገልፅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞነኛውን የቡናዎቹን የአቡበከርን፣ የሚኪያስ እና የአማኑኤልን የረዥም ጊዜ ኮንትራት የክለቡን ፊታዊ እርጋታ የሚጨምር ሲሆን ተጨዋቾቹ በክለቡ፣ በአሰልጣኙ፣ በጨዋታ ዘይቤው እና መሰል ነጥቦች አኳያ ያላቸውን ተስፋ፣ ደስተኝነት እና ምቾት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች አሁናዊም ሆነ ፊታዊ እርጋታ መጠን እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ለማወቅ ያለውን ሁኔታ ለሚከታተል ሰው ቀላል ነው፡፡ የፊታዊ እርጋታ መጠን በሚያስፈርሟቸው የአንድ ቢበዛ የሁለት አመት አጫጭር ኮንትራቶችን መሰረት በማድረግ፤ እንዲሁም አሁናዊ እርጋታ መጠንን ደግሞ በሚፈርሙት ተጨዋቾች ብዛት እና በሚለቁት ተጨዋቾች ከፍተኛ ቁጥር አማካኝነት ምን ያህል ትንሽ እንደሆነ ማወቅ ይቻላል፡፡

ይህንን በቁጥር እና በመረጃ ለመደገፍ ሲባል ለዚህ ፅሁፍ እንዲረዳ በሶከር ኢትዮጵያ ገፅ ላይ የሚገኙ የሶስት አመታት (2010ዓ.ም፤ 2011ዓ.ም እና 2012 ዓ.ም) የጨዋታ እለት ሪፖርቶችን በመቃኘት ለመነሻ የሚሆን ትንታኔ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ (በዚህ አጋጣሚ የሶከር ኢትዮጵያ ድረ ገፅ ፋይዳ ያለውን መሰል ስራዎች ለአመታት መስራቱን ከምስጋና ጋር ከልብ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡)

በጥቅሉ አስር ክለቦች ባለፉት ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን (የወረዱ እና ያደጉ ክለቦችን ሳያካትት) በድምሩ 423 ተጨዋቾችን ተጠቅመዋል፡፡ ይህ ማለት አንድ ቡድን በአማካኝ 42 ወይም 43 ተጨዋቾችን በሶስት አመታት ውስጥ በፔሮሉ ላይ አስፍሮ ተገልግሏል ማለት ነው፡፡

ከ2010ዓ.ም የውድድር አመት አንፃር በ2012ዓ.ም የነበረው የቡድኖች አሁናዊ እርጋታ በ ግራፍ-1 ላይ የቀረበ ሲሆን በአማካኝ አንድ ቡድን 73.16 ከመቶው ያልተረጋጋ ወይም የተቀየረ ቡድን ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህም በሁለት የውድድር አመት ውስጥ ከአራት ተጨዋቾች ሶስቱ ክለባቸውን ለቀው በአዳዲስ ተጨዋቾች ይተካሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ቁጥር ለድሬዳዋ ከተማ 87.50 ከመቶ፣ ለጂማ አባጂፋር 85.71 ከመቶ፣ ለፋሲል ከተማ 81.82 ከመቶ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቡና 80 ከመቶ በመሆን በከፍተኛ ደረጃ ሲመዘገብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ 57.69 ከመቶ በመሆን በአንፃዊነት በዝቅተኛ ደረጃ ተይዟል፡፡ ከአስሩ ቡድኖች አንፃር የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝቅተኛ ቢመስልም በሁለት አመት ውስጥ የቡድኑን ከግማሽ በላይ እንደቀየረ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ከላይ የቀረበው አሀዝ የሁለት አመት (የ2012ዓ.ም ቡድንን ከ2010ዓ.ም ቡድን) አንፃር የሚያሳይ ሲሆን የአንድ አመቱ (የ2012ዓ.ም ቡድንን ከ2011 ዓ.ም ቡድን) አንፃር እንዲሁ ከፍተኛ ሆኖ የተገኘ ሲሆን በአማካኝ የአስሩም ቡድኖች የዝውውር መጠን 48.33 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል (ግራፍ-2)፡፡ ይህ ማለት በአማካኝ እያንዳንዱ ክለብ 2011ዓ.ም ላይ ከነበረው ቡድን ግማሽ ያህሉን ተጨዋቾች በማሰናበት በ2012ዓ.ም በአዲስ እንደተካ የሚያሳይ ነው፡፡ በግራፍ ሶስት ላይ በቀረበው መሰረት ደግሞ የ2011ዓ.ም ቡድን ከ2010ዓ.ም ቡድን አንፃር ያለው አሁናዊ እርጋታ ከፍ ብሎ የተገኘ ሲሆን ቡድኖቹ በአማካኝ 57.27 በመቶ የቡድናቸውን ክፍል በአዳዲስ ተጨዋቾች አዋቅረዋል፡፡

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በወርሀ ኤፕሪል 2018 በታተመው እና በ27 የአውሮፓ ሐገራት ሊጎች ላይ በተሰራ የCIES Football Observatory ሪፖርት መሰረት የቡድን እርጋታ ከውጤታማነት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ተደርጎ የቀረበ ሲሆን ከ 2009-2017 ድረስ በነበረ መረጃ መሰረት  በጀርመን 31.7በመቶ፣ በፈረንሳይ 33.1በመቶ፣ በእንግሊዝ 35.6 በመቶ አሁናዊ አለመረጋጋት ሲታይ ከፍተኛው በሳይፕረስ 57.7 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህንን የስምንት አመት የአውሮፓውያኖቹን መረጃ ከእኛ የሁለት አመት አሀዝ ጋር ስናስተያየው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ (የወረዱ እና ያደጉ ክለቦችን ሳያካትት) 52.8 ከመቶ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ተጨዋቾችን ወደ ክለብ ማምጣት እና ማሰናበት በእግር ኳስ ቡድን ግንባታ ውስጥ ያለ እና የሚኖር ነገር ቢሆንም ቢያንስ ቢያንስ በውድድር አመቱ መጨረሻ የደረጃ ሰንጠረዥ በላይኛው ደረጃ ያጠናቀቁ ክለቦች ውጤታማ አመት አሳልፈዋል ተብሎ ስለሚታሰብ በቀጣዩ አመት የሚያደርጉት ማስተካከያ እና የተጨዋቾች ዝውውር አነስተኛ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ2010ዓ.ም የሊጉ ዋንጫ ባለቤት የነበረው ጂማ አባጂፋር በ2011ዓ.ም ዋንጫ የወሰደውን ቡድን 71.43 ከመቶ ቀይሮ ወደ ውድድሩ ሲመጣ እሱን ተከትሎ በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የቡድኑን 40ከመቶ ቀይሮ አዲሱን አመት ጀምሯል፡፡ ይህ የውጤታማ ቡድኖች የልውውጥ ባህል በ2012ዓ.ም ቀንሶ በ2011ዓ.ም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁት መቀለ ሰባ እንደርታ እና ፋሲል ከተማ የቡድናቸውን 31.82 ከመቶ ብቻ ቀይረው የአዲሱን አመት ውድድር ጀምረዋል፡፡

ይህንን አሀዝ ከላይ ከተጠቀሰው የአውሮፓውያኖች ጥናት ጋር ስናነፃፅረው የስፔን ሻምፒዮናዎች የ20.8ከመቶ፣ የጀርመን 22.4ከመቶ፣ የፈረንሳይ 28.9ከመቶ እንዲሁም የእንግሊዝ 30.7ከመቶ ከሻምፒዮናነት በኋላ የቡድን ለውጥ አድርገዋል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት በነበሩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ (ምንም እንኳን ሁለት አነስተኛ ቁጥር ቢሆንም እና ለትንተና ቢያሻማም) ሻምፒዮናዎች ጂማ አባጂፋር እና መቀለ ሰባ እንደርታ በጋራ በአማካኝ የ51.63በመቶ የቡድን ለውጥ አድርገዋል፡፡ ይህ ቁጥር ከሻምፒዮኖች መረጋጋት አንፃር ከአውሮፓ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ከሚገኘው የሰርቢያ ሻምፒዮኖች በ0.73 ይበልጣል፡፡ ይህ የሚያሳየው ከአውሮፓ የተለያዩ ሐገራት ሻምፒዮና ክለቦች አንፃር የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ሻምፒዮኖች ከፍተኛ ያለመረጋጋት እንደሚታይባቸው ነው፡፡ እዚህ ጋር የኢትዮጵያ ክለቦችን ከአውሮፓ ክለቦች ጋር ማወዳደር አይገባም የሚል ክርክር ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እየተወዳደረ ያለው አቅም፣ ብቃት ወይም ችሎታ ሳይሆን መርህ ከመሆኑ አንፃር ብዙም ችግር የለውም የሚል እምነት አለኝ፡፡

በጥቅሉ ከላይ የቀረቡት አኃዞች የሚያሳዩት በኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ክለቦች ውስጥ ያለው አሁናዊ መጠነ አለመረጋጋት ከፍተኛ እንደሆነ እና ‹‹ውጤታማ›› ተብሎ ሊገለፅ የሚችል አመት ያሳለፈው ክለብ እንኳን ከአመቱ መጠናቀቅ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ የቡድኑን ተዋፅኦ እንደሚቀይር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በክፍል አንድ ፅሁፋችን እንደቀረበው የቡድኑን ግንባታ ሒደት ወደ ኋላ እንደሚመልሰው እና በደረጃ አራት የሚገኘውን ‹‹እውነተኛ ቡድን›› ከመገንባት ይልቅ በደረጃ አንድ እና ሁለት በሚገኙት ‹‹ጊዜያዊ የስራ ቡድን›› ወይም ‹‹ሐሰተኛ ቡድን›› ውስጥ የመቆየት አዝማሚያን ያዳብራል፡፡ ይህ ደግሞ ተጨዋቾች ያላቸውን አውጥተው እንዳይሰጡ፣ ድክመታቸው እንዳይሻሻል፣ ሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጭ እንዳይግባቡ በአጠቃላይ ቡድኑ እና ክለቡ ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡

አለመረጋጋት እና ጉዳቶቹ   

በእድሜዬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ካየኋቸው ድንቅ ቴክኒካል ተጨዋቾች መሀከል አንዱ ዳዊት እስጢፋኖስ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ (ኳስ ሜዳ የሚባል ይመስለኛል) አይኑ በጨርቅ ታስሮ የጨርቅ ኳስ እንዲያንጠባጥብ እና የተለያዩ ኳሶችን ከተወሰነ ርቀት ላይ ወደ ጎል እንዲመታ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ ተጨዋቹ ላይ ያስተዋልኩት አካባቢን የማስተዋል አቅም (Space Perception)፣ ምስልን በጭንቅላት ቀርፆ የማስቀመጥ ችሎታ (Mental Image)፣ ኳስ ከእግር እና ከሰውነት ጋር ሲነካካ የሚፈጥረውን ግኑኝነት የመረዳት እና ውሳኔ የመስጠት ብቃት (Sensation) እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡

በጥቅሉ ዳዊት ላይ ያስተዋልኩት የአእምሮ ደረጃ (Cognitive Capacity) በእጅጉ አስደምሞኛል፡፡ ተጨዋቹ ተዘውትሮ የሚነሱበት ክፍተቶች እንዳሉ ሆኖ ያለውን ፀጋ ያህል ሐገሩን፣ ሕዝቡን፣ ክለቡን እና እራሱን በትልቅ ደረጃ ማገልገል ካልቻለበት ምክንያት አንዱ እና ዋንኛው ኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያለው ቅጥ ያጣ የተጨዋቾች ዝውውር ባህል እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ዳዊት እስጢፋኖስ ባለፉት 12 አመታት ውስጥ 8 ዝውውሮችን አድርጎ ለዘጠኝ ክለቦች ተጫውቷል (ደግሞ የተጫወተበት ክለብ እንዳለ ሆኖ)፡፡ ይህ ማለት የዳዊት አማካኝ የአንድ ክለብ ቆይታ 1 አመት ከስድስት ወር ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ቁጥር ከደጉ ደበበ፣ ሙላለም ረጋሳ፣ አዳነ ግርማ፣ ሳልሐዲን ሰይድ እና ሌሎች በክለባቸው ውስጥ ተረጋግተው ከቆዩ ተጨዋቾች ጋር ስናወዳድረው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

ተጨዋቾች ከአንዱ ክለብ ሌላ ክለብ ሲዘዋወሩ የጨዋታ ዘይቤ፣ የአየር ሁኔታ፣ የቡድን ታሪክ፣ የደጋፊዎች አቀራረብ፣ የህይወት ዘይቤ፣ የውድድርና የልምምድ ሜዳ፣ የቡድን ጓደኞች፣ የአስተዳደር፣ የሚዲያ ትኩረት እና የመሳሰሉትን ለውጦች ስለሚያተናግዱ የአቋም መውረድ በቀላሉ ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ለውጥ ተቋቁሞ አይደለም መሻሻል ወጥ አቋም ማሳየት እንኳን በእጅጉ ከባድ እና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በእነዚህ 12 አመታት ውስጥ ዳዊት 10 ከሚሆኑ የክለብ አሰልጣኞች ጋር ሰርቷል፤ ቢበዛ ደግሞ 225 (ድግግሞሹ እንዳለ ሆኖ) ከሚሆኑ ተጨዋቾች ጋር በአብሮነት ለአንድ ቡድን ተጫውቷል፡፡ ለአንድ ተጨዋች ይህንን ሁሉ የአሰልጣኞች ልውውጥ ተላምዶ፣ ከዚህ ሁሉ ተጨዋች ጋር በተግባርም ሆነ በማበራዊ ሁኔታ ተዋህዶ፣ የራሱን የጨዋታ ዘይቤ ለማሳደግ እንደሚቸገር እሙን ነው፡፡ በብዙ አሰልጣኝ ስር ያለፈ ተጨዋች እና እጅ የበዛበት ችግኝ አንድ አይነት ናቸው፤ አቅማቸውን አውጥተው የመፅደቅ እድላቸው የተዘጋም ባይሆን የጠበበ ነው፡፡

በተለይም ደግሞ እድሜያቸው ለጋ የሆኑ እና ገና አቅማቸውን አውጥተው ያላሳዩ ተጨዋቾች የዚህ ሁሉ ለውጥ መደራረብ እድገታቸው ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ችግኝን ተክሎ ከአንድ አመት በኋላ ነቅሎ ሌላ ቦታ መትከል እድገቱ ላይ ከፍተኛ አደጋ መጣል መሆኑን በመገንዘብ ተጨዋቾች ከክለብ ክለብ መዘዋወርን እንደ ቀልድ ሊያዩት እና ነገሮችን በሙሉ ከጊዜያዊ ጥቅም ጋር ብቻ ሊያተሳስሩት አይገባም፡፡ ምን አልባትም ዳዊት በእነዚህ ዝውውሮች አማካኝነት ‹‹የኢኮኖሚ ተጠቃሚ›› ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን ይህ የተጨዋቹ የኢኮኖሚ ጥቅም ሳይሸራረፍ ተጠብቆለት በውስን ክለቦች ላይ እየተጫወተ ክፍተቱ ቢሞላ እና ቢሻሻል ኖሮ ምን አልባትም ከምናስበው እና ከዚህ በላይ ሐገርም ሆነ እርሱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡

ዳዊት እስጢፋኖስ

የአንድ ተጨዋች ከክለብ ክለብ በፍጥነት መቀያየር ወይም አለመረጋጋት የተጨዋቹን እድገት ከመጉዳቱ በተጨማሪ  የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ትኩረት መቀነስ ስለሚያከትል፣ ስለ ቀጣይ ክለብ መብሰልሰል ስለሚበዛ፣ የአይመለከተኝም ስሜት መዳበር ስለሚጨምር እና ሌሎችም መሰል ባህሪያት እንዲፈጠሩ ስለሚያደርግ አጠቃላይ የክለቡ ውጤታማነት እና የቡድን አጋሮቹ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ክለቡን ሰኔ ላይ እንደሚለቅ እያወቀ የሚጫወት ተጨዋች እና ገና ሶስት እና አራት አመታትን እንደሚቀጥል የሚያስብ ተጨዋች ሜዳ ላይ እኩል አገልግሎት ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡

ክለቡን ሰኔ ላይ የሚለቅ ተጨዋች የክለቡን ውጤታማነት ከመጉዳቱ በተጨማሪ በክለቡ ውስጥ እቆያለሁ ብሎ የሚያስበው ተጨዋች እድገት ላይ የሚኖረው ተፅእኖ የጎላ ነው፤ ምክንያቱም እግር ኳስ በክፍል አንድ ፅሁፋችን እንደገለፅነው ተደጋጋፍያዊ (Interactive) ስፖርት ነው፡፡ ለምሳሌ አብረው በመጫወት ከፍተኛ ጥምረት እያሳዩ ከነበሩ ሁለት ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› አማካኞች ውስጥ ‹‹ሀ›› ክለቡን ቢለቅ እና ‹‹ለ›› እዛው ክለብ ቀርቶ አዲስ አጣማሪ ‹‹ሐ›› ቢመጣለት ከ‹‹ሀ›› ጋር ለአመታት የገነባው የተግባር ተኮር ውህደት በዜሮ ይባዛል፤ አሁናዊ የቡድን እርጋታውም ይቀንሳል፡፡

ይህ ማለት ‹‹ለ›› ከአዲሱ አጣማሪው ‹‹ሐ›› ጋር የሚኖረው ሚና እስኪጠራ (Role Clarity)፣ የደመ ነፍስ መናበብ እስኪጨምር (Telepathic Instinct)፣ ድክመትም ሆነ ጥንካሬ እስኪናበብ ድረስ አቋሙ ለወራት ወይም ለአመታት ያህል የመውረዱ እድል እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም በእግር ኳስ ውስጥ የአንዱ ተጨዋች መጎምራት በሌላኛው ተጨዋች ውስጥ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ የአንዱ ተጨዋች ክለብ መልቀቅ ክለቡ ውስጥ አርፎ ለተቀመጠውም ጦስ እንደሚሆን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ቅጥ ያጣ የተጨዋቾች ዝውውር አንድም ለራሱ ለተጨዋቹ አቅም መውረድ፣ ሁለትም ለቡድን ጓደኞቹ ብቃት መቀነስ፣ ሶስትም ለቡድን ውጤታማነት መጥፋት፣ አራትም ለሊግ ውድድር መፍዘዝ፣ አምስትም ለብሄራዊ ቡድን መዳከም ይዳርጋል፡፡

ከዚህ አንፃር ተጨዋቾች ለእድገታቸው እና ለውጤታማነታቸው ሚና ያለውን የዝውውር ስርዓት በመከተል በእግር ኳሱ የሚኖራቸውን ስኬት እና የረዥም ጊዜ ቆይታ ከግምት ያስገባ ዝውውር እና ውል ሊፈፅሙ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ተጨዋቾች ስራቸው መጫወት እንደመሆኑ አዳዲስ ስርዓት ከመትከል፣ አዳዲስ አሰራር ከመተግበር አኳያ ያላቸው ሚና እጅግ ውስን ነው፡፡ የተፈጠረውን እና ያለውን አካሄድ ተቀብለው ከመጓዝ በዘለለ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም፤ ለዚህም ነው በተሰራው እና እየተሰራ ባለው ጥፋት ተጨዋቾች ተጠያቂ የሚሆኑበት እድል በእጅጉ የጠበበ ነው የምለው፡፡ የተጨዋቾች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተጠብቆ፣ የሚገባቸው ክፍያ ተከፍሎ በወጥነት አንድን ቡድን የሚያገለግሉበትን ባህል ክለቦች ቢፈጥሩ ውጤቱ ሁሉን አቀፍ፣ ሁለንተናዊ እና ሐገራዊ እንደሚሆን ሙሉ እምነቴ ነው፡፡

በቀጣይ የክፍል-3 ጥንቅር አሁን ያለው የተጨዋቾች ዝውውር ባህል ከኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ፍልስፍና፣ ከስፖርት ፖሊሲው አላማዎች፣ ከክለቦች ስትራቴጂካዊ ልማት እና ከሙስና መንሰራፋት አንፃር የነባራዊ ሁኔታ ትንተና ይቀርባል፡፡


ስለ ጸሀፊው


ሳሙኤል ስለሺ

ፀሀፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የስፖርት ስነልቦና እና የእግር ኳስ መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ሲሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡    

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *