የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሼ ፍቅሩ ኪዳኔ ትውስታዎች…

የዛሬ 60 ዓመት ለእንቁጣጣሽ አጥቢያ በሮም ኦሊምፒክ ጨዋታ ፕሮግራም መሰረት የማራቶን ሩጫ ይካሄዳል፡፡ ቀኑ ቅዳሜ ጳጉሜን 05 ቀን 1952 ዓ.ም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሁለት ሯጮች አበበ ቢቂላን እና አበበ ዋቅጅራን አሰልፋለች፡፡ የሯጮቹ አሰልጣኝ ደግሞ ስዊድናዊው ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ናቸው፡፡ አዳዲስ ጫማ ተገዝቶ ለሁሉም አትሌቶች ታድለዋል፡፡ አበበ ቢቂላ የተሰጠውን ጫማ ሞክሮ ስላልተስማማው በባዶ እግር ለመሮጥ ወሰነ፡፡ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን የክብር ዘበኛ ሚሊቴሪ አካዳሚ አስተማሪ ስለነበሩ  እና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በባዶ እግሩ የሚኳትን መሆኑን ስለሚያውቁ አልተገረሙም፡፡ የሮም ከተማ ሙቀት ሯጮቹን እንዳይጎዳ ተብሎ ሩጫው የተጀመረው ከቀትር በኋላ 11፡30 ፒያሳ ካምፒዶሊዮ በተባለ ስፍራ ላይ ነው፡፡

ውድድሩን ያሽንፋል ተብሎ የሚጠበቀው አንድ የመስኮብ ሯጭ ነው፡፡ አፍሪካውያኖች መኖራቸውን የሚያስታውስ የለም፡፡ ሩጫው ተጀምሮ 20ኪ.ሜ ላይ ሲደርሱ ነው ሁለቱ አፍሪካውያኖች ኢትዮጵያውያው አበበ ቢቂላና የሞሮኮው ተወካይ ራዲ አብዲሰላም ብቅ ያሉት እና ፊታቸውን ያሳዩት፡፡

የሚገርመው ደግሞ ኢትዮጵያዊው የሚሮጠው በባዶ እግሩ ነው፡፡ ፈረንጆቹ አፍሪካ በተለይ ኢትዮጵያ ደሃ ስለሆነች ህዝቦቿ ጫማ የላቸውም በማለት አምነዋል፡፡ ሁለቱ አፍሪካውያኖች ጎን ለጎን በመሮጥ የሮማን ጎዳና በጨለማ ተያይዘውታል፡፡

Mamo Wolde, Abebe Bikila and Onni Niskannen

ግራ እና ቀኝ ችቦ ነው የሚበራው፡ ፒያሳ ዲ ፖርታ ካፔና ሲደርሱ፡ አበበ ቢቂላ የአክሱምን ሀውልት ቆሞ ሲመለከት ብልጭ አለበት መሰለኝ ሞሮኳዊውን ጥሎት ገሰገሰ፡፡ ሞሶሎኒም ትዝ ብሎት ይሆናል፡፡ ለማንኛውም የማራቶኑን 42ኪሜ ከ195ሜ ርቀት በሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ በመፈጸም፡ አዲስ የዓለም እና የኦሊምፒክ ክበረወሰን በማስመዝገብ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን በመሆን ሀገሩን እና አህጉሩን ታላቅ ክብር አጎናጸፈ፡፡

አበበ ቢቂላ ባሸነፈ ማግሰት እንቁጣጣሽ ስለነበር የኢትዮጵያኖችን ደስታ ለመገመት አያስቸግርም፡፡ አበበ ወታደር እንደመሆኑ መጠን አዲስ አበባ ሲደርስ የአቀባበሉን ስነስርዓት ያዘጋጀው የክብር ዘበኛ ጠቅላይ መምሪያ ነው፡፡

በቀጥታም የሄደው ወደ ቤተመንግስት ጃንሆይን እጅ ለመንሳት ነው፡፡ እርሳቸውም የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ሜዳይ እና የአስር አለቃነት ሹመት ሰጡት፡፡ አበበ ለመጨረሻ ጊዜ በባዶ እግሩ የሮጠው በ1953 ዓ.ም በአቴንስ ግሪክ ነው፡፡

ከሶስት አመት በኋላ እ.ኤ.አ በ1964 በቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ለመሳተፍ ሲዘጋጅ፡ ሮም ላይ በባዶ እግሩ መሮጡን ያስታወሱት ጃፓኖቹ፡ ጫማ እንስፋልህ ብለው ሃሳብ አቀረቡ፡፡ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ጫማ እያሰፋ የሚያጌጥበት ጊዜ ስለነበር የጃፓን ወጪን የሚችል የለም የሚል መልስ ተሰጠ፡፡ ሃሳቡን ያቀረበው ጃፓናዊ ለአበበ በነጻ ነው ሰፍቼ የምሸልመው በማለት አረጋገጠ፡ እግሩን ተለክቶም ተሰፍቶ መጣለት፡፡

ለማንኛውም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጊዜው አስፈላጊውን ትጥቅ ለሁሉም አትሌቶች አድለዋል፡፡ የአበበ ቢቂላን ጫማ ሰፍተው ያመጡት አዛውንት የአሲክ ኩባንያ ባልደረባ ነበሩ፡፡

አበበ በዚያ ጫማ ሮጦ ነው በሁለት ሰዓት ከ12.11 ደቂቃ ውድድሩን ጨርሶ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግቦ እንደ ልማዱ ጂምናስቲክ እየሰራ ሌሎቹ ሯጮች ቶኪዮ ስቴዲየም ውስጥ እስኪገቡ ይጠብቅ የነበረው፡፡ ሁለተኛ የወጣው የእንግሊዙ ባዜል ሂትሌይ ሲሆን ሶስተኛ የሆነው ደግሞ ኮኪሹ ኩቡራያ ከጃፓን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከአበበ ጋር ያሰለፈቻቸው ሁለቱ ሯጮች ደምሴ ወልዴ 10ኛ ሲወጣ ማሞ ወልዴ ደግሞ በ15ኛው ኪሎሜትር ላይ አቋርጦ ወጥቷል፡፡

ከቶኪዮ መልስ ጃንሆይ ለአበበ ቢቂላ የ100 አለቅነት ማዕረግ ሸለሙት፡፡

ከአራት አመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ1968 ለሜክሲኮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ሲዘጋጅ ስለታመመ ጀርመን ሀገር ሄዶ የአፐንዲሲት ኦፔራሲዪን አደረገ፡፡ ሆስፒታሉም የህክምና ወጪውን የጀርመን መንግስት ነው የሚችለው አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እግሩን ትንሽ ያመው ስለነበረ ሜክሲኮ ሲደርሱ ልዩ ልዩ ሀኪሞች መርምረውት እንዲያርፍ መከሩት፡፡ እንዲያውም ልምምድ እንዳይሰራ እና የሩጫወው ዕለት ብቻ እንዲካፈል የሚል አስተያየትም ተሰንዝሮ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ሜክሲኮ ላይ ከአበበ ቢቂላ ሌላ ማሞ ወልዴን እና ገብሩ መራዊን አስመዝግባ ነበር፡፡ አበበ ሁለቱ የማራቶን ሯጮች በየቀኑ ልምምድ ሲያደርጉ ማየቱ ስላልጣመው ሌሊት ተደብቆ ይለማመድ ነበር፡፡ አበበ ለሶስተኛ ጊዜ የሚወዳደር በመሆኑ የዓለም ጋዜጠኞች በሙሉ ሊያነጋግሩት ይፈልጉ ነበር፡፡ ጥያቄው ስለበዛ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሀፊ ስለነበርኩ የፕሬስ ኮንፈረንስ አዘጋጀሁ፡፡ እኔው ራሴ አስተርጓሚ ሆኜ ከአበበ እና ኦኒ ኒስካኔን ጋር ቀረብን፡፡

የመጀመሪያውን ጥያቄ ተርጉሚ ስነግረው ‹‹ጋሼ አንተ ከእኔ የተሻለ ጉዳዩን ታውቅ የለም፡ ለምን አትመልስልኝም?›› አለኝ፡፡  የኛ አትሌቶች ከልምምዳቸው ውጭ ለፕሬስ የሚጥም ገለጻ ስለማያደርጉ እስካሁን ድረስ ችግር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የቋንቋ ችግር እስካሁን መፍትሄ አልተበጀለትም፡፡ እንደ ኃይሌ ገብረስላሴ አይነቱ ምሳሌ ሊሆን ይችል ነበር፡፡

የሜክሲኮ ማራቶን ሩጫ ከተጀመረ በኋላ 15ኛው ኪሎሜትር ላይ የእግሩ ህመም ጠናበትና አበበ አቋርጦ ወጣ፡፡በአስር ሺህ ሜትር ተካፍሎ የብር ሜዳሊያ ያገኘው ማሞ ወልዴ እና ገብሩ መራዊ ግን ውድድራቸውን ቀጥለው ከመሪወቾ መደብ ውስጥ ተሰልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ማሞ ወልዴ በሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃ ውድድሩን በማሸነፍ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር አዘመረ፡፡ ኢትዮጵያም በተከታታይ ለሶስተኛ ጊዜ የማራቶን አሸናፊ ሆነች፡፡

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ውስጥ የአፍሪካ ሀገሮች ነጻ ወጥተው በኦሊምፒክ ጨዋታ መካፈል ጀምረው ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊው በባዶ እግሩ ሮጦ ካሸነፈ እኛስ ለምን አንችልም በሚል ፉከራ ሁሉም ሀገሮች ከቶኪዮ የኦሊምፒክ ጨዋታ ጀምሮ የማራቶን ሯጮች አሰልፈው ነበር፡፡ ነገር ግን ቶኪዮ ላይ አበበ ሜዳሊያውን ተቀብሎ ወደ ኦሊምፒክ መንደር ከተመለሰ በኋላም ወደ ስቴዲየም የሚደርሱ የአፍሪካ ሯጮች ነበሩ፡፡ ሜክሲኮ ላይም ፋሻ ጠምጥመው የደረሱ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊው ገብሩ መራዊ  ስድስተኛ ነበር የወጣው፡፡

ማሞ ወልዴ በ10ሺህ ሜትር ሩጫ ላይ ለጥቂት ወርቁ ሜዳሊያ እንዳመለጠችው የታዘበ የኮንጎ ስፖርት መሪ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ፕሬዝዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ‹‹ተሰማ ለትንሽ ወርቁ አመለጠህ›› ሲለው፡ ጋሼ ይድነቃቸውም  ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ወርቅ ሞልቶናል የቸገረን ብር ነበር›› ብሎ መለሰለት፡፡

አትሌቶቻችን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ አበበ ቢቂላን ሻምበል፣ ማሞ ወልዴን ደግሞ መቶ አለቃ አድርገው ሾሟቸው፡፡

እ.ኤ.አ በ1969 ነው አበበ ቢቂላ የመኪና አደጋ ደርሶበት በጃንሆይ መልካም ፈቃድ ለህክምና ወደ እንግሊዝ ሀገር የተላከው፡፡ እዛም ስቶክማንድቪል በሚባል ዝነኛ ሆስፒታል ስምንት ወር ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1970 አቶ ይድነቃቸው እና እኔ ከኦውስትሪያ ስብሰባ ስንመለስ ሄደን ስንጠይቀው፡ ከመላው ዓለም የተላኩለት ደብዳቤዎች በአንድ ጆንያ ውስጥ ተጠራቅመው አገኝን፡፡ እኔመ ባለብኝ የስራ ሀላፊነት ምክንያት በእርሱ ስም መልስ ለመስጠት  ድብዳቤዎቹን ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ ቢያንስ ለትልልቆቹ ባለስልጣናት መልስ ለመስጠትም ወሰንን፡፡ ከእነርሱም መካከል፡ ለታላቋ ብሪታኒያ ንግስት ኤልዛቤት እና ለዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ከአዲስ አበባ መልስ ልኬያለሁ፡፡ ንግስት ኤልዛቤት ግን ሆስፒታል ድረስ ሄደው አበበን ጠይቀውታል፡፡ እኛን ስቶክማንድቪል ሆስፒታል የወሰደን ደግሞ ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንድ ዲፕሎማት ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1972 በጀርመን ሀገር በሙኒክ ከተማ የተካሄደውን የኦሊምፒክ ጨዋታን እንዲመለከቱ በክብር ከተጋበዙት የክብር እንግዶች ውስጥ አበበ ቢቂላ ሲገኝበት፣ ሌሎቹ ደግሞ የታርዛንን ፊልም የሰራው ጆኒ ዌስሙለር፣ የናዚው መሪ ሂትለር እጁን አልጨብጥም ያለው እ.ኤ.አ በ1936 በበርሊን ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ አራት የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈው ጥቁር አሜሪካዊው ጄሴ ኦዌንስ ነበሩ፡፡ ማሞ ወልዴ በአምስተኛ ኦሊምፒክ ጨዋታው በመካፈል በማራቶን ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡

Abebe Bikila and Jese Owens

ከአንድ አመት በኋላ ነው በ41 አመቱ አበበ ቢቂላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፡፡ እ.ኤ.አ በ1992 ባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ከ28 አመታት በፊት ቶኪዮ ላይ ለአበበ ቢቂላ ጫማ ለክተው ሰፍተው የሰጡት አዛውንት፡ የኩባንያው ፕሬዝዳንት ሆነው የአበበን ጫማ በብር አሰርተው እኔ በተገኘሁበት ስነስርዓት ላይ ለማስታወሻ እንዲሆን ለኢንቴርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት፣ ለኢንቴርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና ለአበበ ቢቀላ ባለቤት ለወይዘሮ የውብዳር ወልደጊዮርጊስ አበርክተዋል፡፡ የወ/ሮ የውብዳር ጉዞን ያዘጋጀሁት እኔ ነበርኩ፡፡

የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በ10ሺህ ሜተር ሩጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት ወዳጄ ደራርቱ ቱሉ ብቅ ያለቸውም ባርሴሎና ነው፡፡

የ60 ዓመት ታሪክ ለመጻፍ ያበቃኝ ለአምላኬ ምስጋና ይድረሰው!

ፍቅሩ ኪዳኔ

Fikrou Kidane with Nelson Mandela in 1994

 

 

 

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *