በብራስልስ ቤልጄየም ዛሬ በተከናወነው የ2020 የዳይመንድ ሊግ ውድድር የተሳተፉት ሆላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን እና እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በኢትዮጵያውያኖቹ አትሌት ድሬ ቱኔ እና ኃይሌ ገብረስላሴ ለዓመታት ተይዘው የቆዩትን የአንድ ሰዓት ውድድር የዓለም ክብረ ወሰኖች አሻሽለዋቸዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ከኬንያዊቷ የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ብሪጃድ ኮስጌይ ከፍተኛ የሚባል ፉክክር ቢገጥማትም በአንድ ሰዓት ውስጥ 18,930 ሜትሮችን በመሮጥ አዲሱን የዓለም ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ ችላለች። አትሌት ድሬ በጎርጎሮሳውያኑ 2008 ቼክ ሪፐብሊክ ላይ በአንድ ሰዓት ውስጥ 18,517 ሜትሮችን በመሮጥ ነበር የክብረወሰኑ ባለቤት ሆና የቆየችው።

የአራት ጊዜ የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮኑ እና እስከዛሬ ድረስ አንድም የዓለም ክብረ ወሰን በስሙ ያልነበረው እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ፡ በመጨረሻም በአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ 2007 ኦስትራቫ ላይ የተመዘገበውን 21,285 ሜትሮች የወንዶች የርቀቱን ክብረ ወሰን በ45 ሜትሮች በማሻሻል የክብር ባለቤት መሆን ችሏል።

አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በዕለቱ በሞ ፋራህ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ 20,000ሜትሩን በ56:26 በመግባት አስመዝግቦት የነበረውን ሌላኛውን ክብሩንም እስከ መጨረሻዎቹ ሰከንዶች ድረስ ውድድሩን መርቶ ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀው ቤልጀማዊው አትሌት በሺር አብዲ በአምስት ሰከንዶች ተበልጦ ተነጥቋል።

በስኬታማው የሯጭነት ዘመኑ 27 የዓለም ክብረወሰኖችን የግሉ ማድረግ የቻለው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፡ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የዓለም ክብረ ወሰን በስሙ አይገኝም።

አዲሶቹ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቶችም፡ ለዚህ ስኬት ለወራት የዘለቀ ጠንካራ ልምምድ ሲያደርጉ እንደቆዩ በመግለጽ በዚህ ፈታኝ ወቅት እንደዚህ አይነት መድረክ ላሰናዱት የውድድሩ አዘጋጆችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የማንቂያ ደወል ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ?

የአትሌቲክሱ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ልክ እንደተቀረው ክፍል ሁሉ በሩን ለመዝጋት ቢገደድም፤ ነገር ግን ተዋንያኖቹ ከመጋረጃ ጀርባ እጃቸውን አጣጥፈው እንዳልተቀመጡ፡ ባለፉት ቀናት በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ውድድሮች እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶች ምስክሮች ናቸው።

የዛሬዎቹን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ላለፉት አስር እና ከዚያ በላይ አመታት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስም ተይዘው የነበሩ የዓለም ክብረ ወሰኖች ተሰባብረዋል።

የነገሮች አሁናዊ አካሄድ የሚጠቁሙት ሌሎቹም ክብረወሰኖች በቅርቡ ሊሻሻሉ እንደሚችሉ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ ተፎካካሪዎች በአትሌቶቻችን ላይ እየወሰዱት የሚገኘው ፍጹም የበላይነት፡ የሀገራችንን ለዘመናት በትውልድ ቅብብል የተገነባ የአልሸነፍ ባይነት፣ የጽናት እና የድል ምልክት የሆነውን የተለመደ አሸናፊነት አርቀው ሳይወስዱብን ስፖርቱን የሚመሩት አካላት ሁኔታውን እንደ ማንቂያ ደወል ቢጠቀሙበት መልካም ነው።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *