ማርቆስ ኤልያስ (ጋዜጠኛ) – ለልዩ ስፖርት

ሪያል ማድሪድ ከ1956-1960 ያለማቋረጥ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ (የአሁኑ ቻምፕዮንስ ሊግን) ሻምፕዮን ሲሆን እንዲሁም ከ1986-1990 ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የላ ሊጋ ክብርን ሲያሳካ ላ ፋብሪካ የተሰኘው ዝነኛው አካዳሚው የላቀ ሚና ነበረው፡፡ ከዚህ አካዳሚ የወጡ ተጨዋቾች ተፅዕኗቸው ከፍ ያለውን ቦታ ይወስዳል፡፡

ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ እኤአ በ2000 ወደ ክለቡ ፕሬዝደንትነት ከመጡ በኋላ ለዝነኛ ተጨዋቾች ዝውውር ከፍ ያለ ክፍያን ሲፈፅሙ መሰል ተጨዋቾች “ጋላክቲኮስ” የሚለውን ስያሜ ያህል “ዚዳኖች” በሚለው ይወከላሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከአካዳሚው የሚያድጉት ደግሞ “ፓቮኖች” ተብለው ይጠራሉ፡፡

በ ላ ሊጋው እና ሴንጉዳ ሊግ ከላ ፋብሪካ የተገኙ ተጨዋቾች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በላ ሊጋው ከሚጫወቱ ተጨዋቾች 41 ያህሉ ከላ ፋብሪካ የተገኙ ናቸው፡፡ በስፔን ብ/ቡድን ቁልፍ ሚና ያለው የባርሴሎናው ላ ማሲያ አካዳሚ እንኳን በላ ሊጋው የሚወከለው በ30 ተጨዋቾች ነው፡፡ በሴንጉዳ ሊግ (የስፔን ሁለተኛ ዲቪዚዮን) ከላ ፋብሪካ የፈሩ 28 እንዲሁም ከላ ማሲያ 21 ተጨዋቾች በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሪያል ማድሪድ በከዋክብቶች ግዢ ላይ በማተኮሩ ምክንያት ከአካዳሚው በወጡ ተጨዋቾች ላይ እምብዛም ትኩረት ባያደርግም ወሳኝ የሚባሉ ተጨዋቾች፡ በዚህ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡ ዳኒ ካርቫሃል፣ ናቾ ፈርናንዴዝ፣ ካዜሚሮ እና ሉካስ ቫዝኬዝ በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ – ሄዜ ሮድሪጌዝ እና አልቫሮ ሞራታን መርሳትም ተገቢ አይሆንም፡፡

የጨዋታ ፍልስፍና እና አቀራረብ

“ከምንም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ኳስን በቁጥጥራችን ስር ማድረግ እና በተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ላይ መቆየት ነው” ይላል – በ1990ዎቹ ለሪያል ማድሪድ የተጫወተውና ከ2006-2016 ድረስ በላ ፋብሪካ የአሰልጣኝነት ሚና የነበረው ሉዊስ ራሚስ፡፡ “የምንከተለው የጨዋታ ዘይቤ እና የልምምድ ጥራት ከሴቪያ፣ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ልዩነት የለውም፡፡

ኳስን ተቆጣጥረን በመጫወት ረገድ ከባርሴሎና ጋር እንመሳሰላለን፡፡ ሁለታችንም ኳሷን እንደፈለግን ማዘዝ እና መቆጣጠር እንፈልጋለን….የጨዋታው ንጉስ መሆን እንሻለን፡፡ በዚህ በኩል እንመሳሰላለን፡፡ ለማሸነፍ ያለንን ፍላጎት ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ፋታ በማይሰጥ የማጥቃት እንቅስቃሴያችን ደጋግመን አሳይተናል፡፡” ሲል ያክላል።

በላ ፋብሪካ የኳስ ቁጥጥር ቅድሚያውን ይወስዳል፡፡ ኳስን በእግር ስር ማቆየት፣ ሰውነትን ማሟሟቅ፣ ከመከላከል ወደማጥቃት የሚደረግ ሽግግር፣ የኳስ ቁጥጥር፣ በጨዋታ ላይ የሚተገበሩ የታክቲክ ልምምዶች ይተገበራሉ….ልምምዱ የሚሰራው በግማሽ ሜዳ በመሆኑ የኳስ ንኪኪዎች በብዛት ይተገበራሉ፡፡ ታዳጊዎች ከኳስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከፍ ይላል፡፡

የአሰልጣኞች ታክቲካዊ አቀራረብ ቀጣዩን ጨዋታ መሰረት ያደረገ ነው….አንዳንድ ጊዜ ጨዋታው ምን እንደሚመስል ከግምት ውስጥ ያስገባ ልምምድ ይሰራል፡፡

“ልምምዱ ከፍ ያለ የፉክክር ስሜት የተሞላበት ነው” ይላል – ራሚስ ንግግሩን በመቀጠል፡፡ “ልምምድ አሰጣጡ የኳስ ቅብብል ላይ ያተኮረ ቢሆንም ህጉን ጠብቆ እንጂ በዘፈቀደ የሚከናወን አይደለም፡፡ በሜዳ ውስጥ ተጨዋቾች የሚኖራቸው የቦታ አያያዝ እና ታክቲክ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በአጠቃላይ የልምምድ አሰጣጡ በሳምንቱ መጨረሻ ከሚኖረን ጨዋታ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡”

የሳምንቱ የልምምድ አሰጣጥ የራሱ የሆነ ፕሮግራም አለው፡፡ ዕሁድ እለት ጨዋታ ከተደረገ በሁዋላ በቀጣዩ ቀን ሰኞ የመጨወት ዕድል ያገኙት የማገገም ልምምድ ይሰራሉ….የመሰለፍ ዕድል ያላገኙት “የማካካሻ ልምምድ” እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ ማክሰኞ የእረፍት ቀን ነው፡፡ ረቡዕ እና ሐሙስ ከኳስ ጋር የተያያዙ ታክቲካዊ ልምምዶች የሚሰሩበት ነው፡፡ “ዓርብ እና ቅዳሜ የቀደሙትን ሁለት ቀናት ልምምዶች ይበልጥ የምናዳብርበት ነው….በዚህ ልምምድ የጎል ማግባት ሙከራዎችን ማድረግ ጨምሮ የተለያዩ ልምምዶችን እንሰራለን” የሚለው ራሚስ ነው፡፡

ላ ማሲያ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?

እኤአ ከ2007-16 በነበሩት ያለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከላ ፋብሪካ ይልቅ ላ ማሲያ ለዋናው ቡድን ተጨዋቾች በማበርከት የተሻለ እንደነበር ቢያሳዩም በብዙ ሊጎች ብዙ ተጫዋቾችን በማሰለፍ ግን ላ ፋብሪካ ከአለም ቀዳሚው አካዳሚ ነው፡፡

2007/08
ላ ፋብሪካ – 7
ላ ማሲያ – 12

2008/09
ላ ፋብሪካ – 7
ላ ማሲያ – 11

2009/10
ላ ፋብሪካ – 4
ላ ማሲያ – 11

2010/11
ላ ፋብሪካ – 6
ላ ማሲያ – 12

2011/12
ላ ፋብሪካ – 5
ላ ማሲያ – 11

2012/13
ላ ፋብሪካ – 5
ላ ማሲያ – 17

2013/14
ላ ፋብሪካ – 9
ላ ማሲያ -17

2014/15
ላ ፋብሪካ – 7
ላ ማሲያ – 12

2015/16
ላ ፋብሪካ – 8
ላ ማሲያ – 10

በአሁኑ ወቅት በመላው አለም በልዩልዩ ሊጎች ውስጥ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች 200 ያህሉ ከዚህ አካዳሚ የተገኙ ናቸው፡፡ ሰባት ተጨዋቾች ለሪያል ማድሪድ ዋናው ቡድን፣ 48 በሌሎች የላ ሊጋ ክለቦች፣ 55 በሁለተኛው የላ ሊጋ እርከን (ሴንጉዳ ሊግ)፣ 25 በሌሎች የአውሮፓ ክለቦች እንዲሁም 20 የሚሆኑ ተጨዋቾች በመላው ዓለም በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

የላ ፋብሪካ ውስጣዊ ይዘት

ላ ፋብሪካ ወደ ማድሪድ ዓለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፍያ መንገድ በከተማዋ መውጪያ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ አካዳሚው 13 የእግርኳስ ቡድኖች አሉት፡፡ ዕድሜያቸው ከሰባት ጀምሮ እስከ ሪዘርቭ (ተጠባባቂ) ቡድኑ ድረስ ያሉትን የዕድሜ እርከን ቡድኖች ያቀፈ ነው፡፡

አካዳሚው 12 ሜዳዎች አሉት – ከአንዱ ሜዳ በስተቀር ሌሎች ሜዳዎች ጥራት ከሳንቲያጎ በርናባው ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከእነኚህ ሜዳዎች ውስጥ ስምንቱ ልክ እንደ ሳንቲያጎ በርናባው ከሆላንድ በመጣ ተፈጥሮዋዊ ሳር እንዲሁም አራቱ በአርቴፊሻል ሳር የተዋቀሩ ሜዳዎች ናቸው፡፡

ሜዳውን ውሃ በማጠጣት እና የአካዳሚውን ህንፃ ሙቀት የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ጣብያ ክለቡ አዋቅሯል፡፡ በአካዳሚው ውስጥ አራት የመዋኛ ገንዳ፣ ሳውና፣ ሁለት የገላ መታጠብያ (ሙቅ እና ቀዝቃዛ ውሃ) እና ጂምናዚየም አለው፡፡ በታላቁ የቀድሞ የክለቡ ኮከብ አልፍሬዶ ዴ ስቴፋኖ የተሰየመው የአካዳሚው ስታዲየም 6000 ተመልካቾች ይይዛል፡፡ [በኮቪድ-19 ምክንያት ሪያል ማድሪድ በአሁኑ ወቅት እየተጠቀመበት ያለው ይኽንን ስታዲየም እንደሆነ ልብ ይሏል]

የአካዳሚው ተጨዋቾች ለልምምድ ሲመጡ የሚይዙት የመጫወቻ ጫማ ብቻ ነው – ሌላውን ትጥቅ አጥቦና አድርቆ የሚያዘጋጅ ራሱን የቻለ ባለሙያ አለ፡፡ በአካዳሚው ውስጥ የተለያዩ የጌም ክፍሎች አሉ – እንዲሁም ታዳጊዎች ዘና ይሉ ዘንድ ሲኒማ ቤት ተዘጋጅቶላቸው በትርፍ ጊዜያቸው ፊልም ይመለከታሉ፡፡ ሌሎች የተመቻቹ ግብዓቶችን ይዟል፡፡

አንድ ታዳጊ በአካዳሚው በአማካይ ሶስት ዓመት ይቆያሉ፡፡ ለአንድ ታዳጊ አካዳሚው በአማካይ ከ35,000-40,000 ዩሮ ያወጣል፡፡ እያንዳንዱ ታዳጊ በየወሩ 200 ዩሮ የኪስ ገንዘብም ይሰጠዋል፡፡

ታዳጊዎች በሚኖራቸው ቆይታ የሪያል ማድሪድ DNA በውስጣቸው እንዲገባ ይደረጋሉ – ከዚህ በተጨማሪም እስከመጨረሻው ተስፋ በማይቆርጥ የተፋላሚነት ስሜት ጠንካራ አዕምሮ እንዲይዙ የስነልቦና ስራ ይሰራባቸዋል፡፡

ሪያል ማድሪድ ጥሩ ሳይሆን የሚያሸነፍበት አንዱ ምክንያት ይኽ ነው፡፡ “በሌሎች ቡድኖች የአካዳሚ ትርጉም ሒደት ነው – በሪያል ማድሪድ በየትኛውም የዕድሜ እርከን ማሸነፍ የግድ ነው” ይላል – በ10 ዓመቱ ሪያል ማድሪድን ተቀላቅሎ ለቡድኑ ከ100 በላይ ጨዋታዎችን ያከናወነው እና በ2002 ከቡድኑ ጋር የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳው ፓኮ ፓቮን፡፡ “የስልጠና ጥራት እና ማሸነፍ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ጥራት ያለው ስልጠና ይሰጣል – ቡድኑ ካላሸነፈ ደጋፊውን ጨምሮ ደስተኛ የሚሆን አካል አይኖርም፡፡”

የአካዳሚው እውነታ

ሳንትያጎ በርናባው ካረፈበት ቦታ 40 እጥፍ ስፋት የሚልቅ ቦታ ላይ የተቀመጠው ላ ፋብሪካ በ1942 ተገንብቶ በ2005 እንደ አዲስ ሲታደስ 100 ሚሊዮን ዩሮ ወጥቶበታል፡፡ 12 ቡድኖችን በሚይዘው አካዳሚ በ40 መኝታ ክፍሎች ከ270 በላይ ታዳጊ/ወጣቶች ይስተናገዳሉ፡፡ ከምርጥ ተጨዋቾች ውጭ ጥራት ያላቸው ስፔናውያን አሰልጣኞች ከዚህ አካዳሚ ወጥተው ከፍ ባለ ደረጃ አሰልጥነዋል፡፡


በላ ፋብሪካ የሚታወሱ የአካዳሚው ፍሬዎች

ከ1955-1965 ሪያል ማድሪድ ስምንት ጊዜ የላ ሊጋው , ከ1956-1960 አምስት ጊዜ በተከታታይ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን ሲያነሳ እንዲሁም 1980ዎቹ አጋማሽ አንስቶ በተከታታይ ለአምስት ዓመታት የላ ሊጋ ክብሮችን ሲያሳካ ከላ ፋብሪካ የተገኙ ተጨዋቾች ቁልፍ ሚና ነበራቸው፡፡ የሚታወሱ ተጨዋቾች እነማን ናቸው?

*ኤሜሊያኖ ቡትራጊኖ
*ኢከር ካሲያስ
*ጉቲ
*ማርያኖ ጋርሲያ ሬሞን
*ኤስቴባን ካምቢያሶ
*ሚሼል
*ሆዜ ሉዊስ ካሚኔሮ
*ሁዋን ማታ
*ሳሙኤል ኤቶ
*ሮቤሮቶ ሶልዳዶ
*ሶል ኒጌዝ
*ሉዊስ ጋርሲያ
*ሁዋን ፍራን
*ሆዜ ካዬሆን
*ራዑል ብራቮ
*ፓብሎ ሳራቢያ
*ማርኮስ አሎንሶ

ማጠቃለያ

ላ ፋብሪካ የሪያል ማድሪድ ትልቅ እሴት መሆኑ የተደበቀ ምስጢር አይደለም፡፡ አካዳሚው ከሪያል ማድሪድ አልፎ በመላው ዓለም ለሚገኙ ክለቦች ጥቅም እየሰጠ ነው፡፡ ከዚህ አካዳሚ የወጡ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ለተለያዩ ክለቦች ሳይቀር ግብዓት ሆነዋል፡፡

ሎስ ብላንኮስ የሚገቡ ታዳጊዎች የሚመለመሉት ከስፔን እና ከመላው ዓለም ነው፡፡ ሪያል ማድሪድ ለአካዳሚው ምግብ፣ ትምህርት እና የትምህርት ግብዓቶችን ያቀርባል፡፡ በአካዳሚው የቀደሙ ተጨዋቾች ፎቶ ታዳጊዎችን ለማነሳሳት ተሰቅሎ ይታያል፡፡

ላ ፋብሪካ ከተጨዋቾች አልፎ ስኬታማ አሰልጣኞችን አፍርቷል፡፡ ትልቁ ማሳያው ዚኔዲን ዚዳን ነው፡፡ ሪያል ማድሪድን በተጨዋችነት ያገለገለው ፈረንሳዊው ጫማውን ከሰቀለ በሁዋላ ሁለት ዓመት በካስቲያ (የሪያል ማድሪድ ሁለተኛው ቡድን) ሁለት ዓመት አገልግሎ በመጨረሻም ዋናውን ቡድን ለሶስት ተከታታይ ዓመታት የቻምፒየንስ ሊግ ስኬት አብቅቷል፡፡ በ2016/17 እንዲሁም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የላ ሊጋ ክብርንም አሳክቷል፡፡

ራፋ ቤኒቴዝ ሌላው የሚጠቀሱ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ የሪያል ማድሪድ ወጣት እና ዋናውን ቡድን አሰልጥነዋል፡፡ በቫሌንሲያ ሁለት የላ ሊጋ እና ዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን አንስተዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይገቱ ከሊቨርፑል እና ቼልሲ ጋር የቻምፒየንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ ድሎችን አሳክተዋል፡፡

ሉዊስ ሚጌል ራሚስ፣ ሚሼል፣ ሳንቲያጎ ሶላሪ፣ ሁሌን ሎፔቴጊ፣ ጉቲ እና ሻቢ አሎንሶ ሌሎች የአካዳሚው ፍሬ የሆኑ አሰልጣኞች ናቸው፡፡


ስለ ጸሀፊው


ማርቆስ ኤልያስ 

የስፖርት ጋዜጠኛ እና የቀጥታ ጨዋታ አስተላላፊ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *