በ ቅድስት ታደሰ – የአትሌቲክስ ህክምና እና ስነምግብ ከፍተኛ ባለሙያ  – ለ ልዩ ስፖርት ብቻ

አለማችን እስከዛሬ ካስተናገዳቻቸው ወረርሽኞች ሁሉ በአስከፊነቱ እንደሚልቅ እየተነገረለት የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሰው ልጆች ሂወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖውን እያሳደረ ይገኛል፡፡ ቫይረሱ በሀገራችን በወርሃ መጋቢት መከሰቱን ተከትሎ አሰከፊነቱን በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና ሌሎቸ በርካታ ዘርፎች ላይ እያደረሰ በሚገኘው ከፍተኛ ጉዳት እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

የስፖርቱ ዘርፍም በዚሁ ቫይረስ ክፉኛ ከተጎዱት መካከል አንዱ ነው፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ በ2020 ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ታላላቅ ሀገራዊ፣አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ውድድሮች እንዲራዘሙ እና እንዲሰረዙ ሆነዋል፡፡ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የሚወዳደሩ ኢትዩጵያዊያን አትሌቶችም በዚህ ወረርሽኝ ምክኒያት ቤታቸው እንዲቀመጡ ብሎም ከቡድን ልምምዶች እንዲገቱ አድርጓቸዋል፡፡

በተለይም የቡድን ስፖርቶች በሆኑት እንደ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና አትሌቲክስ የመሳሰሉት ስፖርቶች፡ የሚሳተፉ አትሌቶች፡ የስፖርት አይነቶቹ በባህርያቸው ለንክኪ/መቀራረብ ስለሚጋብዙ እንዲሁም  በስፖርት ሕይዎት ውስጥ ሁልጊዜም አብሮነት እና ማህበራዊ ትስስር በመኖሩ ምክንያት ከመደበኛ ሰው ጋር ሲነፃፀሩ ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጮች ሊሆኑ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው፡፡

በመሆኑም አትሌቶችም እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በአለም የጤና ድርጅት እና በሀገራችን የጤና ሚኒስቴር የሚወጡትን የመከላከያ መርሆችን በአግባቡ እንዲተገብሩ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጎን ለጎንም አመጋገባቸውን በማስተካከል በሺታ የመከላከል ስርዓታቸውን እና አቋማቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ180 በላይ የምግብ አይነቶች መኖራቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚሀ የምግብ አይነቶች በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን በተለይም ካላቸው የተፈጥሮ ይዘት የተነሳ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስኬትም የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደቻሉ ይታመናል፡፡

በዚህ ጽሁፌ አትሌቶች ባለንበት አስቸጋሪ ወቅት ከሚሰሯቸው ልምምዶች ጋር አብረው የሚሄዱ ምግቦችን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ለማሳየት እወዳለሁ፡፡ በዚህ የወረርሽን ወቅት የሚደረጉ ልምምዶች በአብዛኛው ጫና የማይበዛባቸው እና አሁን ያለው ወቅታዊ አቋማቸው እንዳይወርድ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም አትሌቶች ቀጥሎ የቀረቡትን ሙያዊ ምክሮች ተባራዊ ቢያደርጓቸው የበለጠ ያተርፋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ኮሮና እና የሰውነት የመከላከል አቅም 

የኮሮና ቫይረስ በዋነኛነት የሚያጠቃው እና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም ሲወርድ ሲሆን፡ የሰው ልጅን የመከላከል አቅም ከሚቀንሱ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው ደግሞ የተጓዳኝ በሽታዎች መኖር ነው፡፡

ስለሆነም ከዚህ ችግር ለመዳን በዚህ ወቅት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የጤና እንጂ የብቃት ጉዳይ አለመሆኑን ታሳቢ በማድረግ ቫይታሚን እና ሌሎች ጠቃሚ ማዕድናትን ያካተቱ በተፈጥሮ ይዘታቸው በበሽታ ተከላካይነታቸውና አቅም በመጨመር የሚታወቁትን እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ምግቦችን መጠቀም እጂግ አስፈላጊ ነው፡፡

ለምሳሌ፡- እንደ ነጭ ሽንኩርት፣ አረንጓዴ አትክልቶች፣ እርድ፣ ሚጥሚጣ፣ ሎሚ ቴምር፣ ዘቢብ፣ በእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኙ ቫይታሚኖች፣ አንጮቴ፣ ምጪራ ወ.ዘ.ተ

ኮሮና እና ጭንቀት

በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት የሰው ልጅ ጤና አደጋ ላይ መውደቁ፣ ውድድሮች አለመኖራቸውና ተያይዞ የሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ የቡድን ልምምድ መቅረቱ፣ ስለ በሽታው የሚሰሙ ያልተጣሩ መረጃዎች፣ ለቤተሰብ አባላትና ለማህበረሰቡ ካለ አሳቢነት፣ ብቸኝነት እና ማህበራዊ ርቀትን መቋቋም አለመቻል ተደማምረው አትሌቱ ላይ ከፍተኛ ጭንቅትንና ውጥረት ይፈጥራሉ፡፡

ሰውነታችን በሚጨነቅበት ጊዜ ደግሞ ኮርቲዞል የሚባል ንጥረ ነገር የሚያመነጭ ሲሆን፡ ንጥረነገሩ በሰውነታችን ውስጥ በከፍተኛ መጠን በሚለቀቅበት ወቅት የተለያዩ የጤና ችግሮችን ያስከትላል፡፡

በተለይም ለስፖርተኞች በዋነኛነት የጡንቻ መድከም፣ የአጥንት መሳሳት፣ ከልምምድ በኃላ አጠቃላይ የሰውነት ዝለት፣ በሴት አትሌቶች ደግሞ የወር አበባ ፍሰት መዛባት እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡

በመሆኑም አትሌቶች በዚህ ወቅት የሰውነት በሺታ የመከላከል አቅምን የሚገነቡ እንደ፡ ሙዝ፣ አረንጓዴ ሻይ፣ እርጎ፣ ወተት እና ውሃ አብዝቶ መጠጣት፣ አቮካዶ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ አረንጓዴ አትክልቶች፣ ካሮት፣ ፓፓዬ፣ እንቁላል፣ ቀረፋ የመሳሰሉ የቫይታሚን መጠናቸው ከፍ ያሉ የምግብ አይነቶችን በመጠቀም ሰውነታችሁ በጭንቀት ወቅት የሚያመነጨውን ኮርቲዞልን በመቀነስ በምትኩም በሰውነት ውስጥ ጥሩ እና የመረጋጋት ስሜት የሚፈጥረውን ዶፓሚን የተሰኘ ቅመም እንዲጨምር የሚረዱ ምግቦችን መመገብ ይኖርባቸኃል፡፡

ኮሮና እና የሰውነት አቋም

ብዙ ውድድሮች በኮሮና ምክንያት መራዘማቸውን ተከትሎ ወቅቱ ፈጽሞ ስለብቃት የሚታሰብበት አይደለም፡፡ ነገር ግን አትሌቶች ይህ ጊዜ አልፎ መደበኛ ውድድሮች በሚጀመሩበት ወቅት የአካል ብቃታቸው ዝግጁ እንደሆነ እንዲቆይ ከመቸውም ጊዜ በላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተለይም ወሳኞቹ የሰውነት ክፍሎች ማለትም ጡንቻ፣ የታችኛውና የላይኛው የመተንፈሻ አካላት፣ የደም ስር ግድግዳ፣ጅማትና ሰረሰር የመሳሰሉትን ጤንነት መጠበቅ አሰፈላጊ ነው፡፡

በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን የሰውነት ክፍሎች ጤንነት ለመጠበቅ ጠቃሚ ከሆኑ የምግብ አይነቶች የተወሰኑትን ከዚህ ቀጥሎ ለመዘርዘር እሞክራለሁ፡፡

ለጡንቻ ጤንነት፡- እንቁላል፣ ስጋ (በተለይ የዶሮ)፣አኩሪ አተር፣ ባቄላ፣ ሽንብራ፣ ለውዝ ፣ወተት፣ ቡኒ፣ ሩዝ ወ.ዘ.ተ

ለሳንባ ጤንነት፡- ቀይ ስር፣ ውሃ በሎሚ፣ ብሮኮሊ፣ እርድ፣ አረንጓዴ አትክልቶች፣ምስር ወ.ዘ.ተ

ለጅማት፣ ለሰረሰር፣ ለደም ግድግዳና አጥንት ጤንነት፡- ቫይታሚን ያላቸው ምግቦች ምሳሌ ብርቱካን፣ አናናስ፣ተልባ፣ ሙዝ፣ ድንች፣ አቮካዶ፣ የእንስሳት ተዋፅኦ (በተለይ አሣ)፣ገብስ ወ.ዘ.ተ

 ኮሮና እና የሰውነት ክብደት

አትሌቶች ውድድሮች በመራዘማቸው ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ ጫና ያለበት ልምምድ አይሰሩም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚሰሩት ልምምድም ያላቸውን የሰውነት አቋም ለመጠበቅ ያለመ ሲሆን ከሰውነታቸው የሚወጣው ሀይል እና የሚገባው የግድ መመጣጠን ይኖርበታል፡ ይህም ማለት ማንኛውም አትሌት በየትኛውም የልምምድ ምዕራፍ ላይ ሲሆን አመጋገቡ ከሚሰራው የልምምድ አይነት ጋር መጣጣም አለበት ማለት ነው፡፡

በመሆኑም አትሌቶች ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጫና ያለው ልምምድ ሲሰሩ በነበረበት ወቅት ይከተሉት የነበረውን የአመጋገብ መንገድ የማያስተካከሉ ከሆነ ላልተፈለገ የክብደት መጨመርና ለተለያዩ ስፖርታዊ ጉዳቶች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም የሰውነት ክብደት እንዳይጨምር የሚረዱ ምግቦችን መመገብ ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይም አብዝቶ አለመመገብ እና ከመጠን ባለፈ መልኩ ሀይል ሰጪ ምግቦችን አለመውሰድ ጉበታችን ምግቡን ወደ ቅባትነት እንዳይቀይረው ይረዳናል፡፡ በአብዛኛው ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው፣ ፋይበር ወይም ቃጫነት ያዘሉ፣ በውስጣቸው ከፍተኛ የውሃ መጠን ያላቸው፣ አነስተኛ የካሎሪ ይዘት ያላቸው እንደ የተቀቀለ ድንች፣ የተቀቀለ እንቁላል፣ የአጃ ገንፎ፣ አሣ፣ ሾርባ፣ቀይ ስጋ፣ እርጎ፣ብርቱካን ወ.ዘ.ተ ያሉ ምግቦች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

ምንም እንኳን በወቅታዊው ችግር ምክንያት ሁሉንም ለማሟላት አስቸጋሪ ቢሆንም፡ አትሌቶች የሰውነት የመከላከል ብቃትን የሚጨምሩ፣ የጭንቀትና የድብርት ስሜትን የሚቀንሱ፣ የሰውነት አቋምን የሚጠብቁና ካልተፈለገ የክብደት መጨመርና የስፖርት ጉዳቶች የሚከላከሉ ምግቦችን አቅም በፈቀደ መጠን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ከፈለጉ ጸሀፊዋ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን ምግቦች እና ለስፖርተኞች በሚሰጡት ጥቅም ዙሪያ ላይ ያሰናዳችውን ሰፋ ያለ ጽኁፍ ቀጥሎ ያለውን ማገናኛ በማስፈንጠር ማንበብ ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያዊ ምግቦች ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች

 


ስለ ጸሀፊዋ


ቅድስት ታደሰ

የአትሌቲክስ ህክምና እና ስነምግብ ከፍተኛ ባለሙያ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *