በኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም – የግል አስተያየት

የምንገኝበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን፡ ስልጣኔ በወለደው የቴክኖሎጂ አብዮት ምክንያት ዓለም ወደ ጠባብ መንደርነት ከተቀየረ ሰነባብቷል፡፡ ከአንደኛው የዓለም ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ የሚደረገው የእውቀት እና የመረጃ ልውውጥም ከዲጂታል እና ማህበራዊ የመገናኛ መንገዶች አመቺነት የተነሳ በእጂጉ ፈጣን ሆኗል፡፡

ዛሬ በዋናነት በዚህ ጽሁፍ ልዳስሰው የፈለግኩት ዐብይ ጉዳይም፡ የማህበራዊ ትሰስር ገጾች (ሚዲያዎች) በዓለም የስፖርት ኢንደስትሪ ውስጥ እየተጫወቱ ስለሚገኙት ጉልህ ሚና እና የሀገራችን የዘርፉ ሁኔታስ ምን ይመስላል? የሚለውን ይሆናል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ ስንል፡ እንደ ስያሜው ሁሉ ማህበራዊ የሆኑ ጉዳዮቻችንን በጋራ የምንካፈልባቸው እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም አይነት የማህበረሰብ ትስስር ገጾችን ያጠቃልላል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከቴክኖሎጂ ግብዓትነታቸው ይልቅ የሰው ልጀች ልዩ ልዩ ስሜቶች እና አስተሳሰቦች ያለገደብ የሚንጻባረቁባቸው መድረኮች በመሆናቸው የተነሳ ብዙሃኑ ጋር ለመድረስ የሚፈልጉ ሁሉ በቀላሉ ኢላማ የሚያደርጓቸው እና በስፋት የሚጠቀሙባቸው የመገናኛ ዘዴዎች  ናቸው፡፡

በባህሪይው ማህበረሰባዊ የሆነው የስፖርቱ ዘርፍም ይህንን የመገናኛ ዘዴ አብዝተው እየተጠቀሙበት ከሚገኙት መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡

በተለይም ማርክ ዙክርበርግ እ.ኤ.አ 2004 ላይ ፌስቡክ የተሰኘውን የማህበራዊ ትሰስር ገጽ ለዓለም ማስተዋወቁን ተከትሎ፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሰው ልጆች የቀደሙ ማህበራዊ ግንኙነቶችን እና የመረጃ ልውውጥ ሂደቶችን ሙሉ በሙሉ መቀየር ችለዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ በመጠቀምም ብዙዎች፣ በተለይም የስፖርቱ ዓለም ዋነኛ ተዋናኞች ፕላትፎርሙን ከተግባቦት ማሳለጫነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማጠናከር እና ለሌሎች ልዩልዩ ጠቃሚ አገልግሎቶች ሲያውሉት እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

ለመሆኑ ለም የት ይገኛል?

የተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የኢንተርኔት እና የማህበራዊ ትስስር ገጸች ተጠቃሚዎች ቁጥር ዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣት በተለይም ለክለቦች፣ አትሌቶች እና በጥቅሉ ለስፖርቱ ዓለም ይዞት የመጣው በረከት ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ የየካቲት ወር 2012ዓ.ም አሀዛዊ መረጃዎች ብንመለከት እንኳን፡ በአሁኑ ወቅት በአለማችን 5.1 ቢሊዮን ህዝቦች የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ 3.8 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በየቀኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ይጠቀማሉ፡፡

ይህንን ያክል ተሳታፊ ባለበት የማህበራዊ ሚዲያ አውድ ውስጥ፡ የስፖርቱ ዋናዋና ተዋናዮች አዋጭ ስተራቴጂዎችን በመንደፍ እና አነስተኛ በሚባል ወጪ፡ የቆሙለትን መርህ የሚጋሩ እና የእኔነት እና የባለቤትነት ስሜት የሚሰማቸው እንዲሁም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም ታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች እና ምዕራባውያን ስፖርተኞች ምሳሌ የሚሆን እጅግ የተሳካ ስራ በመስራታቸው የተነሳ የውጤታማነታቸውን ፍሬ እያጣጣሙ ይገኛሉ፡፡

ማህበራዊ ሚዲያን በውጤታማነት የሚጠቀሙ ተቋማትም ሆኑ ስፖርተኞች የስኬት ሚስጥራቸው ከሁለት ዋና ዋና ነገሮች ይቀዳሉ እነርሱም ተደራሽነት እና ተዓማኒነት ናቸው፡፡

ተደራሽነት፡ ቁጥሮች አይዋሹም የሚለው ተረክ የሚሰራው እዚህ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የአንድ ቡድን ጨዋታ በቀጥታ ቢተላለፍ፡ ምን አልባትም ጨዋታው ምን ያክል ቴሌቪዥኖች ላይ ተላልፏል የሚለውን ልናውቅ እንችል ይሆናል እንጂ ምን ያክል ሰው ጨዋታውን አይቶታል የሚለውን ግን በትክክል ማወቅ አይቻልም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ግን ይሄ አይኖርም፡  ምን ያክል ተከታታይ አለኝ፣ ምን ያክሎቹስ ተመልክተውታል፣ አጋርተውታል ወይንም ተሳትፈውበታል የሚለውን በትክክል ማወቅ ይቻላል፡፡ ላለው ይጨመርለታል እንዲል፡ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ተከታይ ማለት በቀላሉ ብዙ ጥቅም ማለት ነው፡፡  ለዛም ነው ተደራሽነት ላይ ሌት ተቀን የሚሰሩት፡፡

ተዓማኒነት፡ በግልጽ ቋንቋ ሚዲያውን በአግባቡ መጠቀም ማለት ነው፡፡ የተከታዮችን እምነት የማያሳጡ፣ የሁለትዮሽ መስመራዊ ግንኙነት እና የሰጥቶ መቀበል መርህ የመሳሰሉትን በመተግበር በተደራሽነት ላይ ተዓማኒነትን መጨመር ለስኬት ያበቃል፡፡

በዚህ መንገድ ውጤታማ የሆኑ አካላት፡ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ያላቸውን ተደራሽነት እና ተዓማኒነት  በመጠቀም፡

  • ለጋራ ዓላማ የሚሰለፍ አንድ ግዙፍ ዓለምዐቀፋዊ ማህበረሰብ ይፈጥሩበታል
  • ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ያወጡ የነበረውን ወጪ ይቀንስላቸዋል
  • የሽያጭ መጠናቸውን ከፍ ያደርጋል
  • አስተማሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን ይወጡበታል፣
  • በጎ ገጽታቸውን ይገነቡበታል፡
  • የመረጃ ፍሰቱን ይቆጣጠሩበታል
  • ተከታዮቻቸውን የቅርበት ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጉበታል
  • ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያገኙበታል፣ ወዘተ…

ከላይ ከተጠቀሱት እና ሌሎች በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ጥቅሞቹ መካከል፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስለሚያገኙበት መንገድ ጥቂት ነገሮችን ለመመልከት ብንሞክር እንኳን፡ በተለይም ስኬታማዎቹ የአውሮፓ ክለቦች ከትጥቅ አቅራቢ፣ ከትጥቅ ላይ፣ ከሜዳ ዳር እና ከስታዲየም ስያሜ እና መሰል ስፖንሰሮች ጋር ለድርድር ሲቀመጡ ከሚያቀርቧቸው ዋናዋና ነጥቦች መካከል አንዱ እና ወሳኙ ክለቦቹ ራሳቸው እና  በስራቸው የሚገኙ ተጫዋቾቻቸው ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቻቸውን ቁጥር ነው፡፡ የክለቦቹ መልዕክት ግልጽ ነው፡ ከእኛ ጋር ብትሰሩ ይሄን ያክል ህዝብ ጋር ብራንዳችሁን እንደርሳለን ነው፡፡

ክለቦቹም የተለያዬ ዘዴዎችን በመከተል ያለማቋረጥ በሚዲያው አማካኝነት ከሚያስተላልፏቸው  መልእክቶች ጋር የአጋሮቻቸውን ብራንድ ጨምረው በማስተዋወቅ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ትርፋማ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የኦንላይን ሚዲያውን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስርዓቶችን በመጠቀም እንዳላቸው የተከታይ እና ተሳታፊ ብዛት: ክለቦችም ሆነ ተጫዋቾች በየአመቱ ከማህበራዊ ሚዲያው ብቻ ጠቀም ያለ እና ለማመን የሚከብድ  ቀጥተኛ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡

እዚህ ጋር በልዩ ልዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ከአራት መቶ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ፖርቹጋላዊው የጁቬንቱስ  ክለብ ተጫዋች ክርስቲኖ ሮናልዶ በእያንዳንዱ ስፖንሰርድ የተደረገ ፖስቱ የሚያገኘውን ገቢ ማየት ብቻ በቂ ይመስለኛል፤ ሮናልዶ ከ218 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ባሉት የኢንስታግራም አካውንቱ ብቻ፡ በአንድ ፖሰት አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚከፈለው ሲሆን፣ ትዊተር ላይ ለሚሰጠው ተመሳሳይ አገልግሎትም ስምንት መቶ ሰባ ሺህ ዶላር እንደሚከፈለው መረጃዎች ያሳያሉ፡ በተጨማሪም የተጫዋቹ የህይዎት ዘመን ስፖንሰር የሆነው የአሜሪካው የትጥቅ እምራች ኩባኒያ ናይኪም በሮናልዶ የማህበራዊ ሚዲያዎች ብቻ ከሚያስተዋውቃቸው ምርቶቹ በየዓመቱ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ትርፍ ያገኛል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመጠቀም ክለቦች እና ስፖርተኞች ተደራሽነታቸውን አስፍተውበታል፣ ገቢያቸውን አሳድገውበታል ከእነርሱ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶችም እንደዚሁ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡

ይህንን ሁሉ ነገር የማነሳው ዛሬውኑ እነርሱ ያሉበት ቦታ ላይ ካልተገኘን (እንገኛለን) ለማለት ሳይሆን የተቀረው ዓለም ማህበራዊ ሚዲያን ምን ድረስ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ በጥቂቱ ለማሳዬት ያክል ነው።

እኛስ?

አሁንም የየካቲት ወር 2012ዓ.ም አሃዛዊ መረጃን እዚህ ጋር ላምጣው እና በሀገራችን ኢትዮጵየ 47 ሚሊዮን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ይታመናል፤ ከእነዚህም ውስጥ 22 ሚሊዮኑ የኢንትረኔት አገልግሎትን ሲጠቀሙ 6.5 ሚሊዮኑ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያን ያዘወትራሉ፡፡ የሀገራችን ባለብዙ ማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ ክለበ ደግሞ 118 ሺህ ተከታዮች ያሉት ፋሲል ከነማ ነው፡፡

እንግዲህ በእኛ እና ቀደም ብለን በስኬታማነት ባነሳናቸው ባለተሞክሮዎች መካከል ያለው ልዩነት በጣም ግልጽ በመሆኑ ተጨማሪ ማብራሪያ አያስፈልገውም፤ ነገር ግን እነሱ የደረሱበት ጋር እንዴት እንድረስ? ለዛሬ ሁለት ነገሮችን ብቻ ልጠቁም፡፡

ትኩረት መስጠት

የስፖርት ተቋማቶቻችንም ሆኑ ስፖርተኞቻችን ይህንን በአንጻራዊነት በአነስተኛ ዋጋ የሚገኝ ነገር ግን ተያያዥ እና እጅግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጥን ሚዲያ በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት መስጠት ያሻቸዋል፡፡ የኮሙኒኬሽን ክፍሎችን ማቋቋም እና ብቁ በሆነ የሰው ሀይል ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ መሳሪያዎችን ማሟላት፣ ማቀድ፣ ጥራት ያላቸው እና ፈጠራ ያልተለያቸው ኮንተንቶችን ማቅረብ መሰረታዊ ነገሮች መሆን መጀመር አለባቸው፡፡

ትኩረት እንዲሰጠው አጥብቄ የምጠይቀው ከላይ ከዘረዘርኳቸው አንዳቸውም እንኳን የሌላቸው፣ ድረ-ገጽ እና የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት የሌላቸው በርካታ ክለቦች በሀገራችን መኖራቸውን በሚገባ ስለማውቅ ነው፡፡

ለምሳሌ ብንወስድ የጀርመኑ ክለብ ቦሩሺያ ዶርትመንድ በየአንዳንዱ የጨዋታ ቀን የክለቡን የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመረጃ፣ በፎቶ እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተግባቦትን ለመፍጠር ትጉ ሆነው የሚሰሩ 15 ባለሞያዎችን ያሰማራል፡፡

የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከእዚህም ከፍ ይላል በ15 የተለያዩ ዓለምአቀፍ ቋንቋዎች መረጃዎችን በክለቡ የማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ  66 ባለሞዎያች በስሩ ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ ይህ የሚያሳየን ስራው ምን ያክል በትኩረት መሰራት ያለበት እና አስፈላጊ መሆኑን ይመስለኛል፤ ስለዚህ ትኩረት!

በትልቁ እናስብ

ስፖርት የዓለም መግባቢያ ነው፡ ከላይ መግቢያዬ ላይ ዓለም አንድ መንደር መሆኗን ያወሳሁትም ያለ ምክንያት አይደለም፣ ለዛም ነው ታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች በልዩ ልዩ ዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች የማህበራዊ  ትስስር ገጾች ያሏቸው፡፡ ይበልጥ ይግረማችሁ እና እንደ ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ጁቬንቱስ እና ሊቨርፑል አይነት ታላላቅ ክለቦች በማህበራዊ ሚዲያ ከተወዳጇቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው መካከል በሀገራቸው የሚገኙት ከአምስት በመቶው አይበልጡም፡፡

አሁን ላይ ሊቨርፑል ውስጥ ስለሚፈጠር አንድ ነገር  ለማወቅ የግድ ሊቨርፑል መኖር እንደማይጠበቅብን እና አዲስ አበባም፣ ኳላላምፖርም፣ ቤጂንግም፣ ሊማም ሆነን መደበኛ የዜና ሰዓት ሳንጠብቅ መረጃዎችን እንደምናገኝ ሁሉ ጎንደር ላይ ስለሚከሰት ነገር ለማወቅ ሌላው ዓለምስ ለምን ጎንደር ላይ እንዲመጣ እንጠብቃለን?

የእኛ ክለቦችስ ከሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ተከታዮቻቸውን ለማብዛት እና ይህንን ለማድረግ ምን ይከለክላቸዋል? በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ እና በልዩልዩ ዓለምዓቀፍ ቋንቋዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሊጎች ውስጥ በሚጫወቱ ኢንተርናሽናል ተጫዋቾች ሀገራት ቋንቋዎች የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን ቢከፍቱ እና መረጃዎችን ቢያካፍሉ እና የተከታዮቻቸውን ቁጥር ለማብዛት ጥረት ቢያደርጉስ ምን ይከብዳቸዋል? በፈጣኑ የአለም እግር ኳስ የመረጃ ልውውጥ ሂደት ውስጥ ገብተው በንቃት ሃሳባቸውን እና አቋማቸውን ቢያከፍሉስ?

ይህ እስካሁን ለምን አልሆነም? ለሚለው ጥያቄ የአንዳንዶች ምላሽ የማህበራዊ ሚዲያው በቀላሉ መገኘት ዋጋውን አሳንሰን እንድንመለከተው ሳያደርገን አይቀርም ሲሆን፡ ሌሎች ደግሞ: የለም ከላይ የገለጽናቸውን ጠቃሚ ነገሮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ክህሎቱ ስለሌለን ነው ይላሉ፤ ሁለቱም መስተካከለል የሚችሉ እና የሚገባቸው ሀሳቦች ናቸው፡፡

የአስተሳስብ ችግር ከሆነ አሁኑኑ መቀረፍ ያለበት ለመሆኑ ከላይ ያስቀመጥናቸው ጥቅሞቹ ብቻ በቂ ምክንያት መሆን ይችላሉ፡፡ የክህሎት ችግር ከሆነ በዘርፉ የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ተቋማትን እና ግሰቦችን በመቅጠር ወይም በማማከር ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡

በመጨረሻም ማህበራዊ ሚዲያውን በአግባበቡ መጠቀም ከተቻለ፡ ወቅታዊውን የሀገራችን የስፖርት ክለቦች አንገብጋቢ የፋይናንስ ችግርን በዘላቂነት መፍታትን ጨምሮ፣ ስፖርቱን ወደ ተቋማዊ የእድገት ሽግግር ለመምራት አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል፡ ነገር ግን ይህ ዕውን የሚሆነው ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ግብ፣ ስትራቴጂ፣ ዕቅድ እና ሪሶርስ ተመድቦለት ከተሰራበት ብቻ ነው፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *