በ መንሱር አብዱልቀኒ – ለልዩ ስፖርት

የተወደዳችሁ የስፖርት ቤተሰቦች ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ አንዘናጋ፡፡ ኮሮና በመካከላችን ስላለ በመጠንቀቅ ራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና ማህበረሰባችንን ከቫይረሱ እንጠብቅ፡፡

በኮሮና ወረርሽን ምክንያት በጥቂት ሃገራት ካልሆነ በስተቀር የእግር ኳስ ውድድሮች ሁሉ ቆመዋል፡፡ መልሶ ለማስጀመርና የጀመሩትን ውድድሮች ለማጠናቀቅ ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሔ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኗል፡፡

ይህ ውሳኔ ከሌሎች ጉዳዮች የሚለየው በእግር ኳስ ባልስጣናት ሳይሆን በመንግሥታትም ጭምር የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡ ፉትቦልን በመጠቀ የአስተዳደር ክህሎትና ስትራጂካዊ አመራር የሚመሩት ሃገራት ያቃታቸውን ደካማው የሃገራችን እግር ኳስ ያሳካዋል ለማለት ይከብዳል፡፡

አባል ሃገራት የሊጎቻቸውን ዕጣ ፈንታ እንዴት ሊወስኑ እንዳሰቡ እስከ ማክሰኞ ድረስ አብራርተው እንዲያሳውቁት የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን በመጠየቁ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገር ፈጣን ውሳኔ ፈልጓል፡፡

እዚህ ላይ ስለፕሪምየር ሊጉ ብቻ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ በሃገራችን የሊግ ተዋረድ መጨረሻ ላይ እስካለው እርከን ድረስ ያሉ ውድድሮች ሁሉ እርስ በርሳቸው የተያያዙ ስለሆነ ለውሳኔ የሚመረጠው አማራጭ ሁሉንም ሊጎች ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡

ምርጡ አማራጭ ጨዋታዎችን ማከናወን ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግን ምንም አይነት እግር ኳሳዊ ውድድሮችን ከልክሏል፡፡ ስለዚህ የሰፋ የዋንጫ ዕድል ያላቸውን ቡድኖች ሰብስቦ በጥሎማለፍ እንዲለዩ የማድረጉ እድል የለንም፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ?

በእኔ እምነት እነዚህን አማራጮች እንደ መፍትሔ ሃሳብነት ለውይይት አቅርቤያለሁ፡፡

ሁሉም አማራጮች ፍጹም (Perfect) አይደሉምና ውጤታቸው የሚያስደስተው ክፍል እንዳለ ሁሉ ቅር የሚሰኝም ወገን ይፈጥራሉ፡፡ አንዳንዶቹ አማራጮች ከሌሎች አማራጮች ጋር ተመሳሳይ ውጤት (የሰንጠረዥ ደረጃ) ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ግን ደንቡ ለሁሉም ሊጎች የሚሰራ በመሆኑ እስከ ታችኛው ዲቪዚዮን ድረስ ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

አማራጭ – 1 – ከእነጭራሹኑ የ2012ቱን ውድድና መሰረዝ

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግና ብሔራዊ ሊግ ውድድሮች እንዳልተደረጉ ቆጥሮ በመሰረዝ፣ ሁሉንም መስከረም 1 ቀን 2012 ወደ ነበሩቡት ቦታ መመለስ፡፡ በዚህ መሠረት በ2011 ውድድር ያደጉት በ2013 ከፍ ባለው ሊግ ላይ፣ የወረዱት ደግሞ በታችኛው ሊግ ላይ የመጫወት ግዴታ ውስጥ ይገባሉ፡፡

አማራጭ – 2 – ሰንጠረዡ አሁን ባለበት መጨረስ

ሊጉ ከ17 ጨዋታዎች በኋላ በአስገዳጅ ሁኔታ በመቋረጡ፣ ወረርሽኙ ተፈጥሯዊ እንደመሆኑ ሁኔታውን በመቀበል ውድድሩ እዚህ ላይ እንዲያበቃ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ አማራጭ ፋሲል ከነማን ሻምፒዮን የሚያደርግና ለካፍ ቻምፒየንስ ሊግ፣ እንዲሁም መቐለ 70 እንደርታን ለካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚያበቃ ነው፡፡ ጅማ አባጅፋር፣ ወልዋሎ አ. ዩኒቨርሲቲና ሃዲያ ሆሳዕናን ወደ ከፍተኛው ሊግ የሚያወርድ ሲሆን በምትካቸው በከፍተኛው ሊግ በምድብ መሪነት ላይ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ነቀምት ከተማና አርባ ምንጭ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድጉ ያስችላል፡፡ በሌሎችም ዝቅተኛ ሊጎች ላይ በየደረጃው ተመሳሳይ ውሳኔ ይወስናል፡፡

አማራጭ – 3 – በአማካይ ነጥብ በጨዋታ መለየት

በጨዋታ አማካይ ነጥብን (Points Per Game) የተከተለ የሰንጠረዥ ደረጃ ተዋረድ ማውጣት፡፡ ክለቦቹ በ17ቱ ዙር ባገኙት የጨዋታ አማካይ ነጥብ ሲደረደሩ የሚከተለውን ቅደም ተከተል ይይዛሉ፡፡

1. ፋሲል ከነማ …1.76ነጥብ
2. መቐለ 70 እንደርታ… 1.7 ነጥብ
3. ቅ/ጊዮርጊስ….1.65ነጥብ
14. ጅማ አባ ጅፋር… 1.12 ነጥብ
15. ወልዋሎ አ. ዩ. …1.06
16. ሃዲያ ሆሳዕና …0.06
ይህ አማራጭ በተራ ቁጥር 2 ላይ የቀረበው ሃሳብ ከሚያስገኘው የደረጃ ቅደም ተከተል ጋር አንድ ዓይነት ውጤት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን እኩል ጨዋታን ላልተጫወቱ የታችኛው ዲቪዚዮን ክለቦች ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡

አማራጭ – 4 – ለቀሪ ጨዋታዎች አማካይ ነጥብ መስጠት

እያንዳንዱ ክለብ 30 ጨዋታ በሚጫወትበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዝን ዘንድሮ ማድረግ የተቻለው 17ቱን ብቻ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ተሳታፊ 13 ግጥሚያዎች ይቀራሉ፡፡ ጨዋታዎቹ ባለመደረጋቸው ለቀሪዎቹ ግጥሚያዎች ለቡድኖቹ ነጥብ መስጠት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ቀደም ባሉት 17 ጨዋታዎች በጨዋታ በአማካይ ያገኙትን ነጥብ በቀሪዎቹ 13 ግጥሚያዎችም እንዲያገኙ በመስጠት በምናገኘው ድምር ውጤት ደረጃቸውን ለመለየት ይህ አማራጭ ይረዳል፡፡

መሪውን ምሳሌ አድርገን እንየው፡፡

ፋሲል ከነማ

• ከ17ቱ ጨዋታ በአማካይ ያገኘው አማካይ ነጥብ፡- 1.76
• 1.76 X 13 = 22.88
• ፋሲል አሁን ያለው ሙሉ ነጥብ፡- 30
• ድምር፡- 52.88 ነጥብ

በዚህ መሰረት የሰንጠረዡ አናት የሚከተለውን መልክ ይይዛል፡፡

1. ፋሲል ከነማ …52.88 ነጥብ
2. መቐለ 70 እንደርታ ….51 ነጥብ
3. ቅ/ጊዮርጊስ…50ነጥብ

አማራጭ -5 – በ2011 ውጤት ላይ የተመሰረተን መጣኝ (Coefficient) ማስላት

የዘንድሮው ውድድር ባለመጠናቀቁ ምክንያት የክለቦቹን የአምና ውጤት ታሳቢ ያደረገ Coefficient በማዘጋጀትና ይህንን አሃዝ፣ በአማካይ ነጥብና አማካይ ጎል ጋር በመደመር የ2012ቱን ሊግ የክለቦች ደረጃ ማውጣት፡፡ በዚህ መቐለ 70 እንደርታ የአምናው ሻምፒዮን በመሆኑ ከፍ ያለ ነጥብ የማግኘት ዕድል ያገኛል፡፡ ግን ወደ በ2012 ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀሉ ክለቦች ያነሰ መጣኝ ስለሚይዙ ሊጎዱ ይችላሉ፡፡

አማራጭ -6 – ነጥብ፣ ያስቆጠረውን ጎልና የተቆጠረበትን ጎል ያካተተ ፎርሙላ

ይህ አማራጭ በስፖርታዊ ብቃት (Sporting Merit) ላይ የተመሰረተን ግልግል ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡ በሊግ ሰንጠረዥ ላይ ነጥብ፣ የጎል ክፍያና ጎል (አገባ፣ ገባበት) የሚሉት መመዘኛዎች የክለቦችን ወቅታዊ ደረጃ ለመለየት እንደሚያስችል ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት የሚከለተውን ፎርሙላ መከተልና የሰንጠረዥ ቅደም ተከተልን መለየት፡፡

ፎርሙላው፡- በጨዋታ አማካይ ነጥብ + በጨዋታ አማካይ ያስቆጠረው ጎል – በጨዋታ አማካይ የተቆጠረበት ጎል = ድምር ነጥብ
(Avg pts/game + Avg goal for/game – Avg goal against/game) = Total Points

ለምሳሌ፡-
1. ፋሲል ከነማ… 1.76 + 1.53 -0.765 = 2.525
2. ቅ/ጊዮርጊስ …1.647 + 1.29 – 0.765 = 2.172
3. መቐለ 70 እንደርታ …1.705+1.235 -0.88 = 2.06

በዚህ አማራጭ መሰረት ፋሲል የ2012 ሻምፒዮን ሆኖ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ ወደ ካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ያልፋል፡፡ ሌሎችም በዚሁ ስሌት ደረጃቸውና ዕጣ ፈንታቸው ይወሰናል፡፡

ፌዴሬሽኑና የሊጉ ኩባንያስ ከቀረቡት አማራጮች የትኛውን ይመርጡ ይሆን? ወይስ ከእነዚህ የተለየ ሌላ ሃሳብ ያመጡ ይሆን?


ስለ ጸሀፊው


መንሱር አብዱልቀኒ (ጋዜጠኛ)

በብስራት ኤፍኤም 101.1 የሚተላለፈው ዕለታዊዉ የብስራት ስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *