በ ዐቢይ ሐብታሙ – ለልዩ ስፖርት

መንደርደሪያ

ማሳጅ ማለት በሰውነት ውስጥ ያሉ አንድ ዓይነት የኾኑ ለስላሳ የህዋሳት ቡድን (Soft Tissues) ቁጥጥር ነው። ከሰማንያ በላይ የማሳጅ ዓይነቶች እንዳሉ ጥናቶች ይገልፃሉ። ሁሉም የየራሳቸው ባህሪያት ሲኖራቸው ሰውነትን ከማፍታታት እስከ መዝናኛነት፣ ከህመም ለማገገም፡ ህመምን እስከ መቆጣጠር የሚደርሱ ፋይዳዎች ይሰጣሉ።

የማሳጅ ታሪካዊ ዳራ

ማሳጅ ጥንታዊ ከኾኑ የአካል ችግሮች ማስወገጃ (Physical Therapy) ዓይነቶች ውስጥ የሚመደብ ሲኾን፡ ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት እንደ ቻይና፣ ህንድና ግሪክ ባሉ ሀገራት ውስጥ ይዘወተር እንደነበር ይታመናል።

በአንፃሩ ወደ ምዕራቡ ዓለም ለመድረስ ደግሞ ዘመናትን ወስዶበታል። ይህ ልምምድ በስፋት እንዲተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ ባለሙያዎች መካከል ሲዊድናዊው ፔህር ሄኔሪክ ሊንግ (1776 – 1839) ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።

ሊንግ ሲዊዲሽ ማሳጅ እየተባለ የሚጠራውን የማሳጅ ዓይነት ለዓለም ያስተዋወቀ ሰው ነበር። ‘የሲዊዲሽ ማሳጅ አባት’ እያሉም ይጠሩታል። በሂደት የሻሞላ ተጨዋቾች (Fencess) እንዲሁም የጂምናስቲክ አትሌቶች ዓለማቀፍዊ እውቅና ለማግኘት የሚረዳቸውን የራሱን የማሳጅ ስልቶችንና አካላዊ እንቅስቃሴዎችን አዳብሯል።

ሊንግ የበርካታ አዎንታዊ እሳቤዎች (Positive Thoughts) አቀንቃኝ ነበር። ከሀሳቦቹ ገሚስ ያህሉ ለዘመናዊ ስፖርት ማሳጅ መሰረቶችን ጥለዋል።

ዛሬ ላይ ጤናና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚረዱ የተለያዩ የማሳጅ ዓይነቶች ይገኛሉ። ስፖርት ማሳጅ ከበርካታ ዓመታት በፊት በአሜሪካ፣ ካናዳና አውስትራሊያ ተቀባይነት ሲያገኝ በዩናይትድ ኪንግደም ዘንድ ግን በስፋት ተቀባይነት ያገኘው በ1990ዎቹ ነበር።

ስፖርት ማሳጅ ምንድን ነው?

ስፖርት ማሳጅ በመደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ስፖርተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የለስላሳ ቲሹዎች (Soft Tissues) ቁጥጥርን (Manipulation) ያካተተ የማሳጅ ዓይነት ነው። ለስላሳ ቲሹዎች የሚባሉት ደግሞ ቆዳ፣ ጡንቻዎች፣ ቴንደንስና ሊጋሜንትስ ናቸው።

ስፖርት ማሳጅ መሰጠት ያለበት ተደጋጋሚና ጠንካራ በኾኑ አካላዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም አዕምሮን የሚያዛባ ገጠመኝ (Trauma) ሳቢያ ለስላሳ ቲሹዎች ላይ የሚከሰቱ ችግሮችንና ሚዛን አለመጠበቆችን (Imbalancements) ለማስተካከል ስለሚያገለግል ነው።

ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በፊት ኾነ በኋላ የሚሰጥ ስፖርት ማሳጅ የብቃት ደረጃን ያሻሽላል፣ከእክል ለማገገም ይረዳል በተጨማሪም የጉዳት ቅድመ መከላከል አንድ አካል ይኾናል።

ስፖርት ቴራፒ ምንድን ነው?

ስፖርት ቴራፒ እጅግ ሰፊ ክህሎትና ደጋፊ እውቀቶችን የያዙ የልምምድ ከፍተኛ ደረጃዎች ናቸው። የሚከተሉትን ቁልፍ ነጥቦችን በስራቸው ያካትታሉ።

፨ አናቶሚ አና ፊዚዮሎጂ
፨ ስፖርት ማሳጆች
፨ ስነ ምግባርና ፕሮፌሽናሊዝም
፨ ባዮሜካኒክስ
፨ የቴራፒ ክህሎት አድቫንስድ ማንዋል
፨ ከጉዳት ማገገም
፨ ስለጉዳት ጥናትና ህክምና
፨ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ
፨ ከጉዳት በኋላ የሚከሰት እጅግ አስደንጋጭና የሚያቃዥ ተሞክሮን (Trauma) መከላከል
፨ ኤሌክትሮ ቴራፒ
፨ ጥንካሬና ኮንዲሽኒንግ
፨ አመጋገብ

አናቶሚና ፊዚዮሎጂ

ስለሰውነት መዋቅርና አተገባበሩ የሚገልፁ እውቀቶችን መረዳት የስፖርት ማሳጅ ጽንሰ ሃሳብ (Theory of Sport Massage) መነሻ ነጥብ ነው። አንድ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ሰውነት እንዴት መደበኛ ተግባሩን እንደሚያከናውን፣ ይህ መደበኛ ተግባር በምን ዓይነት ነገሮች እንደሚስተጓጎልና ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚፈጠርበት በተረዳ መጠን ሰዎችን ምን ማማከር እንዳለበት በርግጥም ያውቃል።

አጭር መግለጫ

አናቶሚ፡ የሰውነት መዋቅርና ክፍሎቹን ያጠናል።

ፊዚዮሎጂ፡ ሰውነትና ስርዓቶቹ እንዴት መደበኛ ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ያጠናል።

የስፖርት ማሳጅ ጥቅሞች (Benifits of Sport Massages)

ስፖርት ማሳጅ ጠቃሚ ነው ሲባል በምክንያት ይኾን? አዎ! እውነት ነው። በስፖርቱ ዘርፍ የተሻለ እውቀትና ግንዛቤ ተፈጥሮባቸዋል በሚባሉት ምዕራባዊያን ዘንድ ስፖርት ማሳጅ ፋይዳ ብዙ መኾኑ ይነገርልታል። ከቅድመ ጨዋታ አሊያም ውድድር ዝግጅት፣ ፐርፎርማንስ፣ ድህረ ፐርፎርማንስ፣ ከህመም ማገገም ጋር በተገናኘ ከፍተኛ አስተዋኦ ያበረክታል። በተጨማሪም ማሳጅ ስፖርትን እንጀራዬ ብለው ከያዙት እንደ መዝናኛነት እስከሚያዘወትሩ ሰዎች ድረስ ቀዳሚ ተመራጭ ነው።

የማሳጅ ጥቅሞችን በሚመለከት ግልፅ የኾነ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚረዱ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን ማንሳት ማለፊያ ሃሳብ ነው። አንደኛው አዕምሮአዊ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ አካላዊ ጥቅሞች ናቸው።

ዝርዝር ጥቅሞች

፨ የመገጣጠሚያዎች እንቅስቃሴ ደረጃን ይጨምራል።
፨ የሰውነት ቅልጥፍናን ያሳድጋል
፨ የሰውነት መተጣጠፎችን ይጨምራል
፨ አላስፈላጊ የጡንቻ ውጥረቶችን ያረግባል
፨ ነርቮችን በማፍታታት ኒሮሎጂካል መሸበሮችን ያስወግዳል
፨ ድንገተኛ የጡንቻ መኮማተርን (Muscle Spam) ይቀንሳል
፨ ድካምን ያስወግዳል
፨ በካንሰር ሳቢያ የሚመጣ ህመምን ያስታግሳል
፨ የደም ግፊትን ያስተካክላል
፨ በመኝታ ሰዓት ጎንን በሰላም ለማሳረፍ ያግዛል

ተጨማሪ ሃሳቦች

በስፖርት ማሳጅ ጥቅሞች ዙሪያ በመላው ዓለም በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል። ለአብነት ያህል በሀገረ አሜሪካ የተደረገ ጥናትን ማንሳት ይቻላል። ጥናቱ የተደረገው ከሐምሌ 2016 እስከ ሐምሌ 2017 ሲኾን ለምላሽ ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች መካከል 89% የሚኾኑት ማሳጅ ለህመም ፈውስ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከጤና ባለሙያዎች ወገን 69% የሚኾኑት ደግሞ ህመምተኞቻቸው ማሳጅን እንዲጠቀሙ ይመክራሉ።

ይቀጥላል

ቸር ያሰንብታችሁ!


ስለ ጸሀፊው


ዐብይ ሐብታሙ

መምህር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

1 Comment

  1. መልካም ሀሳብ ነው። በቀጣይ ጽሁፎቹ የተሟላ እንደሚሆን አስባለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *