በ ዐቢይ ሐብታሙ – ለልዩ ስፖርት

መንደርደሪያ ሃሳብ!

የብሽሽት ጉዳት በርከት ያሉ ሩጫዎችና ዝላዮችን የሚጠይቁ ስፖርቶች ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በተለይም በእግር ኳስ ተጫዋቾች ዘንድ የተለመደ ነው።

ድንገተኛ ዝላይና አቅጣጫ ቅየራዎች ከብሽሽት ጉዳት ክስተት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ነገሮች ናቸው።

ብሽሽት ( Groin) ምንድን ነው?

በሰውነት ክፍሎች ጥናት (Anatomy) መሰረት በሆድና ጭን (thigh) መሃከል ያለ ወደ ሁለቱም የጭን አጥንቶች (Pubic bones) የሚቀርብ የመገናኛ ክፍል (junctional area) ብሽሽት ይባላል።

በሳይንሰ Inguinal canal ወይም Inguinal region ተብሎ ይጠራል።

የብሽሽት ጉዳት ምንነት

የጭን ወይም የብብሽት ጡንቻዎች (Thigh or Groin Muscles) ላይ ከመጠን ያለፈ ጫና ሲያርፍባቸው የሚከሰት እክል ነው። እነዚህ ጡንቻዎች ደግሞ ጫና ሲበዛባቸው አሊያም ድንገት ሲወጠሩ ከመጠን በላይ ይለጠጣሉ አሊያም ይተረተራሉ።

የብሽሽት ጉዳት ስሜቶችና ምልክቶች

፨ የብብሽትና የጭን ውስጣዊ ክፍል ማበጥ ወይም መቆጣት

፨ ሁለት እግሮችን አንድ ላይ በማንሳት ሂደት ላይ የህመም ስሜት ይኖራል

፨ ጉልበት ሲነሳ ህመም ይሰማል

፨ በጉዳት ወቅት ለየት ያለና ያልተለመደ ዓይነት ድምፅ ሊሰማ ይችላል።

፨ የበረታ ህመም ስሜት መፈጠር።

የጉዳቱ ደረጃዎች (Degrees of the Injury)

ከጉዳቱ አሳሳቢነት (Sevierity level) አኳያ በሦስት ደረጃዎች ይከፈላል። አነርሱም የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ይባላሉ።

የመጀመሪያ ደረጃ (Grade 1)

ጉዳቱ መጠነኛ ቢኾንም ከ25% የሚያንሱ የደም ስሮች ላይም እክል ይፈጠራል። አነስተኛ ህመም፣ ጥንካሬን ማጣትና እንቅስቃሴ ለማድረግ መቸገር ምልክቶቹ ናቸው።

ሁለተኛ ደረጃ (Garde 2)

ከ25% የሚልቁ ደም ስሮች ይጎዳሉ። መካከለኛ ህመም፣ መልፈስፈስ፣የአንዳንድ ቲሹዎች ውድመት ተጠባቂ ነገሮች ናቸው።

ሦስተኛ ደረጃ (Grade 3)

ከፍተኛ ህመም፣የጡንቻዎች ሙሉ ለሙሉ መተርተርን ተከትሎ ከጥንካሬ አኳያ አቅመ ቢስነት ይፈጠራል።

የትኩረት ነጥብ፡ አንድ

የጉዳቱ መጠን በባለሙያዎች በሚከናወን ጥብቅ አካላዊ ምርመራ (Thoroughly physical exam) ሊታወቅ ይችላል። ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ደግሞ እንደ ሁኔታው በX rays እና MRI በሚታገዙ ምርመራዎች ይታወቃሉ።

የማገገሚያ መንገዶች (Rehabilitation Ways)

መልካሙ ዜና! የብሽሽት ጉዳቶች በአመዛኙ በራሳቸው መንገድ የመዳናቸው ዕድል ሰፊ መኾኑ ነው። ይሁንና እንደ ስፖርተኛ ግን የሚጠበቁ ተግባራት ይኖራሉ። ለምሳሌ በቂ ዕረፍት ማድረግ ወይም ፋታ መውሰድ ፈውስን ያፋጥናሉ።

ዝርዝር የማገገሚያ መላዎች

፨ የታፋ(ጭን) ውስጠኛ ክፍልን በበረዶ መያዝ። ለተከታታይ ሦስት ቀናት አሊያም እንደ አስፈላጊነቱ የህመም ስሜቱ እስኪጠፋ ድረስ በየሦስት ወይም አራት ሰዓታት ልዩነት ከሃያ እስከ ሰላሳ ደቂቃዎች ያህል በረዶ መያዝ ተመራጭ ነው።

፨ የተጎዳው የሰውነት ክፍል አካባቢ በተለጣጭ ፋሻ (Elastic Bandage) ወይም ፕላስተር መጠምጠም።

፨ የህመም ማስታገሻዎችን ( Pain killers) መወሰድ የሰውነት መቆጣት (Inflammation) እንዳይፈጠር ይረዳሉ። Neosteroidal Anti Inflammatory Drugs (NSAIDS) ይባላሉ። እንደ Ibuprofen እና Naproxen አይነቶች ደግሞ የህመም ስሜትን ያስታግሳሉ እብጠትንም ይቀንሳሉ።

የትኩረት ነጥብ፡ ሁለት

ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ መድሐኒቶችን ለረጅም ጊዜያት የሚወሰዱ ከኾነ ውጤቶቻቸው አወዛጋቢ ይኾናሉ። የጎንዮሽ ጉዳትም (Side effect) ሊኖራቸው ይችላል። በተለየ ሁኔታ በባለሙያ ካልታዘዘ በቀር አልፎ አልፎ ብቻ መጠቀም ይመከራል።

ተጨማሪ ሃሳቦች

የተጎዱ ቲሹዎች እንዲያገግሙ ከህክምና ባለሙያ ጋር እተመካከሩ ቀለል ያሉ ማሳሳቦችና ለጥንካሬ የሚረዱ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ጥሩ ነው። አንድ ስፖርተኛ እንደሚገኝበት የጉዳት ደረጃ ወዲያው አሊያም ከበርካታ ቀናት ዕረፍት በኋላ መጀመር ይችላል።

የማገገም ጉጉትና ጭንቀት

ከጉዳቴ በፍጥነት አገግሜ እንዴት ወደ ጨዋታ ወይም ወደ ውድድር መመለስ እችላለሁ? ህመሙስ ምን ያህል ሊዘልቅ ይችላል? የመሳሰሉት በስፖርተኞች አዕምሮ ውስጥ የሚመላለሱ የተለመዱ ጥያቄዎች ናቸው። በእርግጥ ምላሽ መስጠት የመጠየቅ ያህል ቀላል ላይኾን ይችላል።

የማገገሚያ ጊዜያት የሚወሰኑት በጉዳቱ አሳሳቢነት ደረጃ ነው። ለምሳሌ ከ4 – 6 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።

ቅድመ መከላከል (Prevention of the Injury)

የብሽሸት ጉዳት ስቃይ የበዛበትና አድካሚ ቢኾንም ‘ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ’ ይበጃልም አይደል ነገሩ! ስለዚህ አስቀድሞ የመከላከል መላዎችን መዘየዱ ተመራጭና አዋጪ ነው።

፨ ከየትኛውም አካላዊ እንቅስቃሴ በፊት ሰውነትን እያፍታቱ ማሟሟቀ፣ ለምሳሌ የሰውነት ሙቀትን ለመጨመር የሚከናወኑ ዝግ ያሉ ሩጫዎችና የመሳሰሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎች የጡንቻ መተርተር ተጋላጭነትን ይቀንሳሉ።

፨ የሰውነትን የጋለ ስሜት (Intensity) በዝግታ ለመጨመር ጥረት ማድረግ። ቢቻል በሳምንት ከ10% በላይ ከፍ ባይል ይመከራል።

፨ ብሽሽት አካባቢ አሊያም ከታፋ ስር የህመም ስሜት በሚፈጠርባቸው ጌዜያት አካላዊ እንቅስቃሴን መግታት ወይም ሙሉ ለሙሉ ማቆም።

፨ ከዚህ ቀደም የብሽሽት ጉዳት ከነበረ የተጎዱ ጡንቻዎችን የሚያጠነክሩ መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን።

ቸር ያሰንብታችሁ!


ስለ ጸሀፊው

ዐቢይ ሐብታሙ

መምህር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *