በ ዐቢይ ሐብታሙ – ለልዩ ስፖርት

ጤና ይስጥልኝ ውድ የልዩ ስፖርት ድረ-ገፅ ቤተሰቦች!

ባሳለፍነው ሳምንት ስለ ጉልበት ጅማት መበጠስ ጉዳት ምንነት፣ የሰውነት መዋቅር (Anatomy)፣ መንስኤዎቹና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች አንስቼላችሁ ነበር። በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ቃል በገባሁት መሰረት ስለ ጉዳቱ ቅድመ መከላከልና የህክምና ሂደቶች ተጨማሪ መሰረታዊ ሃሳቦች አካፍላችኋለሁ።

ACL የፕሮፌሽናሎች ብቻ ሳይኾን በአማተርነት ደረጃ ያሉ ስፖርተኞችም ችግር ነው። በታዳጊነት እድሜ ላይም ሊከሰት ይችላል።

ስለ ታዳጊነት ካነሳን አይቀር አንድ ወዳጄ የነገረኝን ግለ ታሪክ ላጫውታችሁ።

በግምት ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት ስኩል ኦፍ ቱሞሮ እግር ኳስ ጨዋታን ያዘወትር ነበር። እርሱ እንደሚለው፡ ስልጠናው ከሀገር ውጭ ሰልጥነው በተመለሱ አሰልጣኞች ይሰጥ ነበር። በግልም ኾነ በቡድን የሚሰጣቸውን ትዕዛዛት በትክክል ይፈፅማሉ። ይኸኛው ደግሞ በግሉ ይሰጡት ከነበሩ ትዕዛዛት ውስጥ አንዱ እንደነበር ያስታወሳል።

“በጨዋታ ወቅት ግራ እግሬን የበለጠ እንድጠቀም ምክር ይሰጠኝ ነበር። አንድ ቀን ግራ እግሬ ከኳስ ጋር እንቅስቃሴ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ባላንሴን ሳትኩ። ያልታሰበ ነገር ተፈጠረና ጉልበቴ ተጎዳ። የልጅነት አዕምሮ ኾኖ መጎዳቴን እንጂ ጉዳቴ ምን እንደነበር አላወቅኩም።”

ከጉዳቱ ማግስት ነገሮች በጥሩ መልኩ አልተጓዙም። ለሁለት ወራት ያህል ጉልበቱ ራደ። ውሃም ቋጠረ። በህክምና ፈሳሹ ተወግደለት። ይሁንና በጊዜው እንደ MRI ያለ ህክምና አለመኖሩ ለመዳን ጊዜ ወሰደበት።

የደረሰበት ጉዳት ደረጃ መለስተኛ መኾኑ፣የልጅነት ገላውም ታክሎበት ደህና ኾነ እንጂ ነገርዬው የከፋ ሊኾንበት ይችል ነበር።

ዓመታት ነጉደዋል። ባለታሪካችን የጉርምስና እድሜን ተሻገሮ 30ዎቹን ይዟል። በወቅቱ የደረሰበት ጉዳት ትዝታ ብቻ የኾነ ቢመስልም ሰዓታትን መቀመጥ የሚጠይቁ ማንኛቸውም ኹነቶች በሙሉ ህመሙን ይቀሰቅሱበታል።

በርካታ ታዳጊዎችና ወጣቶች በየትምህርት ቤቶች፣ የእግር ኳስ አካዳሚዎች፣በየሰፈሩ አስፖልትና አቧራማ ሜዳዎች ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያዘወትራሉ። ጥያቄው “የግንዛቤ እጥረትና ህክምና እጦት ስንቱን ከልጅነት ህልማቸው ለያይቷቸው ይኾን?” የሚለው ነው። ለማንኛውም ዐቢይ ትኩረታችን ኤ ሲ ኤል እንደ መኾኑ መጠን ስለ ቅድመ መከላከልና ህክምና ሂደቱ ሳይንሳዊ መላዎችን እነሆ!!!

ቅድመ መከላከል (Prevention of ACL)

ተገቢ የኾኑ የስልጠና ስርዓትና አካላዊ እንቅስቃሴዎች የኤ ሲ ኤል ተጋላጭነትን ይቀንሳሉ። የስፖርት ዶክተሮች፣ ቴራፒስቶች፣ አሰልጣኞች እንዲሁም በስፖርት ህክምና ውስጥ ያሉ ባለሟሎች (Specialists) የኤ ሲ ኤል ተጋላጭነትን ለመቀነስ ክትትል፡ ግምገማ፣ መመሪያና ግብረ መልስ መስጠት ይችላሉ።

ጉዳቱን ለመቀነስ የሚረዱ መርሃ ግብሮች (Programs to Reduce ACL Injury)

ለየት ያሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር

በተለይ እንደ ጡንቻ ማሳሳቦች (Hamstring Exrecises) ያሉ እንቅስቃሴዎችን በመጠኑ ማከናወን በእግር ጡንቻዎች ጥንካሬ መሃከል ባላንስን ይፈጥራሉ።

ሰውነትን እያፍታቱ ማሟሟቅ (Proper Body Warm)

ከውድድር በፊት ሰውነት እየተፍታታ እንዲሞቅ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ይመክራል። ለምሳሌ የተመረጡ እንቅስቃሴዎችና ማሳሳቦች (specific exercise & stretches) ሰውነትን በማሟሟቅ ጡንቻዎችን ከመተርተር ይታደጋሉ።

ሰውነትን የሚያጠነክሩ ልምምዶችን ማከናወን

እንደ ሽንጥ፣ የዳሌ አጥንት እንዲሁም የሆድ ታችኛው ክፍል ያሉ የሰውነት ክፍሎችን ለማጠናከር የሚረዱ እንቅሴዎችን ማድረግ።

ቅልጥፍናን ማጎልበት

በክፍል አንድ ጽሑፌ እንደ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎች ድንገተኛ ለውጦችን ሲያስተናግዱ የኤ ሲ ኤል ከፍተኛ ተጋላጭነት አንደሚፈጠር ጠቁሜ ነበር። ስለዚህ እንደ ከቲንግ (cutting) የቅልጥፍና እንቅስቃሴዎችን በመለማመድ ጥሩ አቋም መፍጠር ይቻላል።

የዝላይ ቴክኒኮችን ማዳበር

ዝላይ በሚጠይቁ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ያሉ ቴክኒኮችን በግል ኾነ በባለሙያ እገዛ ማዳበር ይቻላል። አንዱ ቴክኒክ የጉልበት አቀማመጥና የመሬት አስተራረፍ ክህሎት (knee positioning & landing skills) ነው።

የመሬት አያያዝና አቅጣጫ ቅየራ ክህሎትን ማዳበር

በአቅጣጫ ቅየራና ከዝላይ መልስ መሬት በማረፍ ወቅት ጉልበቶችን በተገቢው መልክ አለመጠምዘዝ (Improper knee bend) እግሮች ላይ ከፍተኛ ጫናን በማሳረፍ የኤ ሲ ኤል ተጋላጭነት ይጨምራል።

ስለ ዝላይ ክህሎት ማዳበር ተጨማሪ ምክረ ሃሳቦች

– መሬት ከማረፍ በፊት ጉልበቶችን ሸብረክ ማድረግ

– ሁለቱም እግሮች በትይዩ መስመር መኾናቸውን እርግጠኛ መኾን (በሥልጠናና ልምምድ ይዳብራል)

– በተቻለ መጠን እግሮችን አለማጠባበቅ (በሥልጠናና ልምምድ ይዳብራል)

– ከዝላይ መልስ ከውስጥ አግር ወደ ፊት ጠጋ ብሎ በሚገኝ ክፍል ማረፍ ከዚያም ተረከዞችን ማስከተል።

– ዳሌን ከጉልበቶች አሰላለፍ ጋር ማወዳጀት (አሰላለፍ ሲባል አላይመንትን ለመግለፅ ነው)

– ከወገብ በላይ ያለ የሰውነት ክፍልን ቀጥ ማድረግ። ወገብን ያለቅጥ ወደፊት ኾነ ወደ ኋላ አለማጠፍ

– መሬት ላይ በአንድ እግር አለማረፍ። ካልተቻለ ግን ክብደትን በተስተካከለ መልኩ በማሰራጨት የዘገየውን አግር በፍጥነት አሰከትሎ ማሳረፍ

ከጉዳት በኋላ ያሉ የህክምና ሂደቶች (Medical Procedures After Injury)

ምርምራ (Diagnosis)

የህክምና ባለሙያዎች በሚያደርጉት አካላዊ ምርመራ እብጠት አሊያም ስብራት የደረሰበትን ጉልበት ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ የተጎዳውን እግር ከጤነኛው ጋር ሊያነፃፅሩ ይችላሉ። ሌላው የጉልበት እንቅስቃሴ መጠንና አጠቃላይ ተግባርን ለመረዳት ጉዳተኛውን ወደ በርካታ ቦታዎች ሊያንቀሳቅሱት ይችላሉ።

ህክምናው በዋነኝነት ከአካላዊ ምርመራ ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ ቢኾንም ተዛማጅ መንስኤዎችንና የጉዳቱን ደረጃ ለይተው የሚያሳውቁ ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ።

ኤክስሬይ (X-rays)

ኤክስሬይ የአጥንት ስብራትን ይለያል። ይኹንና እንደ ጅማትና ቴንደን ያሉ ለስላሳ አንድ ዓይነት የሰውነት ህዋሳት ቡድንን (Tissues) ግን አያሳይም።

ኤም አር አይ (MRI)

ምህፃረ ቃሉ ሲተነተን ማግኔቲክ ሪዞናንስ ኢሜጅ ነው። የተጎዳ የሰውነት ክፍልን አጉልቶ ያሳያል። ራዲዮ ሞገዶች (Radio waves) እንዲሁም መግነጢሳዊ ፊልድ (Magnetic field) መተግበሪያዎቹ ናቸው። በሰውነት ውስጥ ያሉ ለስላሳና ጠንካራ ቲሹዎች ምስሎችን ይፈጥራሉ።

ኤም አር አይ ጉዳት መጠንን እንዲሁም ካርቲሌጆችን ጨምሮ በጉልበት ውስጥ ያሉ ሌሎች ቲሹዎች ውድመት ምልክቶችን ያሳያሉ።

አልትራሳውንድ (Ultrasound)

አልትራሳውንድ የድምፅ ሞገዶችን (Sound Waves) በመጠቀም ውስጣዊ መዋቅሮችን ለማየትና የጉልበት ጅማቶች፣ አጥንቶችንና ጡንቻዎች ጉዳቶችን ያረጋግጣል።

ማስታወሻ፡- ከእነዚህ ሁሉ የህክምና በፊት ስፖርተኛው ጉዳት ባስተናገደበት ሰዓት የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ዕርዳታ (First Aid Treatment) ካገኘ ፅኑ ህመሙና እብጠቱ ሊቀንስለት የሚችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የቤት ውስጥ እንክብካቤ ሞዴል (Home care model)

ከህክምና በኋላ ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ቀለል ያሉ ተግራት ከህመም በፍጥነት ለማገገም ይረዳሉ። ግለ ክብካቤ (Self Care) ናቸው። እነርሱም R.I.C.E በሚል ምህፃረ ቃል ይታወቃሉ።

R – REST
I – ICE
C – COMPRESSION
E – ELEVATION

REST (ዕረፍት)

ዕረፍት ማድረግ ቁስሉ ጠገግ፣ የህመም ስሜቱም ጋብ እንዲልና ጉልበት ላይ ያለ ጫና እንዲቀንስ አስተዋፅኦው ላቅ ያለ ነው።

ICE (በረዶ)

ነቃ የማለት ደረጃ ላይ ሲደረስ በየሁለት ሰዓታት ልዩነት ቢያንስ ለሃያ ደቂቃዎች በረዶ ጉልበት ላይ ማድረግ። ከተቻለ በረዶውን በአይስ ባግ አድርጎ መያዝ ይመከራል።

COMPRESSION (ማመቅ)

በተጎዳው ጎልበት ዙሪያ የላስቲክ ባንዴጅ ወይም ኮምፕረሽን በጥንቃቄ መጠምጠም።

ELEVATION (መስቀል)

የተጎዳውን እግር ዘርግቶ የተደራረበ ትራስ ላይ ከፍ አድርጎ መስቀል።

ቸር ያሰንብታችሁ!!!


ስለ ጸሀፊው


ዐቢይ ሀብታሙ

መምህር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *