በ ዐቢይ ሐብታሙ – ለ ልዩ ስፖርት

ጉዳት ለስፖርተኞች መፈተኛቸው ነው፤በተለይ አንዳንድ ጉዳቶች ከባድ ፈተናዎች ይኾናሉ። የጉልበት ጅማት መበጠስ ወይም መተርተር እክል ደግሞ ከነዚህ ፈተናዎች ውስጥ የሚመደብ ነው።

በሳይንሳዊ ስሙ አንቲሪየር ክሩሺየት ሊጋመንት (Anterior cruciet ligament) ይባላል ወይም ባጭሩ ACL ብለን ልንጠራው እንችላለን።

ከሚወዱት ስፖርት በኤ ሲ ኤል ሳቢያ የተደናቀፉ ስፖርተኞች በጉዳቱ የራደው ጉልበታቸው በርትቶ ዳግም ወደ ሙያቸው ይመለሱ ዘንድ ቀዶ ጥገና ማድረግ የግድ ይኾንባቸዋል።

ምንም እንኳን ሁሉም ኤ ሲ ኤል ጉዳቶች በተመሳሳይ የህክምና ሂደት ውስጥ ማለፍ ይኖርባቸዋል ማለት ባይቻልም የጉዳቱ አሳሳቢነት (severity of the injury) እንዲሁም ስፖርተኞቹ ተሳታፊ የኾኑበት የእንቅስቃሴ ደረጃ (Activity level) ከግምት ውስጥ የሚገቡ ቁልፍ ነገሮች ናቸው።

ከፍተኛ እንቅስቃሴ፣አካላዊ ንክኪ እና ፍትጊያን የሚጠይቁ ስፖርቶች የጉልበት ጅማት መበጠስ እክል ይስተዋልባቸዋል። እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ደግሞ በተደጋጋሚ የዚህ ጉዳት ዋነኛ ሰለባዎች ናቸው ይባላል።

ኤ ሲ ኤል (ACL) እንግዳ የኾነ ቃል ቢመስልም በጥቂቱም ቢኾን ሲነገር ሰምታችሁ ታወቁ ይኾናል። በሀገራችን፣ ሚዲያ ላይ በተለይ የስፖርት ጋዜጠኞቻችን በተጫዋቾች ጉዳት ወሬዎቻቸው ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ‘እገሌ የተባለ ተጫዋች እንዲህ ባለ ጨዋታ የጉልበት ጅማት መበጠስ ጉዳት አስናግዷል’ የሚሉ ዜናዎችን ያቀርባሉ።

ለመኾኑ የጉልበት ጅማት መበጠስ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ስለኾነ ስለጉዳዩ በጥልቀት ለመወያየት ከሰውነት ክፍሎች ጥናት (Anatomy) መነሳቱ ማለፊያ ሃሳብ ይኾንልናል።

አናቶሚ

ከላይ የምንመለከተው ምስል መደበኛ የጉልበት አናቶሚ ሲኾን የተዋቀረውም አጥንት፣ ካርቲሌጅ፣ ጅማት እንዲሁም ቴንደን ከሚባሉ ዐራት ነገሮች ነው። ሦስት ዓይነት አጥንቶች ደግሞ እርስ በርስ በመተሳሰር የጉልበት መገጣጠሚያ (knee joint) ይፈጥራሉ። ትስስር የሚፈጥሩትም በጅማቶች (ligaments) አማካኝነት ነው።

እነዚህ አጥንቶች የጭን አጥንት (Femur)፣ የመሃል አገዳ ወይም ቅልጥም (Tibia) እና የጉልበት ሎሚ(Patella) ናቸው። ፓቴላ ፍይዳው ላቅ ያለ ነው። በአቀማመጥ ረገድ ከመገጣጡሚያ ፊት በመኾን ከለላ (protection) ይሰጣል።

ሌላው ጉልበት አካባቢ ዐራት መሰረታዊ ጅማቶች ይገኛሉ ጥቅማቸውም ቀደም ብሎ ብለው የተገለፁ የአጥንት ዓይነቶችን እርስ በእርስ በማስተሳሰር ጉልበት ሳይሰንፍ መደበኛ ተግባሩን እንዲወጣ የሚያደርጉ ናቸው።

ክሩሺየት ጅማቶች (Cruciate ligaments)

ኤ ሲ ኤል የጉልበትን መሃከል ከሚያቋርጡ ሁለት የጅማት ዐይነቶች የመጀመሪያዎቹ ናቸው። እነዚህ ጅማቶች የሚገኙት በጉልበት መገጣጠሚያ ውስጥ ኾነው ከመዋቅር አኳያ ከፊት ከአንቲሪየር ክሩሺየት እንዲሁም ከኋላ ደግሞ ከፖስቲሪየር ክሩሺየት ጅማቶች ጋር የተጠላለፉ ናቸው። ጥልፍልፋቸውም X የሚመስል ምልክት ይሰጣል።

ክሩሺየት ጅማቶች ለምን ይጠቅማሉ?

ቁጥጥር፣ መከላከልና እርጋታ መፍጠር ከበርካታ ጥቅሞቻቸው መካከል ከፊሎቹ ናቸው።

እግሮቻችን የሚመሯቸው ዱካዎች ዘወትር ወደተመሩበት አቅጣጫ ይነጉዳሉ። ተጓዥ እግሮች ሁሌም በእንቅስቃሴ ውስጥ ይኾናሉ። እንቅስቃሴ ደግሞ ከጉልበት እጥፍ ዘርጋ ይጀምራል። እጥፍ ዘርጋ ማለት ወደ ፊት እና ወደ ኋላ የሚደረግ እንቅስቃሴ ማለት ሲኾን እንቅስቃሴዎቹ ቁጥጥር የሚደረግላቸው በእነዚህ ጅማቶች አማካኝነት ነው።

አንቲሪየር ክሩሺየት ጅማት አቀማመጥ በተመለከተ በአግድሞሽ መስመር (Diagonal line) የጉልበት መሃከለኛው ክፍል በማለፍ የአገዳ አጥንት(Tibia) የጭን አጥንት (Femur) ፊት ተንሸራቶ እንዳይመጣ ይከላከላል። በተጨማሪም ለጉልበት ሽክርክሪት(Knee rotation) መረጋጋት ይሰጣሉ።

አንቲሪየር ክሩሺየት ጅማቶች እንዴት ይጎዳሉ?

እነዚህ ጅማቶች እክል ሊገጥማቸው የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች ይኖራሉ። ጉዳዩን ቀለል ባሉ ቃላት ለማስረዳት እጅግ ተወዳጅ የኾነውን የእግር ኳስ ጨዋታን በምሳሌነት እንቃኝ።

፨ በሩጫ መሃከል አቅጣጫን በፍጥነት መለወጥ
፨ በሩጫ መሃከል ድንገት መቆም
፨ ሩጫን ድንገት ማቀዝቀዝ
፨ አግባብ ያልኾነ ዝላይ
፨ ቀጥተኛ አካላዊ ንክኪ
፨ ግጭት(collision)
፨ ከባድ ኳስ ማስጣሎች(Tacles)

የጅማት መበጠስ ጉዳት ምልክቶች

ምልክቶች ሲባል በዐይን የሚታዩ አለፍ ሲሉ ወደ ጥልቅ ምርመራ ከመገባቱ በፊት አንድ ተጎጂ ስፖርተኛ በአንደበቱ ስለ ክስተቱ የሚናገራቸውንና እንደ እብጠት ያለው ህመም፣ የመገጣጠሚያ መስመሮች ላይ እብጠት አሊያም መቆጣት ምልክት እንዲሁም በአርምጃ ወቅት ምቾት ማጣት ያሉ ሳይንሱ ለይቶ የዘረዘራቸውን ነገሮች ሊያጠቃልሉ ይችላሉ።

ተጨማሪ ሃሳቦች

የጉልበት ጅማት መበጠስ ወንድ ስፖርተኞችን ከሴቶች ነጥሎ የሚያጠቃ ሳይኾን በሁለቱም ዘንድ የሚከሰት ነው። ይኹንና እንደ በርካታ ጥናቶች ከኾነ ሴት ስፖርተኞች የኤ ሲ ኤል ከፍተኛ ሰለባዎች መኾናቸው ይነገራል። አካላዊ ልምምድ(physical conditioning)፣የጡንቻ ፈርጣማነት(muscular strength)፣ኒሮመስኩላር ቁጥጥር እንዱኹም በእርግዝና ወቅት የሰውነት ለውጥ የሚያመጣቸው ሆርሞኖች(oestrogens) የጅማቶች ባህሪያት ላይ የሚኖራቸው ውጤቶች አንድ ሁለት ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው።

በቀጣይ ጽሁፌ ጉዳቱን እንዴት አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል እና ከተከሰተ በኋላ በፍጥነት ለማገገም  በሚጠቅሙ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች ዙሪያ የምለው ነገር ይኖረኛል።


ስለ ጸሀፊው


ዐቢይ ሀብታሙ

መምህር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *