በልዑል ዓምደጽዮን

ኢትዮጵያ በታሪኳ እስካሁን ድረስ ብቸኛ ሆነውን የአፍሪካ ዋንጫ ያሸነፈችው ከዛሬ 58 ዓመታት በፊት (ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም) ነበር፡፡ ዋንጫውን ያገኘችውም ራሷ ባስተናገደችው በሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ግብጽን 4 ለ 2 በማሸነፍ ነው፡፡

ጥር 6 ቀን 1954 ዓ.ም ውድድሩ ሲጀመር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሉቺያኖ ቫሳሎ (2)፣ በግርማ ዘለቀና በመንግስቱ ወርቁ ግቦች ቱኒዝያን 4 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አለፈ፡፡ በሌላኛው ምድብ ደግሞ ጥር 10 ቀን 1954 ዓ.ም ግብጽ ኡጋንዳን 2 ለ 1 በማሸነፍ በፍጻሜው የኢትዮጵያ ተፋላሚ መሆኗን አረጋገጠች፡፡

ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስቴድዬም (የአሁኑ አዲ አበባ ስቴዲዬም) በተመልካቾች ተሞልቶ ጨዋታው ተጀመረ፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቋሚ ተሰላፊዎች ጊላ-ሚካኤል ተስፋማርያም (1)፣ አስመላሽ በርኸ (2)፣ ክፍሎም አርዓያ (3)፣ በርኸ ጎይቶም (4)፣ አዋድ መሐመድ (5)፣ ተስፋዬ ገብረመድኅን (6)፣ ግርማ ዘለቀ (7)፣ መንግሥቱ ወርቁ (8)፣ ሉቺያኖ ቫሳሎ (9/አምበል)፣ ኢታሎ ቫሳሎ (10) እና ጌታቸው ወልዴ (11) ሲሆኑ ተጠባባቂዎች ደግሞ ተኽለ ኪዳነ (በግርማ ዘለቀ ተቀይሮ ገብቷል)፣ ጌታቸው መኩሪያ፣ እስማኤል ጊሪሌ፣ ብርሃኔ አስፋው፣ ኃይሌ ተስፋ ጋብር እና ነፀረ ወልደሥላሴ ነበሩ።

ጨዋታው በተጀመረ በ35ኛው ደቂቃ ግብጽ በአብደልፋታህ በደዊ ግብ መምራት ጀመረች፡፡ ግርማ ዘለቀን ቀይሮ የገባው ተኽለ ኪዳነ በ74ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያን አቻ የምታደርግ ግብ አስቆጥሮ ደጋፊውን አስፈነጠዘው፡፡ ይሁን እንጂ ከሰከንዶች በኋላ ግብጽ በአብደልፋታህ በደዊ አማካኝነት ሌላ ግብ አስቆጥራ በድጋሚ መሪ መሆን ቻለችና የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ደስታው ወደ ውጥረት ተቀየረ፡፡ አምበሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ በ85ኛው ደቂቃ ወሳኝ ግብ አስቆጥሮ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስታዲዬምን ዝምታ ነፍስ ዘራበት፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ሰዓት አመራ፡፡

በ101ኛው ደቂቃ ላይ ኢታሎ ቫሳሎ ለኢትዮጵያ ሦስተኛ ግብ አስቆጠረ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት (በ117ኛው ደቂቃ) መንግሥቱ ወርቁ አራተኛውንና የመጨረሻውን ግብ ሲያስቆጥር በስቴድየም ውስጥ የነበረው ተመልካች በደስታ ዘለለ! ጮኸ! ጨዋታውም 4 ለ 2 በሆነ ውጤት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ኢትዮጵያም የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ሆነች!

የዋንጫ ባለቤት መሆን የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ‹‹የኢትዮጵያ ዘመናዊ የስፖርት አባት›› የሚባሉት ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ ረዳት አሰልጣኞቹ ደግሞ አቶ ፀሐየ ባሕረ እና አቶ አዳሙ ዓለሙ ነበሩ፡፡ ጥላሁን እሸቴ ደግሞ የቡድኑ ወጌሻ/ሐኪም ሆነው አገልግለዋል፡፡

የውድድሩ ከፍተኛ/ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ እና የግብፁ አብደልፋታህ በደዊ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡ የውድደሩ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው ደግሞ ዝነኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቹ መንግሥቱ ወርቁ ነበር፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *