በአቶ ፍጹም አጎናፍር | የእግር ኳስ ተንታኝ | ለልዩ ስፖርት|

አዲስ አበባ – ህዳር 12/2012ዓ.ም – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2021 የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ የውድድር መድረክ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከአይቮሪኮስት ፤ ማዳጋስካር እና ኒጀር ጋር በምድብ 11 ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን እያካሄደ ይገኛል።

በዚህ የማጣሪያ ጨዋታ ጉዞውም በመጀመሪያ ጨዋታው በማዳጋስካር 1ለ0 ሲሸነፍ፡ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ አይቮሪኮስትን ባሕርዳር ላይ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ብሔራዊ ቡድኑ በእነዚህ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ በጠባብ ውጤት 1ለ0 ከመሸነፉ እንዲሁም በሜዳው አይቮሪኮስትን 2ለ1 ከማሸነፉ በበለጠ፡ በሁለቱም ጨዋታዎች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የመረጠው ምክንያታዊና አዋጭ የሆነ የአጨዋወት መንገድ ትልቅ ትኩረትን የሚስብና ለብዙዎቻችን ምቾትን የሰጠ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ይሄ ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው ሁለት የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች፡ ከሜዳው ውጪ ማዳጋስካር ላይ እንዲሁም በሜዳው ከአይቮሪኮስት ጋር ሲጫወት ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክር ተመልክተነዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን ቀልብ ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተግባራዊ በማድረግ በኩል፡ ከአጨዋወት ውሳኔ ጀምሮ በተጫዋቾች አመራረጥ እና በቡድን ግምባታ በኩል ለሰሩት ውጤታማ ስራ የመጀመሪያውን እና ትልቁን ድርሻ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሊወስዱ ይገባል።

በመቀጠል ደግሞ አሰልጣኙ ይህንን ኳስን ተቆጣጥሮ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ለመስራት የመረጧቸው ተጨዋቾችና እንዲሁም በሜዳ ላይ ሀሳቡን ለመተግበር በቅድሚያ አሰላለፍ ውስጥ ከቦታ አጠቃቀም ጋር ያስቀደሟቸው ተጨዋቾች ለታየው ምርጥ ጅማሬ ሌሎቹ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያቶች ነበሩ።

ከአጨዋወት የሀሳብ መንገድ ምርጫ ፤ ለአጨዋወቱ የሚሆኑ ተጨዋቾችን ከመምረጥ ጉዞ እንዲሁም የአጨዋወቱን መንገድ በደንብ ተግባራዊ ለማድረግ ከተደረጉት ቅድመ የወዳጅነት ጨዋታዎች ደረጃ በደረጃ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፡ የመጣበት መንገድ አዋጭ እንደሆነ በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ የተመለከትን ይመስለኛል።

በተለይም በትልልቅ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ብዙ ስመ-ጥር እንዲሁም ፈጣንና ጉልበተኛ ተጨዋቾች ባለቤት የሆነችውን ሀገር አይቮሪኮስትን ባህር ዳር ላይ ያሸነፍንበት የጨዋታ እንቅስቃሴና መንገድ የበለጠውና የተሻለው ነበር። ነገር ግን የመጨረሻችን አይደለም።

በዚህ ጨዋታ ላይ በአካላዊ ጉዳዮች ማለትም በቁመታቸው አጫጭርና በክብደታቸው ደቃቃ የሆኑትን እንጀ ይሁን እንዳሻው፤ ሽመልስ በቀለ፤ ሱራፌል ዳኛቸው፤ ታፈሰ ሰለሞን እና አቡበከር ነስሩ አይነት ተጫዋቾችን ለጨዋታው ቅድሚያ ተመራጭ በማድረግና እንዲሁም ለእነርሱ አዋጭ የሆነውን የጨዋታ መንገድ በመምረጥ በጉልበተኛዋ ተጫዋቾች ሀገር ላይ፡ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በመብለጥ ጭምር ማሸነፍ ተችሏል።

ለዚህም ነው መላው የእግር ኳሱ ቤተሰብ ከድሉ እኩል በቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ደስታውን ሲገልጽ የነበረው።

ነገር ግን ይሄ የተመለከትነው መልካም እንቅስቃሴና ጅማሬ ያለምንም እንቅፋት ቀጣይ ጉዞው እስከምን ድረስ ይሆናል የሚለው ፡ መልስ የሚሻ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይመስለኛል?

ለዚህ አስፈላጊ እና የብዙዎች ጥያቄ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የራሳቸው መልስ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ብሆንም፤ ነገር ግን ይሄ ትልቅ ተስፋና ጭላንጭል የታየበትን እንቅስቃሴ ሳይቆራረጥ እያሳደጉ ለመቀጠል እንዲረዳቸው ከወዲሁ የመጀመሪያ መልዕክቴን ላካፍላቸው እወዳለሁ።

ሁላችንም እንደተመለከትነው የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የወቅቱ ብሔራዊ ቡድን የሚከተለው የአጨዋወት አስተሳሰብና መንገድ በአካላቸው ከገዘፉ ተጨዋች ይልቅ በክህሎታቸውና በአእምሮ አስተሳሰባቸው የላቁ ተጨዋቾችን የመጀመሪያ ተመራጭ በማድረግ ነው። በእንቅስቃሴ ረገድም በሁሉም የሜዳው ክፍል የሚገኙ ተጨዋቾችን ተሳታፊ በማድረግ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ መጫወትን ነው።

ይሄ የአጨዋወት መንገድ ደግሞ ከሌሎቹ የአጨዋወት መንገዶች በተሻለ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ሳይቋረጥ የሁሉንም ተጫዋቾች ከፍተኛ የአስተሳሰብንና የሜዳ አጠቃቀም ተሳትፎን በእያንዳንዷ ሰከንድ የሚፈልግ የአጨዋዎት ሀሳብ ነው። ለዚህ የአጨዋዎት መንገድ ውጤታማነት ደግሞ ከምንም በላይ በሚገባ የተዋሀደ ቡድን እጂግ አስፈላጊ ነው።

እንግዲህ በተዘዋዋሪ ይሄ ምን ማለት ነው፡ ይሄንን የአጨዋወት መንገድ በተሻለ ለማሳደግና የታየውን ነገር እያሻሻሉ በቀጣይነት ይዞ ለመጓዝ፡ ብሔራዊ ቡድኑ የሊግ ውድድሮቻችን ሲቋረጡና ክፍተቶች በተገኙ ቁጥር ቡድኑ እየተሰባሰበ የሜዳ ላይ ልምምዶቹን በመስራትና ሀሳቡን እያሳደገ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በመጫወት ያለውን ነገር ይዞ ለመቆየት ጥረት ቢያደርግ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ።

ይሄ ካልሆነ ግን ምናልባት እነዚህ በተለያየና በተዘበራረቀ የአጨዋወት አስተሳሰብ ውስጥ በየክለባቸው ቆይተው በድጋሚ ከብዙ ወራቶች በኋላ የሚገናኙ ተጨዋቾችን በድጋሚ ከቆዩበት የክለቦቻቸው የአጨዋወት መንገድ በፍጥነት ወደተመለከትነው አጨዋወት በመመለስ ውጤትና አስፈላጊውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መፈለግ ምናልባት አድካሚ ስራ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ።

ነገር ግን ይሄንን መልዕክቴን በማስተላለፍበት ወቅት አንድ አስምሬበት ማለፍ የምፈልገው ነጥብ ቢኖር፡ አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚከተለውን የአጨዋወት መንገድ በተሻለ መንገድ ይዞ እንዲቆይና እንዲጓዝ በተዘዋዋሪ መንገድ በተጨዋቾቻቸው አማካኝነት ሀሳቡ ላይ ትልቅ እገዛን የሚያደርጉለት ባለሙያዎችና ክለቦችም እንዳሉ በማሳወቅ ነው።

በቀጣይ ጽሁፎቼ ተጨማሪ መልዕክቶቼን እና የግል ምልከታዬን ይዤ እስክመለስ ለዛሬ የመጀመሪያውን መልዕክቴን በዚሁ እቋጫለሁ።

ግልባጭ፦
👉 ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
👉 ለኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ
👉 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቴክኒክ ክፍል ኃላፊዎች


ስለ ጸሀፊው


አቶ ፍጹም አጎናፍር (Fitsum Trequartista)

በFana FM 98.1 ስፖርት ዞን ፕሮግራም ላይ የጨዋታ ተንታኝና በታዳጊዎች ስልጠና ላይ የሚሰራ።

 

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *