አዲስ አበባ – ጥቅምት 12/2011ዓ.ም በሚፈጥረው ለየት ያለ የመዝናናት እና የቤተሰብነት ድባብ አማካኝነት፡ ከስፖርታዊ ኹነትነት ይልቅ፡ ለአመታዊ የጎዳና ላይ ትርኢትነት የቀረበ እንደሆነ የሚነገርለት፤ የአፍሪካ ግዙፉ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 45000 ተሳታፊዎች የሚሳተፉበትን የዘንድሮውን የ10ኪ.ሜ አለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድር ከሳምንታት በኋላ ያካሂዳል፡፡

በየዓመቱ ከ500 በላይ የሚሆኑ ታዋቂ እና የሙሉ ጊዜ አትሌቶች በሚሳተፉበት እጅግ ፈታኝ ውድድር ላይ እስከዛሬ የተመዘገቡትን አስደናቂ እውነታዎች ቀጥለን እናጋራችኋለን፡፡

0 – ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ አትሌቶች ያሸነፏቸው ውድድሮች ብዛት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሁለቱም ጾታ የተከናወኑ ውድድሮችን በሙሉ ያሸነፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቻ ናቸው፡፡

1 – ኃይሌ ገብረስላሴ እና ብርሐኔ አደሬ በ1994 የተካሄደውን የመጀመሪውን ውድድር ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው፡፡

2 – እስከዚህ ሰዓት ድረስ ውድድሩን ለተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ የቻሉት ሁለት አትሌቶች ብቻ ናቸው፡፡ አትሌት ገነት ጌታነህ በ1997 እና በ1998 ዓ.ም እንዲሁም አትሌት ውዴ አያሌው በ2000 እና 2001 ዓ.ም

2 – ሁለት ጥንዶች በተመሳሳይ አመት በሁለቱም ጾታዎች ውድድሩን አሸንፈው ያውቃሉ፡፡ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም እና ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ1995ዓ.ም እና አትሌት ስለሺ ስህን እና ባለቤቱ ጥሩነሽ ዲባባ በቀጣዩ አመት፡፡

3 – አትሌት ውዴ አያሌው በውድደሩ ታሪክ በ2000፣ 2001 እና 2007 ዓ.ም ለሶስት ጊዜያት ያክል በማሸነፍ ውጤታማዋ አትሌት ነች፡፡

4 – ገነት ጌታነህ 1997 እና 1998፣ ፎቴን ተስፋይ 2009 እና 2011 በሴቶች ፤ አዝመራወ በቀለ በ2003 እና 2007፣ ሀጎስ ገብረህይዎት በ2004 እና 2011ዓ.ም በወንዶች – እነዚህ አራት አትሌቶች ይህንን ውድድር ለሁለት ለሁለት ጊዜያት ማሸነፍ የቻሉ ናቸው፡፡

5 – አምና በተካሄደው የዋናዋና አትሌቶች ውድድር አትሌቶችን ያሳተፉ ሀገራት ቁጥር ብዛት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ቦትሰዋና እና ኡጋንዳ

14 – አስራ አራት የተለያዩ አትሌቶች በሴቶቹ ውድድር አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥሩነሽ ዲባባ፣ አበሩ ከበደ፣ ኮረኔ ጀሊላ፣ ሱሌ ኡቱራ እና ነጻነት ጉደታ ይጠቀሳሉ፡፡

16 – በወንዶቹ ውድድር ያሸነፉ አትሌቶች ብዛት ነው፡፡ ሞስነት ገረመው፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ጸጋየ ከበደ እና ታምራት ቶላ ከአሸናፊዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

18 – አትሌት ፎቴን ተስፋይ እና ሀጎስ ገብረህይዎት ባለፈው አመት የተከናወነውን እና 18ኛውን ውድድር ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው፡፡

19 – የዘንድሮው ውድድር ለ19ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው፡፡

28:18.61* – አትሌት ድሪባ መርጊያ በ1999ዓ.ም ውድድሩን ሲያሸንፍ የገባበት ይህ ሰዓት፡ የውድድሩ የወንዶች ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

32:16* – አትሌት ማሚቱ ዳስቃ በ2008ዓ.ም የገባችበት 32፡16 የውድደሩ የሴቶች ፈጣን ሰዓት ሆኖ ይገኛል፡፡

30:30* – የመጀመሪያውን ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የገባበት ሰዓት በውድደሩ ታሪክ በአሸናፊነት ከተመዘገቡት ሁሉ በወንዶች የዘገየው መሆኑን ታሪክ መዝግቦታል፡፡

35:07* – አትሌት ብርሀኔ አደሬ፣ ልክ እንደ ኃይሌ ሁሉ የመጀመሪያውን ውድደር በአሸናፊነት ስታጠናቀቅ የገባችበት ይህ ሰዓት በውድድሩ ታሪክ እጅግ የዘገየው የአሸናፊነት ሰዓት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ማስታወሻ፡ የውድደሩ ቦታ በተደጋገሚ ጊዜ በመቀያየሩ ምክንያት ውድደሩ ይፋዊ ክብረወሰን የለውም፡፡ በመሆኑም ከላይ የተቀመጡት ሰዓቶች እስካሁን ድረስ በተካሄዱት ውድደሮች ከተመዘገቡት ፈጣኖቹ እና የዘገዩት ናቸው፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *