ዶሃ – ኳታር – መስከረም 21/2012ዓ.ም – የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጸረ-አበረታች ቅመሞች ተቆጣጣሪ ድርጅት (ETH-NADO) ትላንት ምሽት ይፋ ባደረገው አቋሙ እንዳስታወቀው: ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና የስፖርት ባለሞያዎች ከዛሬ ጀምሮ ከአሜሪካዊው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር ጋር የሚኖራቸውን ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል ሲል አስጠንቅቋል።

ሳላዛር ለበርካታ አመታት ስሙ ከአበረታች ቅመሞች የረቀቀ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሲነሳ ቢቆይም እስከአሁን ድረስ ምንም አይነት ማረጋገጫ ስላልተገኘ ተጠያቂ ሊሆን አልቻለም ነበር።

ነገር ግን በትላንትናው እለት የአሜሪካ ጸረ ዶፒንግ ጽ/ቤት (USADA) ለሁለት አመታት ያክል በፍርድ ቤት ሲከራከር ቆይቶ የሳላዛርን ጥፋተኛነት በማረጋገጡ፣ አሰልጣኙ በፈፀመው የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ከቦታ ቦታ የማዘዋወር (Trafficking)፣ የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴውን በማወክ (Tampering) እና በተለያዩ የፀረ-ዶፒንግ የህግ ጥሠቶች ምክንያት ለሚቀጥሉት አራት አመታት በስፖርቱ ውስጥ እንዳይሳተፍ ቅጣት ተጥሎበታል።

እንደ ብሔራዊ የጸረ-ዶፒንግ ተቆጣጣሪ ድርጂቱ ገለጻ ከሆነ፡ የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) ይህን የቅጣት ውሳኔ ለአተገባበር ያግዝ ዘንድ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት(ETH-NADO) ጉዳዩን ማሳወቁን ገልጾ፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን መግለጫ አውጥቷል።

“በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ህግና በአገራችን የፀረ-ዶፒንግ መመሪያ አንቀፅ 2.10 መሠረት በህግ ጥሰት ቅጣት ከተላለፈባቸው ግለሰቦች ጋር ያልተገባ ግንኙት መፍጠር በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን እስከ 2(ሁለት) ዓመት የሚደርስ ቅጣትን ያስከትላል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የአገራችን አትሌቶች በተለያየ መልኩ ከአሠልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር ጋር እንደሚሠሩ የሚታወቅ ሲሆን በግለሰቡ ላይ የተጣለው ይህ የቅጣት ውሳኔ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ፅ/ቤታችን ጥሪውን ያስተላልፋል። ከዚህ ባሻገር የስፖርት ባለሞያዎችም ይሁን ሌሎች አካላት ከዚህ ግለሠብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርባቸዋል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ስፖርተኞችም ይሁን ሌሎች ባለሞያዎች የተቀመጠውን ህግ በመተላለፍ ቀደም ሲል የነበራቸውን ግንኙነት ለማስቀጠልና አዳዲስ ግንኙነቶችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ፅ/ቤታችን ጉዳዩን በማጣራት አስፈላጊውን የህግ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ያሳውቃል።”

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *