አዲስ አበባ – መስከረም 10/2012 ዓ.ም – ከፊታችን መስከረም 16 እስከ 25/2012 ዓ.ም በዶሃ ኳታር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን ዛሬ በሂልተን ሆቴል አሸኛኘት ተደርጎለታል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የባህል፡ ቱሪዝም እና ስፖርት ሚንስትሯን ሒሩት ካሳሁንን (ዶ/ር)፥ የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና ኮማንደር ጌጤ ዋሚን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተው ልዩልዩ የማነቃቂያ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ሂሩት ካሳሁን በሽኝት ስነ-ስርዓቱ ወቅት “ይህ ቡድን የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ቡድን ነው። ወርቅ ብታመጡ ደስ ይለናል፣ ብር ብታመጡም እንደዛው፣ ነሀስ ብታመጡም ቅር አይለንም፤ ስላስለመዳችሁን ነው እንጂ ባዷችሁን ብትመጡም አይከፋንም፡ ነገር ግን ድል አድርጋችሁ በደስታ እንደምንቀበላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።” የሚል መልዕክት ያስተላለፋ ሲሆን።

የፌዴረሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ “ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ ያላትን አንጸባራቂ ድል በመድገም በተስፋ የሚጠብቃችሁን ህዝብ እንደምታስደስቱት ተስፋ አደርጋለሁ።” በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።

አትሌቶቹ ለዝግጅት ሆቴል ውስጥ በቆዩባቸው ባለፉት ሁለት ወራት የነበራቸውን ዝግጅት አስመልክቶ አስተያቱን የሰጠው የ5000ሜ ተወዳዳሪው አትሌት ሰለሞን ባረጋ፡ ዝግጂቱ በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን በመግለጽ በሁሉም መንገድ ከጎናቸው ለነበሩ በሙሉ ምስጋናውን አቅርቧል።

በ20ኪሜ የርምጃ ውድድር ኢትዮጵያን ወክላ የምትወዳደረው አትሌት የኋልዬ በለጠው ደግሞ “የምንሄድበት አካባቢ ሞቃታማ መሆኑን በማወቅ ተቀራራቢ የአየር ጸባይ ባላቸው ቦታዎች ላይ ስንለማመድ ቆይተናል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን።” ብላለች።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እና በአለም ሻምፒዮናው 10ኛ ተሳትፏቸውን የሚያደርጉት ኮማንደር ሁሴን ሺቦ ዝግጂቱን በማስመልከት በሰጡት አስተያዬት “ለሁለት ወራት ያክል ውጤታማ የሚያደርገንን ልምምድ ስንሰራ ቆይተናል። አትሌቶቻችን በዶሃው ውድድር የሀገራችንን የከዚህ ቀደም የበላይነትእንደሚያስጠብቁ መሉ እምነት አለኝ።” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአስራ ስድስቱም የአለም ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ 27 የወርቅ፡ 25 የብር እና 25 የነሀስ ሜዳሊያወችን ያሸነፈች ሲሆን፣ በዶሃው ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጂት መደረጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በዚህ ሻምፒዮና ለመሳተፍ 29 አባላት ያሉት የኮንግረስ ተሳታፊ፣ የልዩ ልዩ የቴክኒክ እና የህክምና ቡድን አባላት እንዲሁም 36 አትሌቶችን በማካተት በሰባት የውድድር አይነቶች ለመካፈል ከነገ ጀምሮ በአራት ዙር የጉዞ ፕሮግራም ወደ ስፍራው ያቀናል።

 

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *