ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት ዘርፍ የአለም ቁንጮ ተብሎ ተመርጧል፡፡ በLets Do This የሚታገዘው እና በእውቁ የሩጫ መጽሔት Runner’s World የሚቀርበው The Challenges Award ባለፉት ሦስት ሳምንታት ገደማ በኦንላይን ሲያካሂደው በቆየው ውድድር አንዱ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተወዳደረበት ዘርፍ እስከ ትናንት ሌሊት ማለትም እሁድ መስከረም 4 ቀን ከተሰጠ አጠቃላይ ድምጽ 56 በመቶውን በማግኘት አሸንፏል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድምጽ መሠጠት ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ በመሪነት የዘለቀ ቢሆንም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት መጥበብ ጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያዊው የውድድር አዘጋጅ ተቋም በመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት በርካታ ድምጽ በማግኘቱ ልዩነቱን በማስፋት ሁለተኛ ደረጃን ከያዘው እና 24 በመቶ ድምጽ ከወሰደው San Diego Beach and Bay Half Marathon ርቆ በአስተማማኝ የበላይነት ውድድሩን ጨርሷል፡፡ Bay Bridge Half በ10 በመቶ ድምጽ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአለም ዙሪያ አንጋፋ ከሚባሉትና በርካታ አስርተ አመታት ካስቆጠሩት ታዋቂ የጎዳና ውድድሮች ጋር ተፎካክሮ ያመጣው ውጤት ከለጋ እድሜው ጋር ሲነጻጸር ስኬቱን አስደናቂ ያደርገዋል፡፡ ዘንድሮ 19 አመት የሚሞላው የኢትዮጵያው ውድድር ከአመት አመት እያደገ መጥቶ በመጪው ህዳር 45000 ገደማ ተሳታፊዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን ዓለም አቀፋዊ እንግዶችም ይኖሩታል፡፡

የሽልማት ስነ ሥርዓቱ ከአንድ ወር በኋላ ኦክቶበር 18 West Kensington በሚገኘው አስደናቂው Queens Club በደማቅ ዝግጅት የሚከናወን ሲሆን በስፖርቱ አለም ከፍ ያለ ስም ያላቸው እንግሊዛዊያን ዝነኞች በዝግጅቱ ይገኛሉ፡፡ በማራቶን የቀድሞዋ የአለም ሻምፒዮን ፓውላ ራድክሊፍ፤ የፓራ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎቹ ሳራ ስቶሪ እና ታኒ ግሬይ ቶምሰን እንዲሁም የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ ሪዮ ፈርዲናንድ ከእንግዶቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ይህ ሽልማት/እውቅና በሂደት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮቹን ተጠቅሞ በሀገሪቱ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት በሚገባ እንደሚያግዝ ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያዊው ተቋም ውጤቱ ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ድምጽ በሚወሰን ውድድር ተፎካክሮ ማሸነፉ በተለይ የሀገራችን የቴክኖሎጂ/ኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር ከግምት ሲገባ ትርጉሙ ይበልጥ ከፍ ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አሁንም በአንድነት በሚጋሯቸው ሀብቶቻቸውና እና ጉዳዮቻቸው ላይ እንጥፍጣፊ ሀብታቸውን ተጠቅመው በጋራ ከማሸነፍ እንደማይመለሱ አይተናል፡፡ በዚህ ውድድር የመጨረሻ ሁለት ቀናት የታላቁ ሩጫ ቤተሰቦች ከእጃቸው ሊወጣ የቀረበን ድል እንዴት ማርሽ ቀይረው መልሰው የራሳቸው ማድረግ እንደሚችሉ ታዝበናል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለዚህ ስኬት እውን መሆን ድምጽ ለሰጡ፤ በተለያየ መንገድ ሌሎች እንዲሰጡ የጋበዙ፤ ጥሪ ያቀረቡና ያመቻቹትን ሁሉ በእጅጉ ያመሰግናል፡፡

መረጃው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነው

author image

About Liyusport.com

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *