በ ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም 

አዲስ አበባ – ነሀሴ 28/2011 ዓ.ም – የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ የትራክ ቡድንን በአምስት ኦሊምፒኮች፤ ዘጠኝ የአለም ሻምፒዮናዎች እና አምስት የአፍሪካ ጨዋታዎች በዋና እና ምክትል የአሰልጣኝነት ሀላፊነቶች የመሩት እና ለሶስት አስርት አመታት በዘለቀው ስኬታማው የአሰልጣኝነት ቆይታቸው ከ360 በላይ ሜዳሊያ ያሸነፉ አትሌቶችን ያሰለጠኑት፡ አሰልጣኝ ሁሴን ሺቦ በተለይም ለትራክ ተወዳዳሪዎች ለተሻለ ውጤታማነት ይረዳቸው ዘንድ በማሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ምክራቸውን አካፍለዋል፡፡

ለስፖርቱ መሰጠት

ለማንኛውም አትሌት ስኬታማ እንዲሆን ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው በተፈጠሮ ከሚገኝ ተስጥኦ ቀጥሎ የሚመጣው ለስፖርቱ ያለ መሰጠት ወይም ታማኝነት ነው፡፡ አንድ አትሌት በስፖርቱ ውጤታማ ለመሆን ከፈለገ ስፖርቱ የሚጠይቃቸውን መስዋዕትነቶች በሙሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹ላብ ደምን ይተካል‹‹ እንዲሉ ያለ መስዋዕትነትም ድል እንዲሁ አይገኝምና ለዚህ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በትክክለኛ ስልጠና እና ከትክክለኛ አሰልጣኝ ጋር መስራት  

ደረጃውን የጠበቀ (በበቂ ባለሞያዎች የተደገፈ) እና ወጥ የሆነ ስልጠና ከብቁ አሰልጣኝ ጋር ማግኘት ለአትሌቶች ውጤታማነት የሚያስፈልግ ሌላኛው ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በተለይም የትራክ ሩጫ በባህሪው እንደ ረጅም እና አጭር ርቀት ውድድሮች ተወሰነው የተለዩ የብርታት ወይንም የፍጥነት ልምምዶች ብቻ የማይደረግበት እና ይልቁንም ሁለቱንም ብቃቶች በሚገባ ማዳበር የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህንን ማምጣት የሚያስችሉ ልምዶችን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ሁሉም አትሌት አንድ አይነት ብቃት የለውም፡ በመሆኑም ለእርሱ በትክክል የሚያስፈልገውን ስልጠና ለይቶ የሚያሰራው አሰልጣኝ፡ ትክክለኛ የልምምድ እቅድን የሚያዘጋጅ እና አትሌቱን በአካልም ሆነ በስነ ልቦና የሚያበቃ አሰልጠኝ እና ስልጠናዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ውጤታማነትን ማሰብ ግን በእጂጉ ይከብዳል፡፡ ስለሆነም አትሌቶች ትክክኛ አሰልጣኝ እና ስልጠናን ስለማግኘት መጨነቅ ይኖርባቸዋል፡፡

አጋዥ እንክብሎችን አለመጠቀም

በመጀመሪያ አንድ አትሌት ተሰጥኦ ካለው፤ ለስፖርቱ ታማኝ ከሆነ እንዲሁም በቂ እና ትክክለኛ ስልጠናን ካገኘ በፋብሪካ የሚመረቱ አጋዥ ምግቦችንም ሆነ እንክብሎችን ለምን ይጠቀማል? እነ ኃይሌ እና ደራርቱን የመሳሰሉ አትሌቶች ያንን ሁሉ ውድድር ሲያሽንፉና ክብረወሰኖችን ሲሰባብሩ የትኛውን አጋዥ ኪኒን ወስደዋል? ፈረንጆቹ እኮ የሚወስዱት እኛ በተፈጥሮ ያለን የሰውነት ሁኔታ፤ የአየር ንብረት እና መልክዓ ምድር እንዲሁም ተፈጥሯዊ ንጥረነገር ያላቸው ምግቦች ስለሌላቸው ነው፡፡ እኛስ ምን አጣን እና ነው?

ይሄ ነገር ከጥቅሙ ይልቅ በአትሌቶቻችን ላይ እየፈጠረ ያለውን አሉታዊ ስሜት በተለይም ሳይወሰዱት ሲቀሩ በራስ የመተማመን ስሜታቸው ሲቀንስ እየተመለከትን እንገኛለን፤ ስለዚህም አትሌቶቻችን ልምምድ ላይ በመበርታት፡ ራስን ከአላስፈላጊ ነገሮች በመጠበቅ እና ሌሎች ውጣታማ ለመሆን የሚያግዙ ለምሳሌ፡- አመጋገበን ባበለሙያ ምክር እንዲታገዝ በማድረግ እና ማሳጅን መጠቀም በመሳሰሉ መንገዶቸ ብቃታቸውን ለመጨመር የሚያግዙ ውጤታማ አካሄዶችን በመከተል ራሳቸውን ከአርቲፊሻል አጋዥ ምግቦች መጠበቅ ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡

ጠንካራ ስነ-ልቦና መገንባት 

የአትሌት የስነ ልቦና ሁኔታ ምንጊዜም ሰላማዊ እና ጠንካራ እንዲሁም ለጫና እጅ የማይሰጥ መሆን አለበት፡፡

አትሌቶች አታካች የሆነውን ልምድ፡ ፈታኝ የሆነውን ውድድር፡ መራር የሆነውን ሽንፈት እና አስከፊ የሆነውን ጉዳት በድል ተውጥተው ስኬታማ ለመሆን ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጁነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ለዚህም ከአሰልጣኞቻቸው በተጨማሪ በስነ ልቦና ባለሞያዎችም ቢታገዙ ይመከራል፡፡

ፆታዊ ግንኙነትን መመጠን

በተለይም በዝግጅት እና በውድድር ወቅት አትሌቶች ከፆታዊ ግንኙነት እንዲርቁ ይመከራል፡፡ እንደሚታወቀው በልምምድ ወቅት ሰውነት ይጠነክራል ፤ ጡንቻ ይዳብራል፡ በራስ መተማመን ከፍ ይላል ነገር ግን በዚህ መሀል ጾታዊ ግንኙነት የሚፈጸም ከሆነ የተሰራው ሁሉ ይፈርሳል፡ አላስፈላጊ እርግዝና ሊከሰት ይችላል ወይንም እርሱን ለመከላከል መድሀኒት ይወሰዳል ይሄም የራሱ የሆነ ስነልቦናዊ ጫና ይኖረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በግንኙነት ወቅት ብዙ ካሎሪ ስለሚያወጡ እርሱን ተከትሎ መዳከም ይመጣል፡ ከዛ ጉዳት ይፈጠራል፤ በዚህም ምክንያት ልምምድ ይቆማል… ስለዚህ በእረፍት ሰአት ብቻ ቢሆን ይመከራል፡፡

ለረጅም ሰአት አለማሽከርከር

በተለይም ከአድካሚ የጂምናዚየም እና የመስክ ሩጫ ልምምድ በኋላ አትሌቶች ፈጽሞ ባያሽከረክሩ ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም መኪና ማሽርከር የእግር እና የእጅ ብቻ ሳይሆን ጭንቅላትን ጨምሮ የመላ ሰውነት ትኩረት እና እንቅስቃሴን የሚጠይቅ ስራ በመሆኑ፡፡

ይህ ደግሞ የትራፊክ መጨናነቅ ተጨምሮበት አትሌቶች ከአድካሚ ልምምድ በኋላ ለረጅም ጊዜ እረፍት እንዳያደርጉ ይከለክላቸዋል፡፡ ስለሆነም አትሌቶች በተለይም ከልምምድ በኋላ ያለው እንቅስቃሴያቸው በሹፌር ቢሆን ይመከራል፡፡


ይሄ ጽሁፍ ቀደም ሲል www.ethiopianrun.org ላይ የታተመ ነው።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *