ሙያዊ ትንታኔ | በቅድስት ታደሰ | የአትሌቲክስ ህክምና ባለሞያ| ለ ልዩ ስፖርት ብቻ


አዲስ አበባ – ነሀሴ 23/2011ዓ.ም – ለሰው ልጅ በህይወት መቆየት እጅግ በጣም ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል አንዱ ምግብ ነው፡፡ በተለይም ለአትሌቶች ስኬታማነት ከሳይንሳዊ ልምምድ፣ ጠንካራ ስራ እና ችሎታ እንዲሁም ቁርጠኝነት በተጨማሪ ጤነኛ አመጋገብ አንዱ እና ዋነኛው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምግቦች በተፈጥሮ ይዘታቸው፣ በከፍተኛ ሀይልና ጥንካሬ ሰጪነታቸው፣ በሰውነት ገቢነታቸውና በሽታ ተከላካይነታቸው እንዲሁም አቅም በመጨመር የታወቁ መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ምቹ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስኬት አንዱ እና ዋነኛው ምክኒያት መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ካላቸው የተፈጥሮ ጠቃሚ ይዘት የተነሳ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስኬት የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ የምግብ አይነቶች መኖራቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ምግቦች በተለያዪ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ  ሲሆን በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድም ተዘውትረው አገልግሎት ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡

እንደ እንጀራ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ አጃ፣ ዳጉሳ፣ ማሽላ፣  ስንዴ፣ አደንጓሬ ወ.ዘ.ተ ለምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በተለያዪ የሀገራችን ክፍሎች በባህላዊ መንገድ ተዘጋጅተው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመስጠት ከሚታወቁት ምግቦች ውስጥ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

ሐይል ሰጪ ኢትዮጵያዊ ምግቦች (ካርቦሃይድሬትስ)

ሀይል ሰጪ ንጥረ-ነገርን አብዝተው በመያዛቸው ምክንያት በልምምድ እና ውድድር ወቅት የሚወጣውን ሀይል በቀላሉ ለመተካት የሚያግዙ እና ስፖርተኞቻችን አዘውትረው እንዲመገቧቸው ከሚመከሩ ኢትዮጵያውያን ምግቦች መካከል ጭኮ፣ ጨጨብሳ፣ ኩኩታ፣ ቆሎ፣ ቡናቀላ፣ የቡላገንፎ፣ የቆጮቂጣ፣ የቡላ ገንፎ፣ ኦሞልቾ፣ ቡርሳሜ፣ የገብስ በሶ፣ ስኳር ድንች፣ የበቆሎ ገንፎ፣ ቴምር ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል፡፡

ሰውነት ገንቢ ምግቦች (ፕሮቲንስ)

ስፖርተኞቻችን የተስተካከል ተክለ ሰውነት እንዲኖራቸው፡ ጡንቻወቻቸው እንዲጠብቁላቸው እና ራሳቸውን መልሰው እንዲገነቡላቸው እንዲሁም የጡንቻ አለመታዘዝ እንዳይከሰትባቸው የፕሮቲን ይዘታቸው ጥሩ የሆኑ ምግቦችን መመገብ ይኖርባቸውል፡፡

እነዚህን ንጥረ-ነገሮች ለማግኘት ደግሞ በተፈጥሯዊ መንገድ ብቻ የተቀለበ የበግ፣ የፍየል እና የጥጃ ስጋ፣ የሃይቅ አሣ፣ ባቄላ፣ ሽሮ ፍትፍት፣ አሹቅ፣ ጥህሎ፣ አቆብ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉትን ሀገርኛ ምግቦች ማዘውተር ይመከራል፡፡

ቅባት (ፋትስ)

የቅባት ይዘት ያላቸው ምግቦቻችን ደግም ለሰውነት ሙቀትን በመስጠት አትሌቶቹ የሚወስዷቸው የተለያዪ ቫይታሚኖች በሰውነታቸው ውስጥ እንዲዋሀድ፣ ሀይል እንዲከማች እና ጡንቻ ገንቢ ምግቦች /ፕሮቲኖች/ ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ በማገዝ በዋነኛነት የሚረዱ የምግብ አይነቶች ሲሆኑ ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያውያን ከሚዘጋጁት የኑግ እና ሰሊጥ ዘይቶች፣ የወይራ ዘይት፣ ተልባ፣ ኦቾሎኒ፣ ወ.ዘ.ተ ይህንን ማግኘት ይቻላል፡፡

ቫይታሚኖች

ቫይታሚን እና ማዕድናትን መመገብ ለአትሌቱ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት እና ከጉዳት ለማገገም በእጂጉ ይጠቅሙታል፡፡ በተጨማሪም በልምምድ እና ውድድር ወቅት ከሰውነት የሚወጣውን ጠቃሚ ፈሳሽ ለመተካት፡ የሰውነት ሙቀትን ለመቆጣጠር እንዲሁም የተላያዩ የሰውነት ክፍሎችመደበኛ ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እና ከሰውነት አላስፈላጊ ንጥረ-ነገሮችን ለማስወገድ የሚያግዙ ምግቦችንም አካቷል፡፡

እንጀራ፣ አምባሻ፣ ቤንጋ ሻሻ፣ ጣይቴ፣ አደንጓሬ፣ አትክልትቶች፣ ፍራፍሬ፣ ቴምር፣ ዘቢብ፣ በእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኙ ቫይታሚኖች ፣ አንጮቴ፣ መርቃ፣ ሸከካ፣ ምጪራ ወ.ዘ.ተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ለምሳሌ ያክል፡ የጤፍ እንጀራ እጅግ ጠቀሜታ ካላቸው የምግብ አይነቶች ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን በተለይም በውስጡ የያዘው የብረት ማዕድን ለሰውነት ህዋሶች በጣም ወሳኝ የሆነ ንጥረ ነገር በመያዙ በቀይ የደም ሴሎች አማካኝነት ሄሞግሎቢን የሚባል ኦክስጅን በሰውነት ውስጥ እንዲመላለስና ኦክስጅንን የሚያመላልሰው አይረን በአትሌቱ ሰውነት ላይ በቂ የሆነ ኦክስጅን እንዲኖር በማድረግ በልምምድ እና በውድድር ወቅት የድካም ስሜት እንዳይኖር ይረዳል፡፡

በሀገራችን የሚዘጋጁ ተጨማሪ ለስፖርተኞች የሚመከሩ ጠቃሚ ማዕዶች

ጩካሜ፣ እንሰት፣ ኩርኩባ፣ ፎሰሴ፣ ቤንጋ ሻሻ፣ በዴላ ኡዜ፣ ህልበት፣ በለስ፣ ጋባ፣ ደቀቆ፣ ሀዞ፣ ጣይታ፣ አምባሻ፣ ሀንዛ፣ ህብስት፣ ቂጣ፣ ተልባ ወጥ፤ ዶሮ ወጥ፣ ድፎ ዳቦ፣ ስልጆ፣ አምባዛ ወጥ፣ ጭምቦ፣ መርቃ፣ ቦያ፣ ኢንጀሮ፣ ባራስ ኢሻኩራ፣ ቦስቶ፣ ሳባያድ፣ ኡግኖ፣ ኩዋን፣ ዎሌዋል፣ አልጉራሳ አሞሌ፣ ሰላሜን ፎፊል ተኃሻ፣ ዱኳ ሰለምፀጊ፣ አኮብ፣ ኡፔሎ፤ ቦክዋ፣ በከል፣ እተሀን፣ ኡክሀት፣ መለዋ፣ ኩስኩስ፣ ቱፍቱፍ፣ ዳላን፣ ፈጢራ፣ …

ከላይ የዘረዘርኳቸው እና በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙት የምግብ አይነቶች ለስፖርተኞቻችን ጤናማነት፤ እድገት እና ውጤታማነት የራሳቸው የሆነ እጅግ ጠቃሚ ሚና ስላላቸው በተመጣጠነ ሁኔታ እንዲዘወተሩ የሚመከሩ ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

አትሌቶች የተፈጥሮ ይዘት ያላቸውን/Organic foods/ ምግቦች በማንኛውም ጊዜ ቢመገቡ ይመረጣል፡፡ ይህም በተፈጥሯዊ ምግቦች ብቻ ራስን እና አቅምን መገንባት እንዲሁም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በማሳየት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን እና ለውጤታማነት ሲባል የስፖርቱ ባህሪይ ፈጽሞ የማይፈቅደውን አበረታች መድሃኒቶች የመጠቀም ድርጊት ለመከላከል ይረዳል፡፡

የአትሌቲክስ የስነ-ምግብ ስርዓት በመዘርጋትም ለአትሌቶች ኢትዮጵያዊ ምግቦች ላይ ያተኮሩ የተመጣጠነ ምግብ ሕክምና /የስፖርት ኒውትሪሽን ቴራፒ /እንዲሰጥ በማድረግ፡ እንዲሁም ይህንን ዓይነቱን ምግብ ህክምና አትሌቶች በየቤታቸው እንዲያዘወትሩ የሚያስችላቸውን የማማከር ፕሮግራም በመክፈት ንፁህ ስፖርት እንዲሰፍን ማድርግ እንደሚያስፈለግ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡


ስለ ጸሀፊዋ


ቅድስት ታደሰ
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን
የአትሌቲክስ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *