አዲሱ “ኃይሌ ገብረስላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”

ሰቆጣ – ነሀሴ 17/2011 ዓ.ም – አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፡ ጻግብጅ ወረዳ ያስገነባው የአጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት በዛሬው ዕለት ተመረቀ።

ከሶስት ወራት በፊት በዳስ የሚማሩ ተማሪዎችን ሁኔታ በቴሌቪዥን ከተመለከተ በኋላ ትምህርት ቤቱን ወደ ዘመናዊነት ለመቀየር ስፍራው ድረስ በመምጣት በገባው ቃል መሰረት ሚያዚያ 27/2011 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ት/ቤቱ፡ በቀን ለ16 ሰዓታት እየተሰራ በ110 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።

በአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ስም የተሰየመው ትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ 800 ተማሪዎችን በፈረቃ የሚያስተናግድ ሲሆን፡ ለግንባታውም አራት ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖበታል።

በአካባቢው ባለው ምቹ ያልሆነ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ምክንያትም ከአጠቃላይ ወጪው 30% የሚሆነው ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ ማቴሪያሎችን ለማጓጓዝ የወጣ እንደሆነም ተገልጿል።

በቅርቡ በይፋ ስራ በሚጀምረው “ኃይሌ ፋውንዴሽን” አማካኝነት በመላ ኢትዮጵያ በትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የገለጸው አትሌቱ “ለትምህርት የሚደረግ ኢንቨስትመንት ከማንም በላይ ጥቅሙ ለራስ በመሆኑ ሁላችንም የበኩላችንን እንድንወጣ አደራ ለማለት እወዳለሁ። እኔ ለትምህርት ባለኝ አመላካከት የተነሳ ከ18 ዓመታት በፊት ነበር በባህር ዳር እና አሰላ ከተማ ትምህርት ቤቶችን ያስገነባሁት። በዛሬው ዕለት መርቀን የከፈትነውም ሆነ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ማሻ ወረዳ በግንባታ ላይ የሚገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትምህርት መስክ የምንሰራቸው የልማት ስራዎች ጅምር እንጂ የመጨረሻ አይደሉም።” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

ቀድሞ የነበረው የመማሪያ ክፍል

በአማራ ክልል ከሚገኙት 9013 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 84% የሚሆኑት ከደረጃ በታች መሆናቸውን ያስታወቁት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ እና በትምህርት ቤቱ ምረቃ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ይርጋ ከፋለ (ዶ/ር) ይህንን አስከፊ እውነታ ለመለወጥ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የአትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን አርዓያነት ያለው ተግባር በመከተል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የጻግብጅ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታወይ አብርሃ በበኩላቸው በአካባቢው ህጻናት እና ወላጆች ስም ለአትሌት ኃይሌ እና ለመላ ቤተሰቡ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ፤ በፕሮግራሙ ማገባደጃ ላይ በድንገት የተገኙት አቶ አዳነ ጣፋ የተባሉ ግለሰብ ደግሞ የኃይሌን የትምህርት ቤት ግንባታ ዜና ከሰሙ ጀምሮ በስፔን ሀገር እንዳሰባሰቧቸው የገለጹትን ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚያገለግሉ የ8500 አጋዥ መጽሀፍት ስጦታን ለትምህርት ቤቱ አበርክተዋል።

መረጃው የተገኘው ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነው

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *