የግል ምልከታ| በዳግም ተሾመ ፡ የስፖርት ባለሞያ| ለ ልዩ ስፖርት ብቻ | 


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዘርፈ ብዙው የሀገራችን የእግር ኳስ ችግራችን መፍትሔ ይሆናል በሚል ሰሞኑን ነገሬ ብሎ የያዘው ጉዳይ ቢኖር፡ በሁሉም የሊግ እርከን ላይ በሚፎካከሩ ክለቦች የሚገኙ ተጫዋቾችን የደሞዝ ጣሪያ መገደብ ነው፡፡

እኔም ከዚህ ቀጥሎ በማቀርበው ጽሁፍ ላይ የውሳኔውን ሂደት፡ አግባብነት እና ተቀባይነት እንዲሁም መታየት ነበረባቸው እና አለባቸው ብዬ በማስባቸው ጉዳዮች ላይ ሃሳቤን ለማካፈል እወዳለሁ፡፡

በመሰረቱ፡ “በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ እግር ኳስ ተጫዋቾች አሁን የሚያገኙት ደሞዝ የተጋነነ ነው ወይስ አይደለም?” ለሚለው ጥያቄ የእኔ መልስ በቀላሉ አዎ! ነው፡፡ ከምን አንጻር? ከተባልኩኝ፡ መልሴን እንደሚከተለው ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

  1. ተጫዋቾች ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ እና ከአገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ አንጻር
  2. አብዛኞቹ ክለቦች ከህዝብ በግብር መልክ በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚተዳደሩ ከመሆናቸው አንጻር
  3.  ክለቦቹ የሚወዳደሩበት ሊግ ገንዘብ የሚያስወጣ ብቻ (አክሳሪ) እንጂ በመወዳደራቸው በገንዘብ ትርፍ ሊያገኙ የሚችሉበት ካለመሆኑ እና ሌሎችንም ተጨማሪ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ነገር ግን ለደሞዛቸው እዚህ ደረጃ መድረስ ተጠያቂዎቹ የየክለቦቹ አስተዳዳሪዎች፤ የእግር ኳሱ አስተዳደራዊ ብልሹነት፤ የሙስና መንሰራፋት… እንጂ ተጫዋቾቹ አይደሉም፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በመንግስት እና በልማት ተቋማት የሚተዳደሩ ክለቦች ተጫዋቾችን በሰራተኛ ደሞዝ መሰረት ይቀጥሩ እንደነበር ማስታወስም ይገባል፡፡

ከተወሰኑ አመታት በኋላ ግን አንዳደንድ ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉን ሲቀላቀሉ በሌሎች አትራፊ ሊጎች እንደሚታየው ሁሉ ተጫዋቾችን ከሌላ ክለብ ለማዛወር ከፍ ያለ የፊርማ ክፍያ መክፈል ጀመሩ፡፡ በሂደትም አሁን የምንገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

ሰሞኑንም ለዚህ ጉዳይ እልባት ለማግኘት በሚመስል መልኩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች የተጫዋቾቻቸውን የደሞዝ ጣርያ የሚወስን ህግ በፌደሬሽኑ እና በስፖርት ኮሚሽን አወያይነት: ሁሉም ባይሆኑም የተወሰኑ ክለቦች ከተወያዩ በኋላ ከፍተኛው የደሞዝ መጠን በወር የመንግስት ግብርን ጨምሮ 50ሺህ ብር እንዲሆን ያሳለፉት ውሳኔ ለእግር ኳሱ ጠቃሚ ነው ወይ? ቢባል በእኔ በኩል መልሴ አዎንታዊ አይሆንም፡፡

ለመሆኑ የደሞዝ ጣርያን መወሰን ለምን ይጠቅማል? 

1. ክለቦች የተመጣጠነ ችሎታ (በክፍያ) ያላቸው ተጫዋቾች እንዲኖራቸው እና ፉክክሩ ለሁሉም ክለቦች ፍትሃዊ እንዲሆን፡፡ ይህ ግን ብዙውን ጊዜ በዝግ ሊግ ለሚሳተፉ ክለቦች ማለትም ሁሉም ክለቦች ሁልጊዜ የሚሳተፉበት ሊግ ሲሆን፡ በሀብት የሚበልጡ አንድ ወይም ሁለት ክለቦች ሊጉን ተቆጣጥረውት ሊቆዩ ስለሚችሉ ሊጉ አሰልቺ እንዲሆን ያደርጉታል ከሚል የሚመጣ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ስርዓት ወጪና ወራጅ ክለቦች ባሉበት የሊግ አይነት መጠቀም አግባብ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ገንዘብ አውጥተው ትልልቅ ተጫዋቾችን የሚገዙ ክለቦች ለላይኛው ሊግ አሸናፊነት ሲታገሉ አናሳ በጀት የሚመድቡት እና በጥራት ደረጃ አነስ ያሉ ተጫዋቾችን የሚይዙ ክለቦች ደግሞ ወደታችኛው ሊግ ላለመውረድ የሚያደርጓቸውን ፉክክሮች ስለሚያጠነክረው የደሞዝ ጣራ እዚህ አስፈላጊነቱ እምብዛም ነው፡፡

2. ክለቦች በአጠቃላይ ወጪያቸውን እንዲመጥኑ ይረዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለጊዜው ለማሸነፍ ብሎ በከፍተኛ ወጪ ብዙ ተጫዋቾችን የሚገዛ ክለብ ክለቡን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ክለቦች ብሎም ሊጉን ቀውስ ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡ ይህንን ደግሞ በደደቢት እግር ኳስ ክለብ የተከሰተውን ማስታወስ እንችላለን፡፡ ደደቢት ከፍተኛውን የፊርማ ክፍያ የከፈለ የመጀመሪያ ክለብ ሲሆን ባሳለፍነው አመት ደግሞ ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት የደሞዝ ጣሪያዬ 25ሺ ብር ብቻ ነው ብሎ ለማወጅ ተገዷል፡፡ ለክለቦች የፋይናንስ ቀውስ ግን የተጫዋቾችን ደሞዝ መናር ብቻ እንደዋና ምክንያት ማቅረብ ተገቢ አይሆንም፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የደሞዝ ጣራ መወሰኑ ከሊጉ አወቃቀር ጋር አብሮ የማይሄድ ነገር እንዳለው ማየት ይቻላል፡፡

ደሞዛቸውን ያናረውን አካል የአሰራር ብልሹነት እንደማስተካከል ደሞዝተኞቹ ላይ ይህን እርምጃ መውሰድም ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት እንዳልታሰበ እንዲያውም የሰኔውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹‹መንግስት የሚመድበውን በጀት ይተዋል›› የምትለውን ሀረግ ፍራቻና ይኸው እርምጃ ወስደናል ብሎ ሪፖርት ለማቅረብ የመጣ ይመስላል፡፡

ይሁን ይወሰን እንኳን ብለን ብናስብ ይህ ጣራ እንዲሰራ መመልከት ያለበን ሌሎች ተያያዥ ቢያንስ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡

1. የክለቦች የፋይናንስ አጠቃቀም ግልጽነት፡ ክለቦች ከፌደሬሽኑ ጋር የሚዋዋሉት ውል እንዳለ ሆኖ በጎን ከተጫዋቹ ወይም ከወኪሉ ጋር የሚያካሂዱት ስምምነት ላለመኖሩ መቆጣጠሪያ ዘዴ ፌደሬሽኑ ይዘረጋል ወይ? በአገራችን ገቢ የማሳወቅ ግዴታ እንደሌለ ይታወቃል እና ተጫዋቾች በአካውንታቸው ምንም ያህል ብር ቢገባ በፍርድ ቤት ካልተጠየቁ በስተቀር ምን ያህል ገንዘብ ከክለባቸው እንደተከፈላቸው ለማወቅ አይቻልም፡፡

ስለዚህ ክለቦች ከመንግስት ወይም በጀት ከሚመድብላቸው አካል የሚሰጣቸውን ገንዘብ በሙሉ ለፌደሬሽኑ የሚያሳውቁበት መንገድ ከሌለ የሚያወጡት ገንዘብ ምን ያህሉ ለተጫዋች ደሞዝ ምን ያህሉ ለሌሎች ከውድድር ጋር ተያያዥ ወይም ለክለቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እንደሚውሉ መወቅ ስለማይቻል መጀመሪያ የፋይናንስ አጠቃቀማቸው ግልጽነት ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡

2. በውል ላይ የሚሰፍሩም የማይሰፍሩም የተጫዋቾች ጥቅማ ጥቅሞች፡ ለተጫዋቾች ቃል የሚገቡ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በገንዘብ ሲተመኑ ፌደሬሽኑ ካስቀመጠው ጣርያ በላይ ላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? ይህም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲያዝ መቆጣጠር የሚያስችለው መንገድ ፌደሬሽኑ ይዘረጋል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

በመሆኑም መንግስት፣ ስፖርት ኮሚሽን ወይም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የተጫዋቾች የደሞዝ ጣርያ ከሚያስቀምጡ፡ ወደ ዘመናዊ የእግር ኳስ አስተዳደር የምንሻገርበትን መንገድ/አቅጣጫ ቢፈልጉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡

እግር ኳሱን ትርፋማ ወደ ሆነ የመዝናኛ ኢንዱስትሪነት እንዲቀየር መስራት

1. በተጫዋቾች ላይ የተናጥል የደሞዝ ጣሪያ ከማስቀመጥ ይልቅ በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ ክለቦች የበጀት ጣርያ እንዲቀመጥላቸው በማድረግ በሂደትም ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ በማሳየት እንዲሁም እንዲችሉ በመግፋት፡፡ በጥቅሉ ክለቦቹ ገቢ የሚያስገኙ ነገሮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማብቃት፡፡

ይህንንም ስፖንሰር ማፈላለግ፤ ደጋፊዎችን በመመዝገብ አመታዊ/ወርሃዊ የአባልነት ክፍያ እንዲከፍሉ ማድረግ፤ ለደጋፊዎች የሚሸጡ ቁሳቁሶችን ማዘጋጀት፤ ስታዲየሞችን በኪራይም ሆነ በረጅም ጊዜ እቅድ እንዲሰሩ ማድረግ… ከዚህ ጎን ለጎንም ገቢና ወጪያቸውን የሚያመጣጥኑበትን አስገዳጅ እና ሊተገበር የሚችል ስርአት መዘርጋት እና በትኩረት እንዲያከናውኑ ማድረግ ይገባል፡፡

2. አሁን ፌደሬሽኑ እያካሄዳቸው ያሉት ሊጎች በሙሉ ውድድሮችን ከማድረግ ባሻገር ለክለቦችም ሆነ ለአገሪቱ ገቢ በማምጣት ረገድ ምንም እየፈየዱ ስላልሆነ ሊጎችን ገቢ የሚያስገኙ የቢዝነስ ተቋማት የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት።

3. በሂደት ለክለቦችም ሆነ ለፌደሬሽኖች ከመንግስት የሚመደበው በጀት ለእግር ኳስ ልማት እንዲውል ማስገደድ፡፡ ብሎም በጀት ከመለቀቁ በፊት የፕሮጀክት ንድፈ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ማስገደድ፡፡ ክለቦች ቢያንስ ከ15 አመት በታች ጀምሮ ቡድኖች እንዲኖራቸው ወይም ከፕሮጀክቶች ጋር በጋራ እንዲሰሩ ማስገደድ እና ሌሎች ተተኪ ተጫዋቾችን የሚያፈሩባቸው መንገዶች ላይ እንዲሳተፉ ማስገደድ፡፡

4. ክለቦች በሚመሩበት ሊግ መመሪያ ውስጥ በከፍተኛ ደሞዝ የሚቀጥሯቸውን ተጫዋቾች ብዛት መገደብ፡፡ ይህ በሁለት መልኩ ይጠቅማል፡፡ አንድም ተጫዋቾች በጥሩ አቋም እንዲጫወቱ እና ክፍያቸው ላይ ድርድር እንዲያደርጉ፡፡ ሁለትም ሁሉም ክለቦች ቢያንስ አንድ ወይም ከዚያ በላይ በብቃቱ በንጽጽር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ተጫዋች እንዲኖራቸው ይረዳል፡፡

የሚያስፈርማቸው ተጫዋቾችም የሚያገኙትን ጥቅም በዝርዝር በማስቀመጥ ለተፈጻሚነቱ መስራት፤ በቀን ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ልምምድ የሚሰሩና በውድድሮች ላይ ክለቡ ሲሳተፍ መጫወት ብቻ ሳይሆን በስፖርቱ አፍቃሪ ዘንድ የሚከበሩ እና በስብእናቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን በማፍራት በነዚህ ተጫዋቾች ስም የሚሰሩ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማስተዋወቅም ሆነ ሌሎች ገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ላይ በማሳተፍ የገቢ ምንጭነታቸውን መጨመር፡፡ ለቡድኑ የሚፈርሙበትንም ጊዜ ረዘም በማድረግ ወደፊት ለሌላ ክለብ በሚሸጡበት ወቅት ክለቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ወዘተ…

5. በየሊጉ የሚሳተፉ ክለቦችን ቁጥር መቀነስም በደርሶ መልስ ለሚደረጉ ውድድሮች ክለቦች በትራንስፖርት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የሚያወጡትን ወጪ እንዲቀንሱ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ይህ ተጫዋቾችም በመንገድ ብዛት ከሚደርስባቸው አላግባብ ድካም፡ የአቋም መዋዠቅ ብሎም ጉዳት ይታደጋቸዋል፡፡

6. ውድድሮች በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን አንዲያገኙ ማድረግ ለሊጉ አስተዳዳሪ እንዲሁም ለክለቦቹ ተጨማሪ ገቢን ከማምጣቱም በተጨማሪ ተጫዋቾች በተሻለ ፉክክር እንዲያደርጉ ያስችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በባዶ ስቴዲየም እና በአገሪቱ ህዝብ በሙሉ እየታዩ መጫወት ተጫዋቾች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖን ማነጻጸር ነው፡፡


ስለ ጸሀፊው


አቶ ዳግም ተሾመ 

ስራ: በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ – ኤቨንት እና ኦፕሬሽንስ ማኔጀር

የትምህርት ዝግጅት: ማስተርስ ዲግሪ በስፖርት አስተዳደር እና ቴክኖሎጂ – ከ ኤአይኤስቲኤስ ዩኒቨርሲቲ – ሎዛን ስዊትዘርላንድ

 የመጀመሪያ ዲግሪ – ኢንፎርሜሽን ሳይንስ – ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *