የግል ምልከታ | ስማቸው እንዲገለጽ ባልወደዱ የአትሌቲክስ ስፖርት ባለሞያ | ለ ልዩ ስፖርት ብቻ |


ከመስከረም አጋማሽ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሚከናወነው እና መላው የስፖርቱ አፍቃሪዎች በከፍተኛ ጉጉት በሚጠብቁት 17ኛው የኳታሩ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፡ ሀገራት ውጤታማ ውድድርን ለማካሄድ ዝግጅታቸውን በጊዜ ከጀመሩት ሰነባብተዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም በሌሎች ዘንድ በውድድሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ቅድመ ግምት ከሚሰጣቸው ተርታ የምትሰለፍ እንደመሆኑ መጠን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ይህ ግምት እውን እንዲሆን በየቦታው ብቁ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን አትሌቶች እና ባለሞያወች በመምረጥ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል፡፡

የዛሬው ጽሁፌ ትኩረት የሚያደርገውም በተለይ ኢትዮጵያውያን ለውጤታማነት በብዙ ተስፋ በሚያደርጉባቸው የወንዶች 5 እና 10ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ ይሆናል፡፡

እንደ እድል ሆኖ ሀገራችን በእነዚህ ውድድሮች ላይ እንደተቀሩት ሀገራት የትኞቹ አትሌቶቼ ሚኒማውን ያሟሉልኝ ይሆን የሚል ጭንቀት አልገጠማትም  አይገጥማትምም፤ ነገር የትኞቹን አትሌቶች በየትኞቹ ውድድሮች ላሳትፍ የሚለው በከፍተኛ ትኩረት ልትሰራበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አበክሬ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

የፌዴሬሽኑ የየርቀቶቹ ተመራጮች

10,000 ሜ                                                               5000ሜ.
1. ሀጎስ ገብረህይወት 26:48.95                             1.  ጥላሁን ሀይሌ          12:51.98
2. ሰለሞን ባረጋ 26:49.46                             2. ሰለሞን ባረጋ    12:53.04
3. ዮሚፍ ቀጄልቻ 26:49.99                             3.  ሀጎስ ገብረህይወት 12:54.15
4. *አንዳምላክ በልሁ 26:53.15                             4. *አባዲ ሀዲስ  12:56.35
5. *ጀማል ይመር 26:54.39                             5. ** ሙክታር ኢድሪስ
6. *አባዲ ሀዲስ 26:56.46

በአሁን ወቅት የአለም የ5000ሜ ወንዶች ምርጥ ሰዓትን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ በቅደም ተከተል የያዙት ሰለሞን፣ ዮሚፍ፣ ሀጎስ እና ጥላሁን ናቸው፡፡ አራቱም ከቡድን ስራ ይልቅ በግል ከፍተኛ ውጤት የማምጣት ፍላጎት እና አቅሙም ያላቸው ናቸው፡፡

በዚህ ርቀት የኔ ምርጫ ከፌደሬሽኑ የሚለየው ሀጎስን በዮሚፍ መተካቴ ነው፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ ሀጎስ ከሁሉም በንፅፅር እድሜው ትልቅ በመሆኑ እንዲሁም ውድድሩ የሚካሄድበት ቦታ ሞቃታማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተደራራቢ ውድድሮችን ማድረጉ ውጤታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብየ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም ሀጎስን 10ሺ ሜትር ላይ እንዲያተኩር እመክራለሁ፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ዮሚፍ የናይክ ፕሮጀክት መሰልጠን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልምምዱን እስኪላመደው ድረስ ያሳይ የነበረው ብቃት አስግቶኝ ቢከርምም በዘንድሮው የፈረንጆቹ አመት ከ1ማይል ወይም 1600ሜትር ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከተካፈለበት 10ሺ ሜትር ውድድሮች ድረስ ያሳየው አቋም በ5ሺ ሜትር ውድድሩ ላይ ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

ነገር ግን እሱን በእድሜው ሙሉ አንድ ጊዜ ብቻ በተወዳደረበት 10ሺ ሜትር ማሰለፍ ከፍተኛ ጥፋት ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ምንም እንኳን በመጀመሪያው የሄንግሎ ውድድሩ በፈጣን ሰዓት በሶስተኛነት ቢያጠናቅቅም፡ ይህ ውድድር ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተለየ የተዘጋጀ ከመሆኑ አንፃር የሌሎች ሀገራት በርቀቱ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ባሉበት ውድድር ስላልተፈተነ ውጤታማ ይሆናል ለማለት ያስቸግረኛል፡፡

በተጨማሪም በአለም ሻምፒዮናው በ10ሺ ሜትር ለ3 ተከታታይ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት የሆነው ሞ ፋራህ በርቀቱ ክብሩን ለማስጠበቅ በተጋባዥነት እንደሚሳተፍ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ባለፉት አመታት አብሮት በመወዳደር ምን ያህል ጠንካራ አትሌት መሆኑን ያረጋገጠው፤ በአሁን ሰዓትም በእርግጠኝነት ደካማ ጎኑን የሚረዳው አንዳምላክ በልሁን በዮሚፍ ተክቼ ማስገባትን መርጫለሁ፡ከፌደሬሽኑ ምርጫ ጋር የምስማማበት ነገር ቢኖር የሰለሞን ባረጋን በሁለቱም ርቀት መሳተፍ ነው፡፡

ምንም እንኳን ከቀነኒሳ ውጪ በአንድ የአለም ሻምፒዮና በሁለቱ የትራክ ውድድሮች ያሸነፈ አንድም አትሌት ባይኖረንም እና ተወዳዳሪዎች የችሎታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ካልደረሱ ሁለት ውድድሮችን እንዲካፈሉ ባይመከርም ሰለሞን በዘንድሮ አቋሙ (በአለም የደረጃ ሰንጠረዥ በ5000 ሜ. 1ኛ በ10,000ሜ. 2ኛ) ላይ መገኘቱ፤ የመጨረሻ ዙር ላይ ካለው የአጨራረስ ብቃት፤ በተደጋጋሚ ውድድሮች ላይ እያሳየ በመጣው ብስለት እንዲሁም ከቡድን አጋሩ አንዳምላክ ሊያገኝ የሚችለውን ድጋፍ ታሳቢ በማድረግ ሁለቱንም ውድድር ቢሳተፍ አጠቃላይ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ይችላል እላለሁ፡፡

በ5ሺው ውድድር ከ2013 የአለም ሻምፒዮና ጀምሮ በርቀቱ ሲሳተፍ የቆየው እና በ2017 ለንደን አለም ሻምፒዮና ላይ የመጨረሻ አቅሙን የተጠቀመ የሚመስለው ሙክታር ኢድሪስ የአሸናፊነት ክብሩን ለማስጠበቅ በውድድሩ ተጋባዥ አትሌት ነው፡፡

ነገር ግን ከለንደኑ ሻምፒዮና ጣፋጭ ድል በኋላ የተወዳደረባቸውን የአገር ውስጥም ሆነ ሌሎች ውድድሮች በርቀቱ ማሸነፍ ቀርቶ አንዳንዶቹን በማቋረጥ እድሜው ረዘም ወዳሉ የጎዳና ውድድሮች እየገፋው እንደሆነ ያስታውቃል፡፡

ስለሆነም በዚህ ውድድር ላይ አብረውት ለሚሳተፉት 3 ኢትዮጵያውያን የማሸነፍ የተሻለ እድል ለመፍጠር ቢወዳደር ከለንደኑ ድል ባልተናነሰ ለአገሩ ውለታ እንደዋለ ይቆጠራል፡፡

Yomif Photo by Christopher Lee/Getty Images)

ለዚህም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመመካከር፤ ከተቻለም ለውድድሩ በቀረው ከ2 ወር ያነሰ ጊዜ አብሮ በመስራት በምን ያህል ፍጥነት አብረውት ለመሄድ እንደሚችሉ በማወቅ (ከአቅማቸው በላይም ፈጥኖ ለራሱም ለአጋሮቹም አደጋ እንዳይፈጥር)፤ የውድድሩን የመጀመሪያ ዙሮች በተመካከሩት መሰረት በማፍጠን የቡድን ጓደኞቹ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሮጡ ማድረግ ይችላል፡፡ ይህም በመጨረሻዎቹ ዙሮች የማሸነፊያውን እሽቅድድም ከሶስቱ ኢትዮጵያውያን እንዳይወጣ ለማድረግ ያስችላል፡፡

በ5000ሜ ለዘንድሮው የአለም ሻምፒዮና የተመረጡት ተወዳዳሪዎቻችን ከላይ እንደጠቀስኩት በአለም ከፍተኛውን ደረጃ የያዙት ስለሆኑ አንዳቸው ወርቅ ሜዳልያ እንደሚያመጡ የሚጠበቅ ነው፡፡

በዚህ አመት ያደረጓቸውን ውድድሮች በተከታታይ በበላይነት ማሸነፋቸው የበለጠ የስነልቦና ጥንካሬም ይሰጣቸዋል፡፡ የሙክታር መኖር እና በቡድን መስራታቸው ደግሞ ሜዳልያችን በወርቅ ብቻ እንዳይገደብ ይረዳል፡፡

በ10000ሜ በኩልም ሀጎስና አንዳምላክ ለዚህ ርቀት ትኩረት ሰጥተው አብረው ከሰሩ፤ ሰለሞን ከ5ሺ ሜትር የመጨረሻ ውድድር በኋላ ለማገገም እና ወደ 10ሺ ርቀት ልምምድ ለመመለስ ከዚህ በፊት ከነበሩት አመታት የተሻለ የውድድር መርሃ ግብር በመሆኑ ብዙም የሚቸገር አይመስለኝም፡፡

ዶሃን በተለየ ከበድ የሚያደርገው ሞቃታማው የአየር ንብረት ነው፡፡ ምንም እንኳን የመወዳደሪያ ስቴዲየሙ የሙቀት ማስተካከያ ቢገጠምለትም ከተማዋ ሞቃታማ በመሆኗ በአጠቃላይ ተወዳዳሪዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡

አንዳምላክ በራሱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባይገኝም ለቡድን ስራ የሚተጋ እና በቡድን ስራ የሚያምን መሆኑን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ባሳየው እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዳምላክ ከሰለሞን ባረጋ ጋር የተለየ ቅርበት ያለው መሆኑን ዘንድሮ በተካሄደው የኢትዮጵያ  ሻምፒዮና ላይ አሳይቶናል፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት በ10ሺው ውድድር ላይ ሞ ፋራህ የበፊት ውጤቱን ለማስጠበቅ ተወዳዳሪ ስለሆነ በርቀቱ ከሱ ጋር በተደጋጋሚ የተወዳደሩት ሀጎስና አንዳምላክ የተሻለ እቅሙን ያውቁታል፡ ሞ ፋራህ በዚህ ውድድር ላይ እድሜው ገፍቶ እንዲሁም አመቱን ሙሉ ትኩረቱን ጎዳና ላይ አድርጎ በመቆየቱ በ10ሺ ሜትር ውድድሩ ላይ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ዙሩን በመቆጣጠር እስከመጨረሻው ድረስ እንዳይሄድ ቀደም ብሎ ዙሩን በማክረር 5 ወይም 6 ዙር ሲቀረው ከተፎካካሪነት በማስወጣት ከሰለሞን እና ሀጎስ የተሻለ አጨራረስ ብቃት ያለው ውድድሩን እንዲያሸንፍ መስራት ይቻላል፡፡

በመሆኑም በእኔ እምነት ፌዴሬሽኑ በ5000ሜ.፡ ዮሚፍ ቀጄልቻ ፣ ጥላሁን ሀይሌ እና ሰለሞን ባረጋ፤ ሙክታር ኢድሪስ – ቀጥታ ገቢ እንዲሁም በ10,000ሜ፡ ሀጎስ ገ/ህይወት፣ አንዳምላክ በልሁ እና ሰለሞን ባረጋን ቢያሰልፍ በውድድሩ የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንዳለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *