ደብረብርሃን – ነሀሴ 04/2011 ዓ.ም – የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 44ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን  በደብረብርሃን ጌትቫ ሆቴል አካሄደ፡፡  በጉባኤው አዘገጃጀት እና አጠራር ሂደት ላይ ቅሬታ ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያሉ የጉባኤው አባላት ቅሬታቸውን በጉልህ አንጸባርቀዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እና የኦሎምፒክ ኮሚቴው ስራ አስፈጻሚ አባል ደራርቱ ቱሉ፡ በእለቱ ለጉባኤው አባላት የቀረቡት የ2011 ዓ.ም  የስራ አፈጻጸም፣ የ2012 ዓ.ም የባጀት እና የስራ እቅድ ሪፖርቶች በሙሉ፡ በስራ አስፈጻሚው አባላት ምንም አይነት ግምገማ ያልተካሄደባቸው እና ለእርሷም እንደስራ አስፈጻሚ አባልነቷ የጉባኤው ጥሪ ያልደረሳት መሆኑን ገልጻ በእነዚህ ምክንያቶች ራሷን ከስራ አስፈጻሚነቷ ማግለሏን በጉባኤው ፊት አስታውቃለች፡፡

ይሁንና ጉባኤው በውሳኔዋ ያልተስማማ ሲሆን፡ የጉባኤው ሰብሳቢ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ካለ ደራርቱ ኦሎምፒክ አይታሰብም የቤት ስራውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይወስዳል እናግባባታለን በሚል ጉባኤውን አረጋግተዋል፡፡

ደራርቱ ከሰዓታት በሗላ ከልዩ ስፖርት ጋር ባደረገችው ቆይታ

“ከጉባኤው አባላት እና ከልዩልዩ ወገኖች ውሳኔየን እንድቀለብሰው በቀረበልኝ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት ኦሊምፒክ ኮሚቴው ያሉበትን የአሰራር ችግሮች የሚቀርፍ ከሆነ ብቻ፡ ስፖርቱን ለማገልገል ስል በድጋሚ በሀላፊነት ለመቆየት ወስኛለሁ” በማለት ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በበኩላቸው በመመሪያው መሠረት የጉባኤው አጀንዳዎች፡  ከአንድ ወር በፊት ባለመላካቸው ሪፖርቶቹንም ሆነ እቅዶቹን በደምብ እንዳልተመለከቷቸው፡ በተጨማሪም ጽ/ቤታቸው ለጉባኤው ይፋዊ ጥሪ እንዳልደረሰው በመግለጽ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በበኩሉ በስራዎች መደራረብ ምክንያት ጥሪውን በመደበኛ አካሄዱ ለአባላቱ ባለማድረሱ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በጉባኤው ወቅት፡ ከላይ ቅሬታ የቀረበባቸውን የ2011 ዓ.ም የስራ ክንውን እንዲሁም የኦዲት ሪፖርትን አድምጦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

2011 የኦሎምፒክ ሳምንት በመላው ሃገሪቱ መከበሩ፡ የመላው ሴቶች ጨዋታዎችን በጅግጅጋ ማከናወኑን፡ በደብረ ብርሃን ጫጫ ለሚሰራው የማዕድን ውሃ ማምረቻ የቁፋሮና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸው፡ ከአለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ የስፖርት አመራሮች ጋር ውይይቶችን ማድረጉ ሌሎች እንደ ጠንካራ ስራ በሪፖርቱ የተጠቀሱ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

ጉባኤው በ2012 ዓ.ም የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም ኮሚቴው ያቀደውን እቅድ የማዳበርያ ሃሳቦች በመጨመር ያፀደቀ ሲሆን የጫጫውን የውሃ ፋብሪካ ማጠናቀቅ ፣ የእንቧይ መስክ የሆቴል የመዝናኛና የዌር ሃውስ ግንባታን ማስጀመር ፣ የኦሎምፒክ ሳምንትን በደመቀ ሁኔታ ማክበር በዋናነት የተነሱ ሁነቶች ናቸው፡፡

በተጨማሪም በ2012 ዓ.ም  በክልልና በከተማ አስተዳደሮች የኦሎምፒክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን ለመክፈት አቅዷል፡፡  ይህ ሃሳብ ጉባኤውን ይበልጥ ያነጋገረ ቢሆንም በመጨረሻ ቢከፈት ጠቃሚ ነው በሚለው ሃሳብ መስማማት ላይ ተደርሷል፡፡

በመጨረሻም ጉባኤው የአቋም መግለጫውን በፅሁፍ በማቅረብ፡ ከአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ከተለያዩ ገቢ የማግኛ ዘዴዎች እንደሚገኝ የታሰበ የ170.5 ሚሊዮን ብር የካፒታል በጀት ለ2012 ዓ.ም በማጽደቅ፡ እንዲሁም የ2012ቱን እና 2013ቱን የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅነት በቅደምተከተል ለትግራይ እና አማራ ክልሎች ሀላፊነት በመስጠት ጉባኤውን አጠናቋል፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *