አዲስ አበባ ነሀሴ 03/2011 ዓ.ም – የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ነሀሴ 04 እና 05/ 2011 ዓ.ም (ቅዳሜ እና እሑድ) በደብረብርሃን ከተማ ኤቫ ሆቴል ያካሂዳል፡፡
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስም ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለሚዲያውም ሆነ ለህብረተሰቡ ስለ ጉባኤውም ሆነ ስለጉባዔው አጀንዳዎች በይፋ ያሳወቀው ነገር የለም፡፡
ልዩስፖርት ድረ-ገፅ ስለ ጉዳዩ ባደረገችው ማጣራት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ ሌሎችም የተወሰኑ የጠቅላላ ጉባኤ አባል የሆኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እና ተቋማት ይፋዊ ጥሪ እንዳልደረሳቸው እና መተዳደሪያ ደምቡ በሚያዘው መሠረትም የጉባኤው አጀንዳዎች ለአባላቱ ከአንድ ወር በፊት ቀድመው እንዳልደረሱ እንዲሁም ተጨማሪ አጀንዳዎችን ለማስያዝ እድሉ እንዳልነበራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ነገ ጠዋት በሚጀመረው የኦሊምፒክ ኮሚቴው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፡ የተቋሙ መሪዎች ልዩ ልዩ የህግ እና የአሰራር መመሪያዎችን የማሻሻል ፍላጎት እንዳላቸው እና ነገር ግን በህጉ መሠረት ቀደም ብሎ አጀንዳዎቹ ያልደረሳቸው የጉባኤው አባላት በሂደቱ ላይ ተቃውሞ ሊያሰሙ እንደሚችሉም ይጠበቃል፡፡