የግል ምልከታ | በዘርዓይ እያሱ (የስፖርት ጋዜጠኛ)| ለ ልዩ ስፖርት ብቻ |


አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኙ መፅሃፍ አዟሪዎች መካከል አንዱ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የተፃፉ መፃህፍትን በሁለት እጆቹና በደረቱ አስደግፎ ይዞራል፡፡ በወቅቱ የመግዛት ፍላጎት ኖሮኝ ሳይሆን የስፖርት መጽሐፍት ለምን ገበያ ላይ በብዛት እንደሌሉ ለማወቅ ካለኝ ጉጉት የተነሳ ስለ ሃገራችን ስፖርት የተፃፉ መፅሃፎች ካሉት ብዬ ጠየኩት፡፡

ጥያቄዬ አልጣመውም መሠለኝ ፊቱን ጣል አድርጎ የለም ብሎ መለሰለኝ፡፡ በእርግጥ የተሰጠኝ መልስ ቀድሜ የገመትኩት አይነት ነበር፡፡ ቢሆንም ለስለስ ብዬ ደግሜ እንዴት? ስል ጠየኩት፡፡ ››በመጀመሪያ በእርሱ ዙሪያ የተጻፉት መጻህፍቶች ጥቂት ናቸው ቀጥሎ ደግሞ የፖለቲካ እንጂ የስፖርት መፅሃፍ የሚያነበው ሰው ብዙ አይደለም›› ሲል መለሰልኝ፡፡ አመላለሱ ላይ የተመለከትኩት የእርግጠኝነት ስሜት በጥናት የተረጋገጠ ነበር የሚመስለው፡፡

መፅሃፍ አዟሪው ይህንን ያለው ከልምዱ በመነሳት እንደሆነ ብገምትም እኔ ደግሞ፡ ለመሆኑ ሃገራችን ከስፖርቱ ጋር ካላት የረጅም ዘመን ቁርኝት አንፃር በበቂ ሁኔታ የተፃፉ የስፖርት መፃህፍት ይኖሩን ይሆን ስል ከራሴ ጋር ውይይት ይሁን ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ባልለየሁት ስሜት ተዋጥኩ፡፡ መልሱ በፍጹም! ለመሆኑ ግን ብዙም ጥናት የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ የአዟሪው ሃሳብ ትክክል ነው ብለን ልንወስድ እንችላለን፡፡

መልካም አጋጣሚዎች

የብዙ ጀግኖች ስፖርተኞች መፍለቂያ የሆነቸው ሀገራችን፡ ከሀገራቸው አልፎ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ እንደ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አይነት የእግር ኳስ ባለሞያዎች ባሏት ኢትዮዮጵያ ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የክቡር አቶ ይድነቃቸው የህይወት ተሞክሮ እስከአሁን ካተባለው በላይ ለምን ለትውልድ እንዲተላለፍ ሆኖ አልቀረበም? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡

በአትሌቲክሱም በኩል ከተመለከትን ታላቁን አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ለቁጥር የሚታክቱ አሸናፊወች ከእኛ አልፎ ለመላው አለም ከሚተርፍ እጅግ አስተማሪ የህይዎት ተሞክሮዋቻቸው ጋር በቅርባችን ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሚያብራራ መፅሃፍስ ለምን ተዘጋጅቶ ለመጪው ትውልድ አይተላለፍም? አሁንም ሌላ ጥያቄ፡፡

በእርግጥ መፅሃፍን መፃፍ ’’ለምን አልተፃፈም’’ ብለን እንደምንጠይቀው ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ብዙ ፈታኝ ነገሮች አሉት፡፡ በተለይ ደግሞ በታሪኩ ባለቤት የማይፃፉ ግለ ታሪኮች ፀሃፊው ስለማያውቃቸው የሃሳቡን ፍስት ጠብቆ እና እውነትነቱ ሳይዛባ ለመፃፍ ያስቸግራል፡፡ ይህን ደግሞ እኔ እራሴ በተጨባጭ ገጥሞኝ አይቸዋለሁ፡፡

የግል ተሞክሮ

በስፖርት ጋዜጠኝነት ቆይታዬ ሶስት መፅሃፎችን ለአንባቢያን አድርሻለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ግለ ታሪኮች ሲሆኑ አንደኛው ’’ ከሜዳ ውጪ’’ የሚል ርዕስ ያለው ሆኖ በእግር ኳስ ሞያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

እነዚህን መፅሃፎች በምፅፍበት ግዜ ያገኘሁት ትልቅ ትምህርት ቢኖር፡ በይዘት ቢለያይም ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ታሪክ ያለው መሆኑን ነው፡፡

መፅሃፎቹን በመፃፍ ሂደት ውስጥ ለእኔ ከባዱ ስራ የነበረው ሁለቱን ግለ ታሪኮች ለአንባቢያን አመቺ በሆነ መልኩ መረጃዎቹን ማደራጀት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ የፃፍኩት መፅሃፍ የብርሃኑ ግዛውን የህይወት ተሞክሮ የሚናገረውን መፅሃፍ ነው፡፡ ታሪኩን ቀደም ሲል የማላውቀው በመሆኑ ራሴን ችዬ ለመፃፍ እጂግ ተቸግሬ ነበር፡፡

ታሪኩ እየተነገረኝ እፅፍ ስለነበር ከታሪኩ ባለቤቶች ጋር ተገናኝቶ መረጃዎቹን ለመውሰድ የሚመቻቸውን ግዜ መጠበቅና የእውነታውን ቅደም ተከተል ጠብቆ ለመፃፍ ብዙ ማሰብና መጨነቅ እንዲሁም ግብአቶችን እስካገኝ ትዕግስተኛ መሆን ይጠበቅብኝ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የማላውቀውን ታሪክ መፃፍ ፈትኖኝ የነበረ ቢሆንም አውቃቸዋለሁ ብዬ የማስባቸው ሰዎች፡ ላይ ላዩን እንጂ በደንብ እንደማላውቃቸው ያየሁበት፤ የሰው ልጅ የዛሬውን መልካም ምስል ለመመልከት በመጀመሪያ ብዙ መስዋትነት መክፈል እንዳለበት በደንብ ያሳየኝ በመሆኑ በብዙ የተማርኩበት ነው፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያዬ ለረጅም አመታት የማውቃቸው ብርሃኑ ግዛው እና መሠረት ማኔ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ መስዋትነትን እንደከፈሉ የተረዳሁት ግለ ታሪካቸውን ከፃፍኩ በኋላ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ለማመን ይከብዳሉ ግን እውነት ናቸው፡፡ አስተማሪ ናቸው፡፡ ከፍ ለማለት ዝቅ ብሎ መጀመር ተገቢ መሆኑን የሚያዩ ናቸው፡፡ እናም ይህን ታሪካችንን ሌላውም ይወቅልን የሚማርበትም ካለ ይማርበት ብለው ግለ ታሪካቸውን እንዲፃፍ አድርገዋል፡፡ ይህ ተሞክሮ በሌሎችም ሲደገም ብዙዎች ልምድ ያገኛሉ፤ እነሱም ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክን ፅፈው ያስቀምጣሉ፡፡

ከላይ እንደገለጽነው ለእግር ኳሱም ሆነ ለአትሌቲክሱ ያላቸውን የሰጡ ብዙ ስኬታማ የስፖርት ባለሞያዎች በሀገራችን ይገኛሉ፡ እነዚህ ባለሞያዎች በስፖርቱ ውስጥ ሃገራችንን ውጤታማ ለማድረግ ብዙ ሰርተዋል፤ ውጣ ውረዶችን አይተዋል በመሆኑም እነኚህ ባለሙያዎች ያሳለፉትን ጊዜ በተገቢው መንገድ ጽፈውልን እውቀት እና ልምዳቸውን የሚያካፍሉባችው ግለ-ታሪኮችን እና የምርምር ውጤቶቻቸውን ማካፈል ይኖርባቸዋል፡፡

ነገር ግን ይህ ነገር በሀገራችን ያልተለመደ በመሆኑ ምክንያት የብዙዎቹን ባለሞያዎች የስኬታማነታቸውን ምስጢር በጥልቀት አናውቀውም፡፡ ብናውቀውም እጅግ በጣም ትንሹን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ ባለሞያዎቻችን ስራዎቻቸውን የሚናገሩ ሰነዶችን በበቂ ሁኔታ አለማኖራቸው ነው፡፡

ምንአልባትም የልምድን ማካፈል ጥቅም ከአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ መማር ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ’’የፒያሳ ልጅ’’ በሚለው መፅሃፋቸው በስፖርት ጋዜጠኝነታቸው ወቅት ያካበቱትን ልምድ ሲያሰፍሩ በእሳቸው ዘመን የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴና ውጤታማነት እንዲሁም በመንግስት ዘንድ ይሰጠው የነበረውን ትኩረት በጥሩ ሁናቴ አብራርተው በሰፊው አስቀምጠውታል፡፡

አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የነገሩን አሁን ስላለው የኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክና የግል ተሞክሮአቸውን ሳይሆን ከ40 ዓመት በፊት የሆነውን ነው፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ስፖርት ምን ይመስል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአለም ስፖርት ውስጥ የነበራትን ሚና ምን እንደነበር እና እርሳቸው በጋዜጠኝነት ሞያ ስላሳለፉት ግዜ ፅፈው ለመጪው ትውልድ ይኸው ብለዋል፡፡

ሌሎች ስኬታማና ዝነኛ ሰዎችስ ለምን ይህን ማድረግ አልቻሉም? ልዩነቱ የይዘት ካልሆነ በቀር እዚች ምድር ላይ ያለ የሰው ፍጡር ሁሉ ታሪክ አለው፡፡ ይዘቱ መለያየቱ ደግሞ ሰዎች የተለያየ ተሞክሮ እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው ምንም አይነት ጉዳት የለውም፡፡ እናም ታሪክን ለመጪው ትውልድ ማኖር አስፈላጊና የሚመከርም መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡

ተግዳሮት

በሃገራችን ብዙ ሰዎች በመፅሃፍ መልክ ሊዘጋጁ የሚችሉ ብዙ ሃሳቦች እንዳላቸው እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ደግሞ መጽሀፍ ማሳተም እንደሚታሰበው ቀላለ የሚባል ስራም አይደለም፤ በብዙ ፈተናዎች የታጀበ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ እና ዋነኛው ጣራ ያለፈው ውዱ የህትመት ዋጋ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን አይነት ችግሮችን ተቋቁሞ ለትውልድ የሚሻገር መፅሃፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ማጣት፡ ብዙዎች የሚነገርና የሚያስተምር ታሪክ እያላቸው ለራሳቸው ብቻ እንዲያስቀሩት ግድ ብሏቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ተግዳሮት ምክንያት ብቻ ጠቃሚና አስተማሪ ሃሳቦች ባክነው እንዳይቀሩ ሲባል መንግስትን ጨምሮ አቅሙ ያላቸው አካላት ለፀሃፊያን ድጎማ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው እላለሁ፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን የስፖርት መፃህፍት ማለት የስፖርተኞች ግለታሪክ ብቻ ማለት እንዳልሆነም እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ከግለ ታሪክ በተጨማሪም በስፖርቱ ባለሞያዎች ዘንድ በቂ ምርምር ተደርጎባቸው የሚወጡ ስፖርታችንን የሚያሳድጉ መጽሐፍቶችንም ከምሁራኑ እጠብቃለሁ፡፡

በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ በሃገራችን የስፖርት ሳይንስ ትምህርት እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ በዘርፉ የተማረው የሰው ሃይል ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ይህ ስፖርቱን ሳይንሳዊ መሠረት ለማስያዝ የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ ሆኖ የስፖርት ቤተሰቡንና ባለሞያዎችን ግንዛቤ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸውን መፃህፍቶችን ቢያዘጋጁ የሚል ሀሳብ ይነሳል፡፡

በእነዚህ ባለሞያዎች የሚዘጋጁ መፃህፍቶች ለስፖርተኞችና ለአሰልጣኞች ለስልጠናና ለማስተማሪያት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ደግሞ ለብዙሃን መገናኛዎችና ለሌሎችም ባለሞያዎች በማጣቀሻነት የሚያገለግሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡


ስለ ጸሀፊው


ዘርዓይ እያሱ (የስፖርት ጋዜጠኛ)

በአሁኑ ወቅት በዋልታ ቴሌቭዥን የስፖርት ክፍል ኤዲተር በመሆን እያገለገለ የሚገኝ ባለሞያ ነው

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *