ሐተታዊ አስተያየት | በመንሱር አብዱልቀኒ (የእግር ኳስ ጋዜጠኛ) | ለ ልዩ ስፖርት ብቻ |


‹‹እነሆ የሐረርጌ ቡድኖች በክለብም ሆነ በክፍለ ሃገር ደረጃ ዋንጫ ካገኙ 10 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ዋንጫ ይጓዝበት የነበረው ባቡር፣ ደጋፊዎች አያሆ! ሆ! ማታ ነው ድሌ! ያሉበት የድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ፣ ሉካንዳ ነጋዴዎች የከተማው ህዝብ ሽሮ እንዲበላ ፈርደውበት ሽንጡን ይዘው እየበረሩ፣ ዋንጫ ተቀብለው ሽንጥ የሸለሙበት ያ የቀድሞ ድል ተመልሶ ይመጣ ይሆን?…›› እያለ ጥያቄውን አስቀድሞ ጽሁፉ ሐተታውን ያስከትላል፡፡ ደምሴ ዳምጤ የ10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን አስመልክቶ ከ43 ዓመታት በፊት በታተመ አንድ የስፖርት መጽሔት ላይ የጻፈው አስተያየት ነው፡፡ ወጣቱ ጋዜጠኛ የትውልድ ክልሉ ክለቦች ውጤት ማሽቆልቆል አሳስቦት ብዙ ይላል፡፡ በ1952፣ 54፣ 55 እና 57 ዓ.ም ለአራት ዓመት ጥጥ ማህበር (ኮተን)፣ ከ1953 እስከ 1956 ደግሞ ድሬዳዋ ሲሚንቶ ከክልላቸው አልፈው የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ የደምሴ ጭንቀት ከዚያ በኋላ ባሉት 10 ዓመታት የሐረርጌ ክፍለ ሃገር ክለቦች ውጤታማነት መዳከም ነበር፡፡

ነፍሱን ይማረውና ጋዜጠኛው አሁን በህይወት ቢኖር ምን ይል ይሆን? በ1990 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካለምንም ጥናት፣ ያለ ጊዜው ከተወለደ በኋላ የከተማ ወይም ክልል ሻምፒዮናዎች ቀስ በቀስ ላምባ እንዳለቀበት ፋኖስ እየደበዘዙ ጠፍተዋል፡፡ የከረረው የድሬ ጸሐይ ሳያግደው በየሳምንቱ የከተማውን ክለቦች ፍልሚያ ይመለከት የነበረው የዚያ ትውልድ እግር ኳስ አፍቃሪ ዛሬ በአንድ አንኳር ክለብ ብቻ ቀርቶ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታን ብቻ ይመለከት ዘንድ ተፈርዶበታል፡፡

እንደ ድሬዳዋ ሁሉ የአዲስ አበባ እግር ኳስም በፕሪምየር ሊጉ ግብታዊ መርዝ መርፌ ተወግዶ በቀስታ ወደ ሞት እየተጓዘ ነው፡፡ በሊጉ ላይ የአዲስ አበባ ክለቦች ቁጥር እያደር እየከሰመ፣ ተጽኗቸዉም እየተዳከመ ሄዷል፡፡ የዚያኑ ያህል በከተማዋ የነበሩ ትልልቅ ክለቦች ቀስ በቀስ ከአይናችን ተሰውረዋል፡፡ ክዋክብት ይወለዳሉ፣ ደምቀው ይታያሉ፣ በኋላም ይሞታሉ የሚለው የስነ-ጠፈር እውነት በአዲስ አበባ ክለቦች ላይም እውን እየሆነ መጥቷል፡፡ የመንግስት የልማት ተቋማት ክለቦች ቁጥር እየቀነሰ የከነማ ክለቦች ቁጥር እየጨመረ በሄደበት በዚህ ዘመን የሸገር ክለቦች ከአዲስ ፈተና ጋር ተጋፍጠዋል፡፡ ሆኖም ህመማቸውን ያየላቸው የለም፡፡

አሥራት ኃይሌ በቅ/ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት

የከነማ ክለቦች ቁጥር መብዛት በመርህ ደረጃ ጥሩ ነው፡፡ የክለቦቹ የፋይናንስ አጠቃቀም ግን ጤናማ ውጤት የሚያስከትል አይደለም፡፡ የታክስ ከፋዩን ህዝብ ገንዘብ በማይገባ መጠን እግር ኳሱ ላይ ማፍሰሳቸው መሟላት ያለባቸው ብዙ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላሉባቸው ከተሞች ታላቅ ጥፋት ነው፡፡ የፋይናንስ ጨዋነት ደንብ ባለመኖሩም የተጫዋቾች ደመወዝና የፊርማ ክፍያ ግሽበት ከስፖርትም የዘለለ ዓላማ ያነገቡትን አንዳንድ የክልል ክለቦች ቅጥ ላጣ ወጪና ብክነት አጋልጧቸዋል፡፡ ይህም በቀጥተኛነት በታክስ ከፍዩ ህዝብ ገንዘብ ላይ ያልተንጠላጠሉትን ህዝባዊያን እግር ኳስ ክለቦችን ለፈተና ዳርጓል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንደ ‹‹እገሌ ከነማ›› እጅግ ከፍተኛ ዓመታዊ በጀት የመመደብ አቅምና እምነትም የላቸውም፡፡ ተጫዋቾች በሌሎች ክለቦች ከፍ ያለ ክፍያ የሚከፈላቸው መሆኑ እያደገ ከቀጠለ ሁለቱን የሸገር ክለቦች የመምረጥ ዕድላቸው ጠባብ ነው፡፡ በዚሁ የክለቦቹ ተፎካካሪነትም አብሮ መዳከሙን ይቀጥላል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሪፎርም ጥናት ከሆነ በፕሪምየር ሊጉ፣ በከፍተኛ ሊግና በአንደኛ ሊግ እስከ ግንቦት 30 ድረስ የመንግስት ክለቦች የጨረሱት በጀት 2.2 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ያለው ቢጨመርበትስ ብላችሁ አስቡት፡፡ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ዝቅተኛ ዓመታዊ በጀት የሚባለው 58 ሚሊዮን ብር መሆኑን የአንድ ክልል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አጫውተውኛል፡፡

ድህነት ድሪቶውን ላከናነበን ለእኛ ኢትዮጵያዊያን 2.2 ቢሊዮን ብር ስንቱን ገመናችንን ይሸፍንልን ነበር? እንደ መንግስት የቅርብ ጊዜ መረጃ ከሆነ ተወልጄ ባደግኩባት አዲስ አበባ በዚህ ሰዓት 700ሺህ ስራ አጥ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 170ሺህ ያህሉ ስራ እንዲያገኝ ያስችላል የተባለው ተዘዋዋሪ ፈንድ 2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ በደቡብና ኦሮሚያ መዋሰኛ አካባቢ የሚገነባው የጊዳቦ የመስኖ ፕሮጀክት (በዛ ተብሎ) የሚያስፈልገው 1.2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይኽው ገንዘብ 62.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ ውሃ አለው በተባለ በዚህ ግድብ 13,425 ሄክታር የእርሻ ቦታ የማልማት አቅም አለው፡፡ 10ሺህ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ለ192,000 ወጣቶች የስራ ዕድል ይከፍታል፡፡ በምስራቅ ጎጃም ቡሬ ከተማ የሃገሪቱን 60% የምግብ ዘይት ፍላጎት ያሟላል የተባለለት ግዙፍ የግል ፋብሪካም ኢንቨስትመንት 2.1 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ይህም ካልበቃ ሌላም ማነጻጸሪያ ልጨምር፡፡ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ባለባት አዲስ አበባ 10ሺህ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ መጠን የተዝረከረከ አስተዳደር ላለው እግር ኳስ፣ በመንግስት ክለቦች የዘንድሮው በጀት ፈሷል፡፡

ቢሊዮኖች ወጪ በሚሆንበት ፉትቦል አንድም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መጫወቻ ሜዳ (ስታዲየም አላልኩም) አለመኖሩ እግር ኳስን የማስተዳደር ነገር ለኢትዮጵያችን ሮኬት ሳይንስ እንደሆነባት ያረጋግጣል፡፡ የሜዳዎች ጥራት ማነስ ደግሞ የተጫዋቾችን ክህሎት ከማሳደግ ይልቅ ያዳክመዋል፡፡ እንዳይጎመራ በማክሰም ብቻ አያበቃም፡፡ ተዋንያኑን ለዕድሜ ልክ የመገጣጠሚያ፣ የቁርጭምጭሚትና የጅማት ህመም ይዳርጋል፡፡

‹‹የወላይታ ድቻ ሜዳ ተዳፋት ነው፡፡ የጨዋታን ግማሽ ዳገታማ፣ የጨዋታውን ግማሽ ቁልቁለታማ ሜዳ ላይ ትጫወታለህ ማለት ነው›› ይላል – ለስምንት የሊጉ ክለቦች ተዘዋውሮ የተጫወተው አንጋፋው ዳዊት እስጢፋኖስ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ የነበሩት ስቴዋርት ሐል በእንዳስላሴ ከተማ የስሁል ሽሬን ሜዳ በቦታው እንደተመለከቱ የጨዋታ ስልታቸውን ከቀጥተኛ ጨዋታ ወደ ጎንዮሽ ቅብብል እንዲቀይሩ ተጫዋቾቻቸውን ማዘዛቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ለሃሳብ ለውጡ ምክንያታቸው የሜዳው የቁመትና የጎንዮሽ ርቀት ምጣኔ ያልተለመደ መሆኑ ነበር፡፡ ለሬዲዮ ዘገባ ባደረግነው አንድ ጥናት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በሃገራችን ለሊግ ውድድር የሚያገለግሉ ሜዳዎች ጥራት ቀርቶ ቁመትና ወርዳቸው በፊፋ ደረጃ ስለመመጠናቸው የሚያረጋግጥ ኦፊሴላዊ ምዝገባ እንኳን የላቸም፡፡ የቁመት/ወርድ መመጣጠን ላይ ደንቡ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ካሬ መሆን ወይም ወደ ካሬ መቅረብ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሜዳዎች ግን የፊፋን የመጠን ድንጋጌ ስለማሟላታቸው ምሎ የሚናገር የስፖርት መሪ ማግኘት አይቻልም፡፡

የቅ/ጊዮርጊስ የጎል ፐርፎርማንስ ማሽቆልቆሉን የሚያሳይ ግራፍ

የሊጉ ክለቦች ብዛት ተጽዕኖ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች ብዛት ሲጀምርም አልተጠና፣ የተሳታፊ ክለቦች ብዛትም ከ12 ወደ 14፣ ከ14 ወደ 16 ያደገበት አሳማኝ ምክንያት የለውም፡፡ እኛ ስንወስን እንዲህ ነን፡፡ ለምን እንደምንጨምር፣ ለምን እንደምንቀንስ አናውቀውም፡፡ ለምን እንደምናሸንፍ አናውቅም፡፡ የምንሸነፍበትንም ምክንያት በቅጡ አንረዳም፡፡ እንደው እንዲሁ እንደነገሩ፣ እንደመሰለን ያለኮምፓስ ስለምንጓዝ አንድ ቦታ ስንደርስ አቅጣጫ ይጠፋብናል፡፡ ከፊት ለፊታችንም ተስፋ ማየት እንኳን አልቻልንም፡፡ የሊጉን ፎርማት ከማይደግፉት ወገኖች አንዱ ብቻ ሳልሆን፣ የሊጉ ክለቦች ቁጥርም 16 መሆኑ አቅማችንን ያገናዘበ አይደለም ብዬ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ቁጥሩ ይጨመር ሲባልም በጊዜው ተቃውሞዬን በኢትዮ-ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቶቼ ላይ ጽፌያለሁ፡፡

የሊጉ ክለቦች ቁጥር 14 በነበረበት በ2004 ዓ.ም. መቀመጫቸውን ሸገር ላይ ያደረጉ ክለቦች ብዛት ሰባት ነበር፡፡ የሊጉን እኩሌታ ቁጥር መያዛቸው በሌሎች የክልል ክለቦች ላይ የማይገባ የፉክክር ጥቅም ያስገኝላቸው ነበር፡፡ በሰንጠረዡ ግርጌ የጨረሰው ፊንጫ ስኳር በመኪና እየተዟዟረ ተዳክሞ ሲጫወት፣ ሰባቱ ክለቦች ብዙሃኑን የሊግ ጨዋታዎች ያለጉዞ ድካም በአዲስ አበባ ያካሂዱ ነበር፡፡ በዚያ ዓመት በሰንጠረዡ እስከ አራተኛ የነበረውን ቦታ ይዘው ያጠናቀቁት የአዲስ አበባ ክለቦች መሆናቸዉ አያስገርምም፡፡ በሊጉ በጨዋታ የሚቆጠረው አማካይ የጎል መጠን 2.34 የነበረ ሲሆን እስካለንበትም 2011 ድረስ ይህን ያህል ጎል በአማካይ የተመዘገበበት ዓመት ከዚያ ወዲህ አላየንም፡፡ የዘንድሮው ደደቢት በደረሰበት ከባድ የፋይናንስ ችግር ምክንያት ስብስቡን በማሳሳቱ ዘንድሮ የሊጉ እጅግ ደካማው ቡድን በመሆን በዘጠኝ ዓመታት ከታየው ሁሉ መጥፎውን የጎል ዕዳ ይዞ ወርዷል፡፡ ይህም የሊጉን የጎል ብዛት ያለምክንያት አሳድጎታል፡፡

የ14 ክለቦች ሊግ ከ16 ክለቦች ሊግ የተሻለ ንጻሬ አለው፡፡ በጨዋታዎች መካከል በቂ የማገገሚያ ጊዜ የሚሰጥ መርሐግብር ስለነበር በንጽጽር ያልተዳከሙ ተጫዋቾች በየጨዋታው የመገኘታቸው ዕድል ከፍ ያለ ስለነበር የጨዋታውም ኢንተንሲቲ የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖርም፡፡ የሊግ ክለቦች ቁጥር የሚጨመርበትና የሚቀነስበት በጥናት የጎለበተ ስፖርታዊ ምክንያት መኖር ነበረበት፡፡ ሌላው ቢቀር በዓመት የ58 ጨዋታ ልዩነት ስለፈጠረ፣ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ከሊጉ ካሌንደር ጋር ተጣጥሞ የመከናወኛ ጊዜ በማጣቱ ለዛ ቢስ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡

የሊጉ ተወዳዳሪዎች ብዛት በመደበኛነት 16 ሲደረግ የሊጉ አማካይ የጎል መጠን እያሽቆለቆለ መጣ፡፡ በሊጉ የአዲስ አበባ ክለቦች ብዛት በቀነሰ ቁጥር የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የጎል ፐርፎርማንስ እየወረደ ሊሄድ ተገዷል፡፡

በስምንት ዓመት ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ የዓመቱ መጨረሻ የግብ ክፍያ ከ39 ወደ 10 አሽቆልቁሏል፡፡ የሊጉ የጨዋታ አማካይ ጎል መጠንም ከ2004 እስከ 2010 ባለው የጊዜ ርቀት በጨዋታ በአማካይ በ0.48 ጎል ቀንሷል፡፡ ያለግብ የሚጠናቀቁ ጨዋታዎች ብዛት እየጨመረ፣ የሊጉ አዝናኝነት እየቀነሰ ሲመጣ ያስተዋለው የለም፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ነገር ይበልጥ አስደንጋጭ ነው፡፡ የሊጉ ሻምፒዮን ከሆነበት ከ2003 ወዲህ በየጨዋታው የሚሰበስበው አማካይ ነጥብ ከ2.1 ወደ 1.3 አሽቆልቁሏል፡፡ በሊጉ ላይ ሰባት የአዲስ አበባ ክለቦች በነበሩበት 2003 እና ሶስት ብቻ በቀሩበት በ2011 መካከል ቡና በአማካይ በየጨዋታው የ0.8 ነጥብ ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ በጎል መጠንም ቢሆን በሁለቱ ዘመናት መካከል በጨዋታ 0.8 ጎል ቀንሷል፡፡ ሊጉ በዚሁ መልኩ ከቀጠለ፣ ሁለት የሸገር ክለቦች ብቻ በቀሩበት በ2012 የኢትዮጵያ ቡና ዕጣ ምን ይሆናል?

የኢትዮጵያ ቡና የጎል እና የነጥብ ፐርፎርማንስ በአስደንጋጭ ሁኔታ አሽቆልቁሏል

የቅዱስ ጊዮርጊስም ነገር እንዲሁ ሳይታይ መታለፍ የለበትም፡፡ ከፍተኛ ጎል ካስቆጠረበት ከ2006 ወዲህ በአምስቱ ዓመታት ‹‹የጎል ምርቱ›› ቀንሶበታል፡፡ ቢያንስ የ27 ጎሎች ልዩነት አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነው በዘንድሮው ውድድር ‹‹ፈረሰኞቹ ሶስት ጨዋታዎችን ባለመጫወታቸው ነው›› የሚል ሙግት ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሶስቱን ጨዋታዎች ቢጫወቱና በእያንዳንዳቸው ስምንት፣ ስምንት ጎሎችን ቢያስቆጥሩ እንኳን ልዩነቱ የሚጠብ አይሆንም፡፡ በ2006 አንድ ክለብ 26 ጨዋታዎች ሲጫወት፣ 30 ጨዋታዎች ከሚያደርግበት 2011 ጋር በአራት ጨዋታ እንደሚያንስም ልብ ይሏል፡፡ የጨዋታዎች ቁጥር በዝቶ የጎሉ መጠን ይህን ያህል ዝቅ የሚልበት አንድ አንገብጋቢ ምክንያት ከሌለ በስተቀር በጤና እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡

እነዚህ እና በየግራፎቹ ላይ የሚታዩት በዘመን መካከል ያሉ ሌሎች ልዩነቶች ሁለቱ የአዲስ አበባ ክለቦች የፐርፎርማንስ ህመም እየጠናባቸው መሆኑን ያሳያሉ፡፡

ስፖርታዊ ባልሆኑ ምክንያቶች በተለይ ከሜዳ ውጭ ተጉዞ ማሸነፍ ብርቅ በሆነበት በዚህ ዘመን 2012 ላይ የሊጉን ባህሪይ በአዎንታ የሚቀይር ሰማያዊ ተዓምር አይመጣም፡፡ አካሄዱ ሁሉ ነገር ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሆን የሊጉ አካሄድ ራሱ እየነገረን ይገኛል፡፡ ጨዋነት የሚታይባቸው የክልል ክለቦች ያሉ ቢሆንም፣ በተጫዋቾች ላይ የስጋት ሸክም የሚጭኑ ስታዲየሞች የተበራከቱበት ሊግ ላይ ተጫዋችም ሆነ አርቢትር በሜዳ ላይ ያለጭንቀት፣ በስፖርታዊ መንፈስ ውስጥ ብቻ መቆየት አይችሉም፡፡ አንጋፋው ዳዊት እስጢፋኖስ በክልል ጨዋታዎች ላይ ለእንግዳ ቡድን ተጫዋቾች ‹‹ምክር የሚለግሱ›› አርቢትሮች መኖራቸውን ይናገራል፡፡ ‹‹አንተ ከምትሞትና ቡድንህ ከሚሸነፍ›› የሚል አማራጭ እንደሚሰጧቸው ከብስራት-ስፖርት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ላይ ገልጿል፡፡ ‹‹መሸነፍ ቀርቶ አቻ ውጤት የማይፈለግባቸው ከተሞች አሉ›› የሚለው ዳዊት እንግዳው ቡድን አሸንፎ ብቻ ሳይሆን፣ ጨዋታው በአቻ ከተጠናቀቀ እንኳን የደጋፊዎች ጥቃት ሊከተል እንደሚችል በማስታወስ ‹‹ይህ ውድድር ፕሪምየር ሊግ ሲባል ይገርመኛል›› ሲል ለብዙ ክርክር በር የሚከፍት ሃሳብ ሰንዝሯል፡፡

የ1995ቱ ኢትዮጵያ ቡና ከጥሎ ማለፍ ዋንጫ ጋር

እንዲህ ከሆነ ጠንካራ ቡድን ለመገንባት መልፋቱ ለምን ያስፈልጋል? በሃገሪቱ ዋና ዋና ሚድያዎች ፊት በአዲስ አበባ የሚደረጉ ጨዋታዎች በንጽጽር ለሸፍጥና ስጋት የተጋጡ ባለመሆናቸው በአንጻራዊ ዕይታ የሸገር ጨዋታዎች ከክልል ጨዋታዎች ይልቅ በተሻለ ስፖርታዊ ምክንያት ውጤቶቻቸውን ይወስናሉ ማለት ይቻላል፡፡

ክለቦቹ በራሳቸው ሜዳ እንደዕለቱ ብቃታቸዉ ላባቸውን የሚያገኙ ከሆነና በክልል ግጥሚያዎች ዳዊት በገለጸው ምክንያት ሆን ብለው ለመሸነፍ የሚገደዱ ከሆነ ከዚህ በኋላ (የነገሮች አካሄድ በዚሁ ከቀጠለ) በልፋታቸው ልክ ፍሬ ይሰበስባሉ ለማለት ይቸግራል፡፡

ይህም የከተማዋን ክለቦች የፉክክር ዕድል አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ በ2012 ከምንጊዜውም በበለጠ የሸገር ክለቦች በጉዞ ይደክማሉ፣ ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎቻቸው ይበዛሉ፡፡ ከ2011 ይልቅ ወደ ሶስት አዳዲስ የክልል ሜዳዎች ተጉዘው የመጫወት ግዴታ አለባቸው፡፡ በመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ስንብት ምክንያት አዲስ አበባ በዓመት 30 ብቻ የሊግ ጨዋታዎች የሚደረጉባት ከተማ ሆናለች፡፡ በሚድያ ከሚሰማው ይልቅ ፕሪምየር ሊጉ ከአዲስ አበቤዎች በአካል እየራቀ ሄዷል፡፡ ከከተማዋ በራቀ ቁጥር ደግሞ የሁለቱ አንጋፋ ክለቦች አሸናፊነት ዕድል (ስፖርታዊ በሆኑም ይሁን ባልሆኑ ምክንያቶች) እየቀነሰ መሄዱ መዲናችንን በእግር ኳስ ቀጣይዋ ድሬዳዋ ሊያደርጋት ይችላል፡፡

… ደምሴ ዳምጤ በዘመኑ አጻጻፍ ዘይቤ ሃሳቡን ቀጠለ፡፡ ‹‹ወደፊት ይታያል፡፡ የራቀው ድል ሊመለስ ይችላል፡፡ ምናልባት በመፍለቅ ላይ ያሉት ተጫዋቾች ከአልኮልና ከዝሙት ጥንቁቅ ከሆኑ…›› በማለት ስለድሬዳዋ እግር ኳስ ክለቦች ውጤታማነት ተስፋ ማድረጉን ለአንባቢዎቹ ነግሯል፡፡ አዲስ አበባ ግን እንደዚያን ዘመን ድሬዳዋ አይደለችም፡፡ ዕድሜ በየሰፈሩ ቤቶች ለተገነባባቸው ክፍት ቦታዎች፣ አዳዲስ ተስፈኛ ተጫዋቾችን በከተማዋ በብዛት ማየት ካቆምን ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ መተኪያው ምንጭ ደርቆ፣ የነበረው አርጅቶ ከእግር ኳሱ ይሰናበታል የሚለው ጭንቀቴ ዛሬም በተስፋ አልተተካም፡፡ በሁለቱ ክለቦች ቀጣይ ጉዞ ላይም ከአድማሱ ባሻገር ከተስፋ ብርሃን ይልቅ የስጋት ጭጋግ በጉልህ ይታየኛል፡፡ ስር ነቀል ለውጥ ካልመጣ በስተቀር፡፡


  ስለ ጸሀፊው


መንሱር አብዱልቀኒ (የእግር ኳስ ጋዜጠኛ)

በእግር ኳስ ጋዜጠኝነት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ በእግር ኳስ ጉዳዮች ትንተና ላይ ያተኮረው ‹‹ብስራት-ስፖርት›› ዋና አዘጋጅ ናቸው

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

2 Comments

  1. I share Mensur’s concern. I think this is the time to act, it is better to follow local peace full sport tournaments surrounding us with out interruption. and it will be more controllable to the extent we elders can approach and give advise to make the sport fields are enjoyable and entertaining. The wide the coverage of the sport atonement there is a high chance of trapping the system by individuals with so many interests than sport. I was one of the member of Foot ball team, table tennis team and Hand ball team at Kebele level late in 1960th and early 1970 at Dessie. There was rely enjoyable and entertaining. Almost in each family living at Dessie there was one spectator who follow one sport. (At that time there was regular sport games in Foot ball, Hand ball, Valyball , table tennis, Cycling in both genders )
    Why we do not take the system from previous government (Derge) if it is better for the benefit of the people.
    ‘Thanks’

  2. መንሱሬ ምን ልበልህ እንደት ብየ አድናቆቴን ልግለፅልህ!? አቦ ይመችህ እድሜህ ይርዘም! አንተ እያለህ ሸገር አንጋፋ ክለቦቿን ታጣለች ወይም ከስመው ይቀራሉ ብየ አልገምትም! ምክንያቱም ከሁለቱም ክለቦች ጀርባ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ ፣ዘረኛ ያልሆነ ፣በእግር ኳስ ብቻ የሚያምን ታማኝ ደጋፊ ስላላቸው!። ቢሆንም ግን ትግል ያስፈልጋል ካልሆነ የህልውናቸው ጉዳይ እጅግ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *