የግል ምልከታ| በአቶ ገዛኸኝ ወልዴ | ለ ልዩ ስፖርት ብቻ |


ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበርና የየሀገራት እግር ኳስ ፌደሬሽን ወይም ማህበራት የመጨረሻው ህግ አውጪ አካል ነው፡፡ (the supreme and legislative organ of football association) በእግር ኳስ ማህበራት ወይም ፌደሬሽን የጠቅላላ ጉባኤ አባላትና የጉባኤው ስልጣንና ተግባር በዝርዝር በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ እንዲካተት ይደረጋል ፡፡ በእግር ኳስ እንቅስቃሴ ውስጥ ድርሻ አላቸው የሚባሉ አካላት በጠቅላላ ጉባኤው ውስጥ ውክልና ይሰጣቸዋል ፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው የእግር ኳስ ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን በዋናነት ትኩረት የሚያደርግባቸው ነጥቦች መተዳደሪያ ደንቦችን ማውጣት ፣ዓመታዊ የማህበራት / የፌደሬሽን / ሪፖርት ማድመጥና ማፅደቅ ፣ዓመታዊ ዕቅድን መርምሮ ማፅደቅ፤ በመንግስት የሚወጡ የእግር ኳስ እቅዶችን እና የስፖርት ፖሊሲን ከፌደሬሽኑ እቅድ ጋር በማናበብ ተግባራዊ እንዲሆን መመሪያ መስጠት፤ በስትራቴጂክ እቅድ የተቀመጡ ግቦች፣ዓላማዎችና ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን (progress report ) ማረጋገጥ፤ በሁሉም የእድሜ ክልል እና ፆታ የተዋቀሩ ብሄራዊ ቡድኖችን በመከታተል ያጋጠሙ ችግሮች የሚፈቱበትን ስልት መቀየስ እንዲሁም የእግር ኳስ ልማት (football development)  ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ነው፡፡

ጠቅላላ ጉባኤውን የሀገራት እግር ኳስ አዕምሮ ልንለው እንችላለን። አዕምሮ ጤና ካጣ ደግሞ ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ይከተናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ህመም ዋናው መነሻውም ይሄው ነው።  የእግር ኳሳችን ድክመት የሚመነጨው ከጠቅላላ ጉባኤው አወቃቀርና አሰራር ነው፡፡

የምን ጠቅላላ ጉባኤ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተሻሻለው የ2006 ዓ.ም መተዳደሪያ ደንብ  አንቀፅ 8 መሰረት የፌደሬሽኑ አባላት በሚለው ላይ  ‹‹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አባላት የሚሆኑት፡- በማለት

1. የክልልና የከተማ አስተዳደር ፌደሬሽኖች ፣

2. ፌደሬሽኑ በባለቤትነት የሚያወዳድራቸው የፕሪምየር ሊግ እና የብሄራዊ ሊግ ክለቦች

3. በፕሪምየር ሊግና በብሄራዊ ሊግ ውስጥ የሚሳተፉ የሊግ ክለብ የሌላቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች፣

4. የኢትዮጵያ የዳኞች ማህበር ፣የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ማህበር ፣የኢትዮጵያ የሴቶች ተጫዋቾች ማህበር እና የኢትዮጵያ የወንዶች ተጫዋቾች ማህበራት ናቸው።›› እንደሆኑ ይዘረዝራል፡፡

ከዚህ አንቀፅ መረዳት እንደሚቻለው የፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በቁጥር አይታወቁም ፡፡ ምክንያቱም ስንት የብሄራዊ ሊግ ክለቦች እንዳሉ የሚታወቅበት ሁኔታ ስለሌለ በተጨማሪም በየዓመቱ የብሄራዊ ሊግ ክለቦች ስለሚፈርሱ፤ አዳዲሶች ስለሚመጡ እና  አዳዲስ የሊግ እርከኖችም ስለሚፈጠሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በፕሪምየር ሊግና በብሄራዊ ሊግ ውስጥ የሚሳተፍ  የሊግ ክለብ የሌላቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የፌደሬሽኑ አባል እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ እነማን ናቸው? የሊግ ክለብ የማይኖራቸው እስከመቼ ድረስ ነው? በጉባኤው የሚሳተፉ አባላትስ እነማን ናቸው? የክልሉ አስተዳደር ነው ወይስ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ? ወይስ የአማተር ክለብ ተወካይ? ስንት አማተር ክለቦችስ ይኖራሉ? የሚለውን አንቀጹ የመመለስ ችግር አለበት ፡፡

በማንኛውም ሁኔታ የሚካሄዱ የእግር ኳስ እንቅስቃሴዎችን የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ወይም የእግር ኳስ ማህበራት በበላይነት የመምራት የመቆጣጠርና የመከታተል ሙሉ መብት አላቸው፡፡ ለዚሁም ይረዳቸው ዘንድ በመተዳደሪያ ደንባቸው ተለይተው የተቀመጡ አጋር አካላትን ተባባሪ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት (associate member) በሚል ያካትቷቸዋል ፡፡

ለምሳሌ ያክል በደቡብ አፍሪካና በጋና እግር ኳስ ማህበራት በድምጽ የሚሣተፉ ተባበሪ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት የመጀመሪያ ደረጃ እና የክተኛ ትምህርት ቤቶች፤ ብሄራዊ የመከላከያ ሀይል፤ የኢንዱሰትሪ፤ መስማት የተሳናቸው፤ የአካል ጉዳትኞች እና የቤት ውሰጥ እግር ኳስ ማህበራቶች ሲሉ አስቀምጠዋቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ግን ተባባሪ አባላት ተብለው በድምጽ የሚሳተፉ የእግር ኳሱ ባለድርሻዎች የሉም። በጠቅላላ ጉባኤ የሚሳተፉ የዳኞች ማህበር፤ የአሰልጣኞች ማህበርና የተጫዋቾች ማህበርም ቢሆኑ ተባባሪ ይሁኑ ሙሉ አባላት ስለመሆናቸው በመተዳደሪያ ደንቡ የተገለፀ ነገር የለውም፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የሚያወዳድራቸውን የሊግ ውድድሮች በሶስት ደረጃዎች የከፈላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡  የመጀመሪያውና የሀገሪቱ ትልቁ ሊግ 16 ክለቦች የሚሳተፉበት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው 32 ክለቦች የሚሳተፉበት የሱፐር ሊግ ውድድር ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የብሄራዊ ሊግ ውድድር ነው፡፡

ከላይ በተገለፀው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ ስምንት የሱፐር ሊግ ክለቦች የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ስለመሆናቸው የሚገልጽ ሀሳብ የለውም፡፡ ነገር ግን በጠቅላላ ጉባኤው ይሳተፋሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ የሱፐር ሊጉን ውድድር የጀመረው ራሱ ካወጣው ህግ ጋር መጋጨት እና አለመጋጨቱን በሚገባ ሳያጤነው ነው ወይም መተዳደሪያ ደንቡን ሳያሻሽለው ነው፡፡

የጋና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የጠቅላላ ጉባኤ አደረጃጀት
ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ የጋና የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን የጠቅላላ ጉባኤ አደረጃጀትን ከዚህ ቀጥሎ ለምሳሌ እንመልከት፡-

በጋና 10 ክልሎች ይገኛሉ፡፡ በ10ሩ ክልሎች የሚገኙ የክልል እግር ኳስ ማህበራት የጠቅላላ ጉባኤ አባል ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የክልል ማህበር በሶስት ተወካዮች ይወከላል ፡፡ በአጠቃላይ 30 ተወካዮች የጠቅላላ ጉባኤ አባል ናቸው፡፡ የጋናን ፕሪምየር ሊግ የሚመራው ፕሮፌሽናል ሊግ (professional league) ፕሪምየር ሊግ ቦርድ ይባላል፡፡ 16 ተሳታፊ ክለቦች ሲኖሩት እያንዳንዳቸው በጋና እግር ኳስ ማህበር ሁለት ተወካዮች ይኖራቸዋል ፡፡

ብሄራዊ ዲቪዚዮን አንድ (national division one league) በስድስት ዞን ተከፋፍሎ 48 ክለቦች ይሳተፋሉ። ውድድሩን የሚመራ የብሄራዊ ዲቪዚዮን አንድ ቦርድ (national division one league board) ነው፡፡ እያንዳንዱ ክለብ በእግር ኳስ ማህበሩ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፡፡ የአሰልጣኞች ማህበር ፣የዳኞች ማህበር ፣የሴቶች እግር ኳስ ማህበር፤ የወጣቶች እግር ኳስ ማህበር እና የተጫዋቾች ማህበር እያንዳንዳቸው ሁለት ተወካዮች ይኖራቸዋል ፡፡

በተመሳሳይ የደህንነት አገልግሎት ስፖርት ማህበር፤ የትምህርት ቤት፤ የኮሌጅ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እግር ኳስ ማህበራት እያንዳንዳቸው በአንድ ተወካይ የእግር ኳስ ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አባል ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የጋና እግር ኳስ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብዛት 123 ነው፡፡

የአንባቢዎችን ጊዜ ለመቆጠብ ስል ዝርዝሩን እንደገና ባላስቀምጠውም ሌላ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ቅርብ የሆነ ተሞክሮ የሚገኝበት የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጠቅላላ ጉባኤ ስብጥር እና አወቃቀር ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት እነማን እንደሆኑና ያላቸውን የድምፅ ውክልና ጭምር በዝርዝር አስቀምጧል ፡ የጠቅላላ ጉባኤ አባላቱ ብዛትም 182 ሲሆን የድምፅ ውክልናው ደግሞ 224 እንደሆነ ይገልጻል፡፡

የሀሳብ ድርቅ?

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ የሚታየው ችግር የአደረጃጀት ብቻ ሳይሆን በጉባኤው ተነስተው ውይይት የሚደረግባቸው ሀሳቦች ጥራትም ነው። ሀሳቦቹ ለጉባኤው የማይመጥኑ በአጠቃላይ የእግር ኳሱን እድገት የማያመላክቱ ናቸው ፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በተገኘባቸው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች ሲነሱ የነበሩ ሀሳቦች “ፌዴሬሽኑ የስታዲየም ገቢያችንን አልሰጠንም፤ እከሌ የሚባል ዳኛ በእኛ ክለብ ላይ ችግር አለበት፤ ሁልግዜ ሲያጫውተን ለተቃራኒ ቡድን ያደላል” በሚል ፣ዳኞችን መውቀስ ላይ ትኩረት ያደረጉ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የወሰናቸውን ውሳኔና የቆዩ ጉዳዮችን በማንሳት መነታረክ የበዛበት ውይይት መሆኑን ተገንዝቧል።

በጠቅላላ ጉባኤዎቹ ወቅት የሚነሱት አብዛኞቹ ጉዳዮች ከነገ ይልቅ ትላንት ላይ ያጠነጠኑ እና ጊዚያዊ እና ትንንሽ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡ ለዚህ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሚያቀርበው ሪፖርትም አንዱ መነሻ ነው፡፡

የጠራ አደረጃጀት (clear organization) አንዱ የማስፈፀም አቅም ገፅታ ነው፡፡ ባልተስተካከለ አደረጃጀት የተፈለገው ዓይነት መሳሪያ ቢሰበሰብና የሰው ሀይል ቢከማችም ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የፌደሬሽኑም የማስፈፀም አቅም ድክመት ከአደረጃጀት (organization) ከአሰራር (መመሪያዎች ደንቦች የአሰራር ማንዋሎችን) እና ከብቁ የሰው ሀይል እጥረት የሚመነጭ ችግርም ነው፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በቀጣይ ስለ ሌሎች የፌዴሬሽኑ መዋቅራዊ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው ላይ እይታቸውን የሚያካፍሉን ይሆናል።


ስለ ጸሀፊው


አቶ ገዛኸኝ ወልዴ

ስራ:

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ

የትምህርት ደረጃ፡

የማስተርስ ዲግሪ በህዝብ አስተዳደር እና የልማት አመራር

ቢኤ ዲግሪ በኢንፎርሜሽን ሳይንስ

የፊፋ የአስተዳደር እና አመራር ስልጠና የወሰዱ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *