ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ62 አመታት በፊት ከዚህ አመት ውድድር አስተናጋጇ ግብጽ እና ጎረቤት ሀገር ሱዳን ጋር በመተባበር የመሰረተችው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)፤ ለ32ኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው የአህጉሪቱ ትልቁ የእግር ኳስ ድግስ ዛሬ ከምሽቱ 5:00 ግብጽ ከ ዚምባቡዌ በሚያካሂዱት ጨዋታ ይጀመራል፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ ከውድድሩ አስቀድሞ በብዙ መንገድ ያከናወናቸው ማሻሻያወች የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ለየት እንደሚያደርጉት እየተነገረ ይገኛል፡፡

ለመሆኑ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ምን ምን አዳዲስ ነገሮችን ይዞ መጥቷል?

የውድድር ወቅት ለውጥ

ከአፍሪካ ዋንጫ የከዚህ ቀደም ፈተናዎቹ አንዱ፡  የውድድሩ ወቅት ተወዳጆቹ የአውሮፓው የክለብ ውድድሮች የፉክክር ጡዘት ላይ በሚደርሱበት የጥር ወር ላይ የሚከናወን በመሆኑ እና እርሱን ተከትሎ በታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች እና የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አፍሪካውያን ከዋክብትን ለውድድሩ ትለቃላችሁ አትለቁም በሚል የሚገጥመው እሰጥ-አገባ ነበር፡፡

ነገር ግን አዲሱ የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ለዚህ ጉዳይ የመጨረሻ እልባት የሰጡት ገና በተመረጡበት አመት ነበር፡፡ ውሳኔያቸውም የአፍሪካ ዋንጫ፡ ከዚህኛው ወድድር ጀምሮ የክለብ ውድድሮች በሚጠናቀቁበት ወቅት ማለትም በሰኔ እና ሀምሌ ወራት እንዲከናወን የሚል ነበር፡፡

የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ማሳደግ

በአራት ተሳታፊ ሀገራት ውድድሩን የጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ፡ ዘንድሮ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ክብረወሰን በሆነ መንገድ በማሻሻል 24 አድርሶታል፡፡

የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር መጨመር የውድድሩን ጥራት ይቀንሰዋል፡ እንዲሁም አስተናጋጅ ሀገራትን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት አስቸጋሪ ያደርገዋል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፤ በተቃራኒው ደግሞ የመድረኩ መስፋት፡ ሀገራት እንደዚህ ላሉ ትልልቅ ውድድሮች የማለፍ እውነተኛ ተስፋ ስለሚኖራቸው እግር ኳሱን ያሳድገዋል የሚል እምነት ያላቸውም ይገኛሉ፡፡

እነዚህ አካላት እንደ ቡሩንዲ፡ ማዳጋስካር እና ሞሪታኒያ ያሉ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈው የማያውቁ ሀገራት ለዚህኛው ውድድር እንዲያልፉ፡ የተሳታፊዎች ቁጥር መጨመሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነሳሉ፡፡

ትክክለኛውን መልስ በጊዜ ሂደት የምንመለከተው ቢሆንም፡ ዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫው ካመጣቸው አዳዲስ ነገሮቹ አንዱ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር መጨመር ነው፡፡

በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (VAR) መጀመር

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንመለከተው ሌላኛው አዲስ ነገር፡ ከሩብ ፍጻሜው ጀምሮ የምንመለከተው በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነትን ነው፡፡

ነገር ግን ቴክኖሎጂው በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ እንዳጋጠመው አይነት የቴክኒክ እክል እንዳይገጥመው ብዙዎች ስጋታቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የሶስት ደቂቃው የማቀዝቀዣ እረፍት

እንደ አለምአቀፉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር መረጃ ከሆነ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ወቅት በግብጽ የሚኖረው የሙቀት መጠን እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ ይችላል፡ ይሔ ደግሞ ለተጫዋቾቹ ጤንነት አስጊ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

በዚህም ምክንያት ተጫዋቾቹ በየጨዋታዎቹ ወቅት በ30ኛው እና 75ኛው ደቂቃ እያንዳንዳቸው ለ90 ሰከንድ የሚቆዩ የማቀዝቀዣ እረፍቶችን እንዲያገኙ የሚደረግ ይሆናል፡፡

የትኞቹ ብሔራዊ ቡድኖች ለሻምፒዮንነት ይጠበቃሉ

የአስተናጋጇ ግብጽ ብሔራዊ ቡድን፡ ሳዲዮ ማኔን እና የትውልዱን ከዋክብት የያዘችው ሴኔጋል፡ ጋና፡ የሄርቬ ሬናርድ ሞሮኮ እንዲሁም ናይጀሪያ ይህንን ውድድር የማሸነፍ የተሻለ እድል ካላቸው ሀገራት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

የትኞቹ ከዋክብትስ በውድድሩ ሊደምቁ ይችላሉ

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊዎቹ ሞሀመድ ሳለህ እና ሳዲዮ ማኔ እንዲሁም የቡድን አጋራቸው ናቢ ኬታ፣ ሞሮኳዊዉ ሀኪም ዚየች፣ ሴኔጋላውያኑ ግዙፍ ተከላካዮች ሳሊፍ ሳኔ እና ካሊዱ ኩሊባሊ፡ የዚምባብዌው ኮከብ ካማ ቢሊያት እንዲሁም ደቡብ አፍሪካዊው ፔርሲ ታዎ አይነት ተጫዋቾች የውድድሩ ድምቀቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚጠበቁ ከዋክብቶች ሲሆኑ፣ በተጨማሪም የውደድሩ ክስተት የሚሆኑ ሌሎች ተጫዋቾች እና ብሔራዊ ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይጠበቃል፡፡

 

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *