የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ቴክኒካዊ እንቅስቃሴን እንደሚገመግሙ ኮንፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በቅርቡ አስራ አምስት አባላት ባሉት የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ የቴክኒክ ጥናት ቡድን አባል ሆነው የተመረጡት አሰልጣኙ ፤ ከካፍ የቴክኒክ አማካሪው ሚ/ር ዤን ሚካኤል ቤንዜት ጋር በመሆን በምድብ ሁለት የሚገኙትን እና ከቅዳሜ ጀምሮ በጥንታዊቷ አሌክሳንድሪያ ከተማ ውድድራቸውን የሚጀምሩትን የናይጀሪያ፣ ጊኒ፣ ቡሩንዲ እና ማዳጋስካር ብሔራዊ ቡድኖች፡ በውድድሩ ወቅት የሚኖራቸውን ቴክኒካዊ እንቅስቃሴ የሚገመግሙ ይሆናል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የአሰልጣኞች ኢንስትራክተር የሆኑት አብርሀም መብራቱ ፡ ውድድሩ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ደረጃ ደርሶ ወደ ዋና ከተማዋ ካይሮ እስኪመለሱ ድረስ በአሌክሳንድሪያ የሚሰነብቱ ሲሆን፣ በቆይታቸውም ከሙያ አጋራቸው ጋር በመሆን በየጨዋታዎቹ የሚታዩትን የየቡድኖቹን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከቴክኒክ አንጻር የሚገመግሙ ሲሆን በየጨዋታዎቹ ጥሩ የሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾችንም በኮከብነት የሚመርጡ ይሆናል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ የሴቶች እግር ኳስ ልማት ሀላፊ የሆነችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ወ/ሪት መስከረም ታደሰ በበኩሏ፡ የዚሁ ምድብ ብሔራዊ ቡድኖች የፕሮቶኮል ጉዳዮች ሀላፊ በመሆን እንደምታገለግል ለማወቅ ተችሏል፡፡