በአቶ ኤርሚያስ አየለ | የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ


አዲስ አበባ – ሰኔ 11/2011 ዓ.ም

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከአስራ ስምንት አመታት በፊት በርካታ ህዝብ የሚሳተፍበት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችን ማዘጋጀት ሲጀምር፡ በሀገራችን ሕዝባዊ ስፖርት ብዙም ያልተስፋፋበት እና በህብረተሰቡም ዘንድ መንገድ ላይ ወጥቶ ስፖርት መስራት እንደ ብርቅ የሚታይበት ወቅት ነበር፡፡

ጅማሮ

የሀገራችን ብርቅዬ አትሌቶች አንጸባራቂ ድል ባስመዘገቡበት የሲዲኒ ኦሊምፒክ፡ በተለይም ፍጹም አይረሴ በሆነው እና ጀግናው አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ኬንያዊዉ ፖል ቴርጋትን አንገት ላንገት ተናንቆ የ10,000 ሜ ባለድል በሆነበት ውድድር ማግስት፡ እንግሊዝ ሀገር የሚካሄደው የግሬት ኖርዝ ራን (Great North Run) የጎዳና ላይ ሩጫ፡ አዘጋጆች ለኃይሌ በሀገራችን መጥተህ ተወዳደር ሲሉ ግብዣ ባቀረቡበት ወቅት ነበር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተጠነሰሰው፡፡

ኃይሌ በወቅቱ ግብዣውን ካቀረቡለት አካላት ጋር መሰል ውድድር በሀገሩ ኢትዮጵያ አብረውት እንዲያዘጋጁ ባደረገው የተሳካ የማግባባት ስራ ምክንያትም፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በህዳር ወር 1994 ዓ.ም አሀዱ ብሎ መከናወን ጀመረ፡፡

የመጀመሪያውን እና ታሪካዊዉን ውድድር አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ብርሀኔ አደሬ ሲያሸንፉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩት የተቀሩት ተሣታፊዎች ደግሞ ውድድሩን እንደ ውድድርነት ብቻ ሳይሆን እንደመዝናኛነት በመቁጠር በየጥቂት ኪሎሜትሮቹ እየቆሙ እና እረፍት እየወሰዱ ማጠናቀቃቸውን በሚገባ አስታውሳለሁ ፡፡

እኔም እንደ አንድ የታላቁ ሩጫ የመጀመሪያው ውድድር ተሣታፊ ፡ ለአትሌቶቻችን ያለኝ አድናቆት ይበልጡን የጨመረብኝ ለዚህ ውድድር ልምምድ ለማድረግ ሰፈሬ የሚገኘው ጃን ሜዳ ዱብዱብ ስል አትሌቶቻችን ላይ እመለከት በነበረው ጠንካራ የስራ ስሜት በመደነቅ ነበር፡፡

ምክንያቱም አትሌቶቻችን ለውድድሩ ሲዘጋጁ በቀን ሁለቴ፡ በሳምንት ደግሞ ለስድስት ጊዜያት ያክል ይሰሩት የነበረው ከባድ ልምምድ ምን ያክል አድካሚና ፈታኝ እንደነበር በቅርበት ስለተመለከትኩ ነው፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በግሬት ኖርዝ ራን እና በኃይሌ ግንኙነት ሲጀመር  ፕሮጀክቱ አሁን የደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ ማንም አልገመተም ነበር፡፡ ነገር ግን በጠንካራ ስራ እና በመላው የአትሌቲክስ ማህበረሰብ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ አድጎና ተመንድጎ አሁን የሚገኝበት የስኬት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

እድገቱንም በሚከተሉት መንገዶች መግለጽ ይቻላል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት

  • የተሣታፊው ቁጥር ውድድሩ ሲጀመር ከነበረበት 10,000 ከአራት እጥፍ በላይ በመጨመር 45,000 ደርሷል፡፡
  • ከነበረው አመታዊውን የ10,000ሜ ውድድር የማዘጋጀት አቅም ብቻ ተመንድጎ፡ በሀገር ውስጥ  ብቻ ሳይወሰን በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር  ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅም መፍጠር የቻለ ሲሆን የህጻናት፣የአካል ጉዳተኞች፣ የሴቶች፣ የግማሽ ማራቶን፣ የዱላ ቅብብል እና ሌሎች ከስድስት በላይ በርካታ ህዝብ የሚሳተፍባቸውን ውድድሮች የሚያዘጋጅ ጠንካራ ተቋም መሆን ችሏል፡፡
  • በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ እና የአለም አቀፍ ተሳታፊዎችን ትኩረት የሚስብ ውድድር መሆን ችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በስፖርት ቱሪዝም መስክ ለሀገራችን ተጨማሪ የኢኮኖሚ እድገት አጋዥ ለመሆን በቅቷል፡
  • “ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ” በሚል መርህ ከሩጫው ተሳታፊዎች በሚያሰባስበው ተጨማሪ ገንዘብ ከብር 15,000,000.00 (አስራ አምስት ሚሊየን ) በላይ ለበጎ አድራጊ ተቋማት ብዙዎችን ለመርዳት ለግሷል፡፡
  • ውድድሩ በሚያገኘው ያልተቋረጠ አለምአቀፍ የሚዲያ ሽፋን ምክንያትም የሀገራችንን በጎ ገጽታ ለተቀረው ዓለም በማስዋወቅ በኩልም የራሱን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ በብዙ መንገድ ስኬታማ የሆነ ተቋም ሆኗል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስኬታማነት ምስጢሮች

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ከላይ በጥቂቱ ለተዘረዘሩት ስኬቶቹ ያበቁትን አንኳር ጉዳዮች ደግሞ ቀጥሎ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

1. ኢትዮጵያ በአለም በምትታወቅበት የሩጫ ስፖርት ላይ መስራቱ

በተለይም ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በቀላሉ ለመሳብ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ መሰማራቱ ለእድገቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶለታል፡፡

2. የሀይሌ ገ/ስላሴ ያልተቋረጠ ድጋፍ

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ለታላቁ ሩጫ መሻሻል ከሚሰጠው ያልተቋረጠ ድጋፍ ባለፈ፡ የተቋሙ መስራች እና የቦርድ ሰብሳቢ በመሆኑ ብቻ፡ እርሱ ያለው ተቀባይነት በድርጅቱ ስኬታማነት ላይ ያለው አዎንታዊ ተጽዕኖ በጉልህ የሚታይ ነው፡፡

3. በየጊዜው ማሻሻያና አዲስ ነገር ማምጣቱ

ታላቁ ሩጫን ለዚህ ውጤታማነት ካበቁት ጉዳዮች መካከል አንዱ ራሱን ለአዳዲስ ሀሳቦች፣ አሰራሮች እና ማሻሻያወች ሁሌም ዝግጁ ማድረጉ እና መተግበሩ ነው፡፡

ታላቁ ሩጫ ራሱን ለማሻሻል በሚያደርገው ያልተቋረጠ ጥረት ምክንያት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር፡ በዘርፉ ባለሞያዎች ዘንድ በአሁኑ ወቅት አለም ላይ ሊሮጥባቸው ከሚገቡ 10 ውድድሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ሊመሰከርለት ችሏል፡፡

4. በወጣትና ጠንካራ ሙያተኞች መደራጀቱ

ከከፍተኛ የቦርድ አመራር እስከ በጎ ፈቃደኛ አገልግሎት ሰጪዎች ድረስ እንዲሁም በተቋሙ ውስጥ በሚገኙ እያንዳንዱ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ ትክክለኛ እና ብቁ ባለሞያዎች መኖራቸው፤ ለስራ እና ፈጠራ አመቺ የሆነ የስራ ከባቢ መኖሩ እና በሰራተኞች መካከል ያለው ቤተሰባዊ ቅርርብ እንዲሁም ተቋሙ ትክክለኛ እና ሊተገበሩ የሚችሉ ዕቅዶችን የሚያዘጋጁ እና ለተፈጻሚነቱም በጋራ በሚረባረቡ ጠንካራ ሰራተኞች የተደራጀ መሆኑ ሌላኛው የስኬቱ ምንጭ ነው፡፡

5. ከባለድርሻ አካላት ጋር የመሰረተው መልካም ግነኙነት

እንደዚህ አይነት ብዙዎችን አሳታፊ የሆኑ ውድድሮችን በብቃት እና ጥራት ለማዘጋጀት ከውስጥ ጥንካሬ ባለፈ የሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ በእጅጉ አሰፈላጊ ነው፡፡

ታላቁ ሩጫም እዚህ የስኬት ጫፍ ላይ ለመድረስ በሁሉም መንገድ አብረውን ከነበሩት ስፖንሰሮች፡ ተሳታፊዎች፡ ሚዲያዎች እና የሚዲያ ባለሞያዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የፈጠርነው መልካም የሚባል ግንኙነት ትልቅ እገዛ ነበረው፡፡

በአጠቃላይ እነዚህ እና ሌሎች እዚህ ጽሁፍ ላይ ያልተጠቀሱ መልካም ተሞክሮዎቻችን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን አሁን ለደረሰበት ትልቅ ደረጃ እንዳደረሱት ይሰማኛል፡፡


ስለ ጸሀፊው


አቶ ኤርሚያስ አየለ

የስራ ሁኔታ፡

  • ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የሰሩ እና በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ፡፡
  • በስኮትላንድ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ረዳት የፕሮግራም አዘጋጅ የነበሩ፡ እንዲሁም ለአምስት አመታት ያክል የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለገሉ፡፡

የትምህርት ዝግጅት፡

  • ሁለተኛ ዲግሪ፡ በስፖርት ማኔጅመንት ከሊድስ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ፡ እንግሊዝ ሀገር
  • የመጀመሪያዲግሪ፡ በሜካኒካል ኢንጂኒየሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *