አዲስ አበባ – ግንቦት 26/2011 ዓ/ም – ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ባሳለፍነው ሳምንት በግብጽ አሌክሳንድሪያ፡  የግብጹ ዛማሌክ እና የሞሮኮው ቤርካኔ ክለቦች ያካሄዱትን የ2019 የካፍ ክለቦች የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ፡ ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን የዋና ዳኝነት ሀላፊነታቸውን መወጣታቸውና፡ ባለሜዳው ዛማሌክም በመለያ ምቶች አሸንፎ የውድድሩ ሻምፒዮን  መሆኑ ይታወሳል፡፡

ይሁንና እንደ ግብፅ እና አልጀሪያ ጋዜጦች ዘገባ ከሆነ፡ በውጤቱ ደስተኛ ያልሆኑት የካፍ ሶስተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የበርካኔ ክለብ የክብር ፕሬዝዳንት ፋውዚ ሌክያ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኀላ የእለቱ አርቢትር ባምላክ ተሰማ ላይ አካላዊ ጥቃት መፈጸማቸው በስፋት እየተዘገበ ይገኛል፡፡

እንደመረጃወቹ ከሆነ፡ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ፡ በጨዋታ ሪፖርታቸው ላይ የተፈጸመባቸውን ጥቃት አስመልክቶ ማመልከቻ ማስገባታቸውን እና ፋውዚ ሌክያ ጥቃቱን ሲፈጽሙ የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃው ለካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ እንደደረሰ እና እንደተመለከቱት፡ “ቦቶላ ሄብዶ” የተሰኘው የአልጀሪያ ጋዜጣ በፈረንሳይኛ እትሙ አስነብቧል፡፡

ይህንን ጉዳይ የተከታተሉት የቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሀያቱ አማካሪ  አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ግልጽ ደብዳቤ መፃፋቸውን ልዩ ስፖርት አረጋግጣለች፡፡

አቶ ፍቅሩ በደብዳቤያቸው ላይ፡ ፌዴሬሽኑ በድርጊቱ ዙሪያ ለ ፊፋ እና ካፍ ግልጽ የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባት እና ከባምላክ ጎን በመቆም ጥፋተኛው ግለሰብ ላይ ተገቢው አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቅ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

አቶ ፍቅሩ አክለውም የፌዴሬሽኑ ፍላጎት ከሆነ፡ ጉዳዩን በህግ አግባብ የሚከታተሉ ጠበቆችን ከአዲስ አበባም ሆነ ከአውሮፓ ለማገናኘት ፍላጎታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ፡ በነገው እለት የ2019 የአፍሪካ ክለቦች ውድድር አፈጻጸምን አሰመልክቶ ድንገተኛ የስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በፈረንሳይ፡ ፓሪስ ለማካሄድ ጥሪ እንዳስተላለፉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፡ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና ጸሀፊው በዚህ ሰዓት በፊፋ ጉባኤ ለመካፈል እዛው ፓሪስ ይገኛሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፋውዚ ሌክያ ባምላክ ላይ በፈጸሙት ጥፋት፡ ለእድሜ ልክ ከእግር ኳስ የሚያርቃቸው ቅጣት ሊያስጥልባቸው እንደሚያስችል ቢታሰብም፡ አዲሱ የካፍ ፕሬዝዳንት ከሞሮኮዎቹ ጋር ያላቸው በእጅጉ የጠበቀ ግንኙነት ውሳኔው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጉዳዩ ዙሪያ ስለያዘው አቋም ላቀረብንለት ጥያቄ፡ “ለካፍ አቤቱታ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን” በህዝብ ግንኙነቱ በኩል አሳውቆናል፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *