አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011 ዓ/ም – ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አስርት አመታት፡ ሰንደቅ አላማዋን በአለም የአትሌቲክስ ውድድር አደባባዮች በኩራት ከፍ አድርገው ያውለበለቡ በርካታ ስመጥር እና ውጤታማ አትሌቶች መፍለቂያ ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡

ዛሬም ይህንን ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ታሪካዊ የውጤታማነት ጉዞ ለማስቀጠል፡ በርካታ ወጣት አትሌቶች ሌት ከቀን ሳይለዩ፡ ነገ ላይ የትላንት ባለድሎች የደረሱበት የስኬት ማማ ላይ ለመድረስ ከውድድር በላይ ፈታኝ የሆነውን የአትሌቲክስ ልምምድ አስቸጋሪ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ሆነው ዘወትር እየከወኑ ይገኛሉ፡፡

ውጤታማው የረጅም ርቀት ሩጫ አሰልጣኝ ሀጂ አዴሎ ለእነዚህ ባለ ብሩህ ተስፋ አትሌቶቸ፡ ወደ ውጤታማነት ለመገስገስ ይጠቅሟቸዋል ያሏቸውን ሙያዊ ምክሮች ከሰፊው ልምዳቸው በመጨለፍ ከዚህ እንደሚከተለው አካፍለዋቸዋል፡፡

በቅድሚያ ግን አሰልጣኙ፡ የሩጫ ስፖርት፡ የዓላማ ጽናትን የሚፈልግ እና ከጠንካራ ስራ በስተቀር ምንም አይነት አቋራጭ የሚባል መንገድ የሌለው ስፖርት በመሆኑ፡ ወደዚህ ስፖርት የሚገባ ማንኛውም ሰው ከሁሉም በላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ የአእምሮ ዝግጅት እንደሚስፈልገው ማስታወስ ይገባል ይላሉ፡፡

ተሰጥኦ እና ጠንካራ ስራን አብሮ ማስኬድ መቻል

ተፈጥሯዊ ተስጥኦ እና ጠንካራ ስራን ባለሞያዎቹ፡ በሩጫ ስፖርት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉት ግብአቶች መካከል ‘የማይነጣጠሉት’ ሲሉ ይገልጹዋቸዋል፡፡

የበርካታ አትሌቶች ፈተናም እነዚህን ሁለት ነገሮች አጣጥሞ መሄድ አለመቻል ነው፡፡ አንዳንድ አትሌቶች ተፈጥሯዊው ተሰጥኦ አላቸው ነገር ግን ታታሪነቱ ይጎድላቸዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ፍላጎቱ እና ቁርጠኝነቱ ይኖራቸው እና ተሰጥኦው ይጎድላቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አይነት አትሌቶች በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ፈጽሞ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

ስለዚህ ሁለቱን ነገሮች አጣጥሞ መቀጠል፡ አንድ አትሌት ነገ ሊደረስበት ወዳሰበው ከፍታ ለመውጣት ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን ማወቅ፡ ማመን እና ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከሁለቱ አንደኛው ኖሮ ሌላኛው ከሌለ እንደሚታሰበው ውጤታማ መሆን ስለማይቻል፡፡

የአሰልጣኝን ምክር መስማት

ማንኛውም አትሌት ከእርሱ በእድሜ፡ በእውቀት እና በልምድ የሚበልጠውን እና ለአትሌቱ ውጤታማነት ከእርሱ እኩል ታች እና ላይ ለሚደክመው አልጣኙ ተገቢውን ክብር መስጠት እና ለሚያወጣቸው መመሪያዎች ታዛዠ መሆን፡ ሌላው አትሌቱን ለውጤት የሚያበቃው ምስጢር ነው፡፡

አሰልጣኙ የአንድን አትሌት ሁለንተናዊ ሁኔታ በሙያዊ እይታ ከገመገመ በኋላ፡ አትሌቱን ወደ በለጠ ውጤታማነት ለማምጣት ይሆናሉ/ይጠቅማሉ የሚላቸውን የስልጠና፡ የእረፍት እና የአመጋገብ ፕሮግራሞቸን ከሌሎች ባለሞያዎች ጋር በመነጋገር ያዘጋጀል፡፡ ነገር ግን አትሌቱ አሰልጣኙ የሰጡትን ይህንን የቤት ስራ በሚገባ የማይከውን ከሆነ፡ ውጤታማ ለመሆን በእጅጉ ይቸገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄው አሰልጣኝን ማክበር እና ትእዛዛቱን በተገቢው ሁኔታ መፈጸም ነው፡፡

በቂ እረፍት ማድረግ

የአትሌቲክስ ስፖርት በሚጠይቀው እጅግ ፈታኝ የልምምድ እና የውድድር ሀይል ምክንያት፡ በባህሪው ሲበዛ አድካሚ እና አሰልቺ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሆኖም ግን፡ ዓላማው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ለሆነ አትሌት፡ ብቸኛው መፍትሔ ይህንን ሁሉ በጽናት ተቋቁሞ ማለፍ ብቻ ነው፡፡ በእንዲህ አይነት ተደጋጋሚ እና አሰልቺ ሁኔታ ውስጥ ጥንካሬን እንደያዙ በውጤታማነት ለመቀጠል ብቸኛው መፍትሄ ደግሞ ለሰውነት በቂ የሚባል የእረፍት ጊዜ መስጠት ነው፡፡

ከልምምድ – ልምምድ፤ ከውድድር – ውድድር የሚኖረው የጊዜ ክፍተት በቂ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም እረፍት ሲባል የአካል/የሰውነት ብቻ ማለት አይደለምና፡ በልምምድ እና ውድድር መደራረብ እንዲሁም በሌሎች የግል እና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ከሚፈጠር የስነ-ልቦና ጫናም፡ የመንፈስ እረፍት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከባለሞያዎች ጋር በመነጋገር በቂ እና ለበለጠ ውጤታማነት የሚያዘጋጅ የእረፍት ካሌንደር ማዘጋጀትም ይመከራል፡፡

አመጋገብን ማስተካከል

ለአትሌቶች ውጤታማነት ሌላኛው እጅገ ጠቃሚ ጉዳይ ለስፖርቱ አስፈላጊ የሆነ የአመጋገብ ልማድን መከተል መቻል ነው፡፡ ስፖርተኞች በልምምድ እና ውድድር ምክንያት እጅግ በርካታ ጉልበት ስለሚያፈሱ ይህንን ሀይል በቶሎ ሊተኩ እና ለቀጣዩ ስራ የሚያዘጋጁ ሀይል እና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን እንዲያዘወተሩ በስፖርት የስነ-ምግብ ባለሞያዎች ይመከራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እጅግ አድካሚ ከሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በኋላ ሰውነታችን እና ሰርአተ ምግባችንን ለሌላ አስቸጋሪ ስራ የማይጋብዙ፡ ፈሳሽ እና ቀለል ያሉ ምግበችን መመገብ ይኖርብናል፡፡

እዚህ ጋር ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው አንድ ጉዳይ አለ እርሱም፡ አልፎ አልፎ አትሌቶቻችን ከልምምድ በኋላ ጥሬ ስጋ ሲመገቡ መመልከቴን ነው፡ ነገር ግን ይሄ ፈጽሞ የሚመከር ነገር አይደለም፡ ምክንያቱም ምግቡ ቶሎ ስለማይዋሃድ የሰውነታችንን መልሶ የማገገሚያ ጊዜ በእጅጉ ያረዝመዋል፡ ያ ደግሞ እራሳችንን ለበለጠ ድካም ይዳርገናል፡፡

ሌላው አመጋገባችንን ማስተካከላችን የሰውነታችንን የክብደት ሁኔታ መቆጣጠር ያስችለናል፡፡ አትሌቶች እንደሚወዳደሩበት የርቀት አይነት የሰውነታቸውን የክብደት እና የጥንካሬ ሁኔታ ማስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡

ለምሳሌ እንደ ማራቶን ያሉ የረጀም ርቀት ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች፡ የሰውነት መጠናቸው ቀለል ያለ እና የብርታት ልምምዶች ለይ ጠንክረው የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ይመከራል፡ ታዲያ እንደዚህ ያለ የሰውነት አቋም እና የብርታት ሁኔታን ለማምጣት፡ አመጋገብን ማስተካከል ከላይ ከተገለጹት ሌሎች ጠቃሚ ነገሮች ጋር ተደምሮ ለአንድ አትሌት ውጤታማነት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ስነ-ምግባር

ስነ-ምግባር በስፖርቱ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የህይወት መንገድ የሰው ልጆች ሁሉ ሊኖራቸው የሚገባ መልካም እሴት ነው፡፡ አትሌቶች ላይ ደግሞ ይህ ነገር  በአጅጉ ይፈለጋል፡፡ ምክንያቱም እነሱ፡ ሀገር ወካይ ናቸው፡ ምክንያቱም እነሱ፡ ለሌሎች አርዓያ ናቸው፡፡

ስለዚህ አትሌቶች ለስፖርት ከተከለከሉ ንጥረ-ነገሮች መራቅ፡ ለታላላቆቻቸው አክብሮት መስጠት እና ከእነርሱ ልምድ መቅሰም፡ እንዲሁም ለተተኪዎቻቸው ደግሞ በመልካም ነገር ሁሉ አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመጨረሻም፡ ማንኛውም በሩጫው አለም ውስጥ ትልቅ የሚባለው ደረጃ ላይ ለመድረስ ህልም ያነገበ አትሌት ከላይ የተዘረዘሩትን ቁምነገሮች ተግባራዊ ማድረግ ከቻለ፡ ልምምዱን አንድ ብሎ ሲጀምር ያለመውን ታላቅ እና ውጤታማ አትሌት የመሆን ምኞትቱን እንደሚያሳካው አልጠራጠርም፡፡


© ይህ ጽሁፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ www.ethiopianrun.org ድረ-ገጽ ነው፡፡ 

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *