ነገሩ እንዲህ ነው… እንግሊዛዊው የረጅም ርቀት ሯጭ ሞ ፋራህ፡ ረቡዕ ሚያዚያ 16/2011 ዓ.ም፡ እሁድ እለት ከሚካሄደው የ2019ኙን የለንደን ማራቶን አሰመልክቶ  በተዘጋጀ አለምአቀፍ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፡ በኢትዮጵያ በነበረው የሶስት ወራት የዝግጅት ቆይታው ባረፈበት ያያ አፍሪካ አትሌቲክስ ቪሌጅ  የተፈጸመበት የ2500 የእንግሊዝ ፓውንድ፡ ሁለት ተንቀሳቃሽ  ስልኮች እና የባለቤቱ ስጦታ የሆነ የእጅ ሰዓት የስርቆት ወንጀል፡ ዝግጅቱ ላይ መጠነኛ ችግር እንደፈጠረበት እና ነገሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለሆቴሉ ባለቤት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱ እንዳሳዘነው ይገልጻል፡፡ ይህንን ነገር የሰሙት የእንግሊዝ ብዙሀን መገናኛዎችም ነገሩን ያራግቡታል፡፡

ይህንን ጉዳይ ከሚዲያዎች የሰማው አትሌት ኃይሌም፡ የሞ ፋራህን ድርጊት አስቀድሞ የታሰበበት እና በከፍተኛ ጥረት የተገነባውን መልካም ስሜን እና ቢዝነሴን ሆን ብሎ ለመጉዳት ያለመ ነው፡ ሲል ጠንከር ባሉ ክሶች የታጀበ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ኃይሌ በመግለጫው ላይ፡ ሞ ፋራህ ድርጊቱ ተፈጸመብኝ ካለበት ቀን ጀምሮ ጉዳዩን ለፖሊስ በፍጥነት በማሳወቅ አስፈላጊው ምርመራ እንዳስደረገ እና አምስት የሆቴሉ ሰራተኞችም ለተጨማሪ ምርመራ በሚል ለሶስት ሳምንታት ያክል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምንም አይነት ፍንጭ ባለመገኘቱ መለቀቃቸውን ይገልጻል፡፡

መግለጫው አክሎም፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሆቴሉ በግልጽ ባስቀመጠው ፓሊሲ መሠረት አንድ ደምበኛ ወደ ሆቴሉ ሲመጣ ከ10, 000 ብር በላይ ከያዘ ማሳወቅ እንዳለበት ወይም የደህንነት ሳጥን እንዲሰጠው መጠየቅ እንዳለበት ቢደነግግም ሞ ፋራህ ግን ሁለቱንም አላደረገም፡ በዚህም ምክንያት ሆቴሉ በህግ አግባብ ተጠያቂ አይሆንም፡ ነገር ግን ሞ ፋራህ ካለው አለም አቀፍ እውቅና እና ከኃይሌ ጋር ባላቸው መልካም ወዳጅነት ምክንያት አስፈላጊው ጥረት ቢደረግም ስለዘራፊዎቹ ብቻ ሳይሆን ስለመዘረፉም ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም ይላል፡፡

የሀይሌ መግለጫ በዚህ አያበቃም፡

1. ሞ ፋራህ በሆቴል ቆይታው እስከ 50% የሚደርስ ቅናሽ ቢደረግለትም የተጠቀመበትን 81,000 ብር ሳይከፍል መሄዱን
2. በቆይታው ወቅት በእሱ እና የቅርብ ሰዎቹ ያልተገቡ ድርጊቶች እና ባህሪያት በሆቴሉ ሰራተኞች ተደጋጋሚ ቅሬታወች ይቀርብበት እንደነበር እና
3. በሆቴሉ ጅምናዚየም ውስጥ ልምምዴን ኮረጃችሁ በሚል ምክንያት ባልና ሚስት አትሌቶች ላይ ጥቃት በማድረሱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት በመሀል ገብቼ በማሸማገሌ ጉዳዩ ወደ ህግ እንዳያመራ የበኩሌን እንደተወጣሁ ይታወቅልኝ ይላል፡፡

ከሁሉ በላይ ግን ሀይሌ፡ ሞ ፋራህ እኔን ለማጥቃት ሆነብሎ እንዳደረገው ማሳያ ነው የሚለው፡  ጋዜጣዊ መግለጫውን ከመስጠቱ ሶስት ቀናት አስቀድሞ የላከለትን አጭር የጽሁፍ መልዕክትን ነው፡፡

ከሞ፡  ለሀይሌ የደረሰው መልዕክት ሲጠቃለል ” በተደጋጋሚ ጊዜ ላገኘህ ብሞክርም አልቻልኩም፡ በለንደኑ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለተፈጠረው ነገር የምለው ይኖረኛል፡ በዚህ ምክንያት በግል ዝናህና በቢዝነስህ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ ሀላፊነቱን አልወስድም ይላል::”

ሀይሌ መግለጫውን ሲያጠቃልልም፡ በመልካም ስሜ እና በንግዴ ላይ ለተቃጣብኝ ስም የማጉደፍ ተግባር ጉዳዩን በህግ እንዲዳኝ አደርጋለሁ ይላል፡፡

የአለም ብዙሀን መገናኛዎችም የሁለቱን ታላላቅ አትሌቶች የአደባባይ እሰጥ-አገባ በፊት ገጾቻቸው ላይ በመለጠፍ ሰፊ ሽፋን እየሰጡት ይገኛሉ፡፡ እውነት ከየትኛው ወገን እንደሆነች ለማጣራት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *